1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ከድርጅትና ንቅናቄ ወደ ፓርቲነት-የኦሕዴድ እና ብአዴን መንገድ

ሰኞ፣ መስከረም 21 2011

ኦሕዴድ እና ብአዴን ፓርቲ ሆነው፣ አርማ እና መተዳደሪያ ደንብ አሻሽለው ለኢሕአዴግ ጉባኤ እየተዘጋጁ ነው። ተንታኞች በሕወሓት ጥላ ስር የነበሩት ሁለቱ ፓርቲዎች ባደረጓቸው ለውጦች እና ማሻሻያዎች "እንደ አዲስ ታድሰናል፣ እንደ አዲስ ተመስርተናል" የሚል መልዕክት ለማስተላለፍ መሞከራቸውን ያምናሉ

https://p.dw.com/p/35peq
EPRDF Logo

ODP & ADP becomes party, what does that mean for Ethiopia? - MP3-Stereo

ብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት ስያሜውን ወደ አማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ከመቀየር ባሻገር የቀደመ አርማውን፣ የልሳናቱን ስያሜ፣ እና በመተዳደሪያ ደንቡ የተወሰኑ አንቀጾች ላይ ማሻሻያ አድርጓል። የፓርቲው አርማ "መደቡ ከላይ አረንጓዴ መሃል ላይ ጎህ ሲቀድ የሚኖር ቀለም (ቢጫ) ሆኖ ከግርጌ ቀይ" እንዲሆን ወስኗል።

የቀድሞው የኦሮሞ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት ወደ ኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ሲቀየር የቀደመ አርማውን ሙሉ በሙሉ ለውጧል። በቀደመ አርማው መሐል ላይ የሚታየውን ዋርካ ብቻ ያስቀረው ኦዲፒ ግብርና እና ኢንዱስትሪን የሚወክሉ ምልክቶችን አስወግዷል።

"እነዚህ ሁለት ፓርቲዎች ስማቸውን በሚያወጡበት፤ ራሳቸውን በሚያደራጁበት ጊዜ ሕወሓት በወታደራዊ ኃይልም፣ በርዕዮተ-ዓለምም በፖለቲካ ሥራም በውጭ ግንኙነትም ከእነሱ እጅግ የላቀ የፖለቲካ ድርጅት ነበረ" የሚሉት አቶ ሐሌሉያ ሉሌ የኦሕዴድ እና የብአዴን ለውጥ የስም ብቻ አይደለም ሲሉ ይናገራሉ። በሕወሓት እገዛ ስማቸውን ሲያወጡ፣ አባላት ሲመለምሉ፣ መተዳደሪያቸውን ሲቀርፁ ነፃ ነበሩ ብሎ መናገር ይቸግራል የሚሉት በአማኒ አፍሪካ የፖሊሲ ጥናት እና አማካሪ ተቋም የጸጥታ እና ፖለቲካ ጉዳዮች ተመራማሪው ሁለቱ ፓርቲዎች ስም በመለወጥ ጠንካራ መልዕክት አስተላልፈዋል የሚል ዕምነት አላቸው። "ዋናው ማሳየት የፈለጉት እንደ አዲስ ታድሰናል፣ እንደ አዲስ ተመስርተናል ከሚል ብዙ አይለይም። ስማቸውን ሲያወጡ በራሳቸው ፍላጎት፣ በራሳቸው አመለካከት፣ ራሳቸው በመሩት ሒደት ማንም ጣልቃ ሳይገባባቸው ስለሆነ ከድሮ ታሪካቸው በእነሱ እና በሕወሓት መካከል እንዲሁም በኢሕአዴግ ውስጥ ከነበራቸው ሚና እና ቦታ ተለያይተዋል" ሲሉ አቶ ሐሌሉያ ያስረዳሉ።

ሁለቱም የፖለቲካ ፓርቲዎች በድርጅታዊ ጉባኤያቸው ከምሥረታቸው ቅርበት ያላቸውን ነባር የተባሉ ሹማምንት አሰናብተዋል። በኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ በኩል መሥራች የነበሩት አቶ አባዱላ ገመዳ እና አምባሳደር ኩማ ደመቅሳን ጨምሮ 14 ነባር የተባሉ አመራሮች ከተሰናባቾቹ መካከል ይገኙበታል። የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ በበኩሉ አቶ ካሳ ተክለብርሐን፣ አቶ ከበደ ጫኔ እና ጌታቸው አምባዬ ከተሰናባቾቹ መካከል ይገኙበታል። ፓርቲው ለማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነት ካቀረባቸው እጩዎች መካከል ለረዥም ዓመታት ታስረው የተፈቱት አቶ መላኩ ፈንታ እና ጀኔራል አሳምነው ፅጌ ይገኙበታል። በኔዘርላንድስ የላይደን ዩኒቨርሲቲ በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ እና ጸጥታ ጉዳዮች ላይ አተኩረው የፒ.ኤች.ዲ. ጥናታቸውን በመሥራት ላይ የሚገኙት አቶ ይነበብ ንጋቱ ኦሕዴድ እና ብአዴን ለውጥ የይስሙላ አይደለም የሚል ዕምነት አድሮባቸዋል። "ኦሕዴድም ሆነ ብአዴን ከተፈጠሩበት ጊዜ ጀምሮ የፖለቲካ ነፃነት አላቸው ተብሎ አይታሰብም። ሕወሓት ለራሱ ሲል የፈጠራቸው በኦሮሚያ እና በአማራ ጉዳይ አስፈሚ" ተደርገው ይቆጠራሉ የሚሉት አቶ ይነበብ ባለፉት አመታት በኢትዮጵያ ከታየው ሕዝባዊ ተቃውሞ ጎን በመቆም ሚናቸውን የመቀየር ጥረታቸው እንደሰመረላቸው ይገልፃሉ። "ኦሕዴድም ሆነ ብአዴን ሲታሙበት የነበረውን ተቀፅላ ናቸው፤ ራሳቸውን የቻሉ አይደለም፤ ተላላኪዎች ናቸው የሕዝባቸውን አጀንዳ አይወክሉም ሲባሉ የነበረውን እንደተላቀቁ፤ ራሳቸውን ነፃ እንዳወጡ በየፓርቲዎቻቸው አዲስ ምዕራፍ መከፈቱን ለማብሰር ይመስለኛል" ሲሉ ያብራራሉ።

የጸጥታ እና ፖለቲካ ጉዳዮች ተንታኙ ፕሮፌሰር መድሕኔ ታደሰ በበኩላቸው ወደ ፓርቲ መቀየራቸው የለወጠው ነገር ቢኖርም በርዕዮተ-ዓለም ረገድ ግልፅ መሆን ያለበት ጉዳይ እንዳለ ገልጸዋል። ፕሮፌሰሩ "በአንድ ግልፅ በሆነ ፕሮግራም አባላትን አደራጅቶ ይንቀሳቀሳል ማለት ነው። ግንባር እና ንቅናቄ ሲሆን ብዙ አመለካከቶችንም የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎችንም ከዘርም ከሐይማኖትም ሊያካትት ይችላል ማለት ነው። አሁን እያደረጉ ያሉት እንደዛ ነው ማለት አይደለም። ምክንያቱም የርዕዮተ-ዓለም እና የፖለቲካ ማኒፌስቶ ጉዳይ በግልፅ አልወጣም። ይኸ ማለት እንግዲህ ራሳቸውን በፓርቲነት ለብቻቸው የሚንቀሳቀሱበት ዕድል ይኖራል ማለት ነው" ሲሉ ተናግረዋል።

ደኢሕዴን የቀድሞውን ጠቅላይ ምኒስትር አቶ ሐይለማርያም ደሳለኝን ጨምሮ በመንግሥት መዋቅሩ ውስጥ ለረዥም ዓመታት ያገለገሉ ፖለቲከኞቹን ከማዕከላዊ እና ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴዎች በጡረታ ማሰናበቱን አስታውቋል። ከተሰናበቱት 24 ፖለቲከኞች መካከል ለኢሕአዴግ ሊቀ-መንበርነት የተወዳደሩት አቶ ሽፈራው ሽጉጤ፣ የቀድሞው መከላከያ ምኒስትር አቶ ሲራጅ ፈጌሳ፣ የቀድሞው የብሔራዊ ባንክ ገዢ አቶ ተክለወልድ አጥናፉ ይገኙበታል። መጠሪያ እና አርማን በመሳሰሉ ጉዳዮች ላይ ውይይት እንደሚደረግ የገለጸው ንቅናቄው እስካሁን የደረሰበት ውሳኔ ስለመኖሩ ያለው ነገር የለም። ሕወሓት በበኩሉ ሊቃነ-መናብርቱን መርጦ፣ ነባር ያላቸውን አመራሮች አሰናብቶ ጉባኤውን አጠናቋል። አራቱ የኢሕዴግ አባላት ጠቅላይ ምኒስትር አብይ አሕመድ ሥልጣን ከጨበጡ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ  ከመስከረም 23 እስከ 25 ቀን 2011 ዓ.ም. በሐዋሳ ከተማ ድርጅታዊ ጉባኤ ያካሒዳሉ። ግንባሩ ለረዥም ዓመታት ሲያቀነቅነው በነበረው ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነትን ጨምሮ በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ልዩነቶች እንዳሏቸው ታይቷል። አቶ ሐሌሉያ እንደሚሉት በሁለቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ የተደረጉት ለውጦች በኢሕአዴግ ላይ የሚያድሩት ተፅዕኖ ቢኖርም ግንባሩን ለክፉ አይሰጠውም።

እሸቴ በቀለ

አዜብ ታደሰ