1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ማቆሚያ ያጣዉ ሞትና መፈናቀል

ሐሙስ፣ መስከረም 24 2011

ከቤንሻንጉል ክልል የተፈናቀሉ ሰዎች ቁጥር 90 ሺህ መድረሱን የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን አስታወቀ።ተፈናቃዮቹ በኦሮሚያ ክልል ምዕራብና ምስራቅ ወለጋ በተለያዩ ቦታዎች ተጠልለዉ እንደሚገኙ ኮሚሽኑ ገልጾ፤ እነሱን ለመደገፍ ህብረተሰቡና ለጋሾች ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርቧል። 

https://p.dw.com/p/3609S
Äthiopien Somalia Vertriebene Menschen
ምስል DW/B. Girma

Displaced people in Oromia - MP3-Stereo


በኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ማንነትን መሰረት ያደረገ ግጭትና መፈናቀል እዚህም እዚያም ይታያል። በሀገሪቱ ከዚህ ቀደም በሀዋሳ ፣በጅግጅጋ ፣ በቤንሻንጉል ፣ በኦሮሚያ በቅርቡ ደግሞ በመዲናዋ አዲስ አበባ አቅራቢያ ቡራዩ በርካቶች ለሞትና ለመፈናቀል ተዳርገዋል።ሰሞኑንም አራት የቤንሻንጉል ክልል አመራር አካላት አሮሚያ ክልል ዉስጥ ስብሰባ ተካፍለዉ ሲመለሱ  በታጠቁ ሀይሎች  መገደላቸዉን ተከትሎም በአካባቢዉ  ከፍተኛ ዉጥረት ሰፍኖ ቆይቷል። በግጭቱም  ለአካባቢዉ« መጤ» ናችሁ በተባሉ የተለያዩ ብሄር አባላት ላይ በተፈፀመ ጥቃት ከ40 በላይ ንጹሃን ዜጎች ሲገደሉ፤ 70 ሺህ  የሚጠጉ ዜጎች ጥቃቱን በመሸሽ  ከቀያቸዉ መፈናቀላቸዉን በተለያዩ አካላት ዘንድ ሲገለፅ ቆፕቷል። የኢትዮጵያ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን በዛሬዉ ዕለት እንዳስታወቀዉ ደግሞ የተፈናቃዮቹ ቁጥር ከ90 ሺህ በላይ ደርሷል።የኮሚሽኑ የህዝብ ግንኑነትና የኮሚንኬሽን ሀላፊ አቶ ደበበ ዘዉዴ ከኦሮሚያ ክልል ደረሰኝ ባሉት መረጃ መሰረት የቁጥሩን ማሻቀብ እንዲህ ያብራራሉ።

«በመስከረም 16፤18 እና 22 ቀን 2018 አ/ም የደረሰኝ መረጃ የሚያመለክተዉ በአሁኑ ስዓት ከ16 ሺህ 182 እማ/አባዉራዎች ወይም ደግሞ በቁጥር 93 ሺህ 384 ወገኖች በተፈጠረዉ ግጭት ቀደም ሲል ይኖሩበት ከነበረዉ ቀዬ ተፈናቅለዋል።
ተፈናቃዮቹ በምዕራብና ምስራቅ ወለጋ አስር ወረዳዎች ዉስጥ ተጠልለዉ የሚገኙ ሲሆን በቁጥሩ መሰረትም በሁሉም ወረዳዎች የምግብና ምግብ ነክ እንዲሁም የአልባሳትና ቁሳቁስ እርዳታ መድረሱን አቶ ደበበ ገልፀዋል።
እሳቸዉ ይህን ይበሉ እንጅ በጊዚያዊ የመጠለያ ጣቢያዎች የሚገኙት እነዚህ  ተፈናቃዮች ህይወታቸዉን  ለማዳን ሀብት ንብረታቸዉን ጥለዉ በመሸሻቸዉ አሁኑ ወቅት በአንዳንድ ቦታዎች ከፍተኛ ችግር እያጋጠማቸዉ መሆኑን ነዉ የአካባቢዉ ነዋሪዎች የሚገልፁት። ያምሆኖ ግን በመንግስት በኩል እስካሁን ድጋፍ ሲደረግላቸዉ አልመመልከታቸዉን ነዉ ፤ስማቸዉ እንዲጠቀስ ያልፈለጉ በምስራቅ ወለጋ ዞን በግዴአያና ወረዳ የአድገርጉቴ ከተማ ነዋሪ ለD,W የገለፁት። ነገር ግን የአካባቢዉ ማህበረሰብ ተፈናቃዮቹን ለመርዳት ርብርብ እያደረገ መሆኑን ነዉ ነዋሪዉ ያስረዱት።
በአሁኑ ጊዜ እየተፈጠሩ ባሉ ግጭቶች የአካባቢዉ ህበረሰብ የራሱን ማህበራዊ ተቋማት ተጠቅሞ የሚያደርገዉን እርዳታና ትብብር አቶ ደበበ አድንቀዉ፤ከቦታ ርቀት አንፃር በወቅቱና በፍጥነት ላይደርስ ይችል እንደሁ እንጅ፤ መንግስትም የበኩሉን እያደረገ መሆኑን ነዉ ሀላፊዉ የገለፁት።ቀጣዩ ስራም ልክ እንደ ከዚህ በፊቶቹ ግጭቶች ተጎጅዎቹን ወደ ቀያቸዉ መመለስ ይሆናል ነዉ ያሉት። 
እንደ አቶ ደበበ ገለፃ ችግሮቹ በድንገት የተፈጠሩ በመሆናቸዉ የመንግስትን የመጠባበቂያ በጀት የሚፈትኑ ናቸዉ።ስለሆነም ተጎጅዎችን ከመደገፍ ባለፈ ወደ ቀያቸዉ ለመመለስና በዘላቂነት ለማቋቋም ህብረተሰቡና ለጋሾች ትብብር እንዲያደርጉ ጠይቀዋል። 
 መንግስት ተጎጅዎችን በምግብና ቁሳቁስ ከመደገፍና በተደጋጋሚ እየተከሰቱ ያሉ ግጭቶችን በጊዚያዊነት ከመፍታት ባሻገር ከመከሰታቸዉ በፊት ባህላዊና ሀይማኖታዊ መሰረትን ያደረጉ ስራዎችን በመስራት ህዝቡ ተቻችሎና ተከባብሮ የመኖር እሴቱን እንዲያዳብር ሊያደርግ ይገባል የሚል ትችት በአንዳንዶች ዘንድ ተደጋግሞ ይነሳል።በምስራቅ ወለጋ በግዴአያና ወረዳ ነዋሪም ይህን ሀሳብ ይጋሩታል።
በኢትዮጵያ በቅርቡ አንድ አለም አቀፍ ተቋም ባወጣዉ ዘገባ መሰረት በ2018 ዓ/ም ግጭትና ጥቃት ሸሽተዉ ዜጎቻቸዉ ከሚሰደዱባቸዉ 10 የዓለም ሀገራት ዉስጥ ኢትዮጵያ 1 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሰዎች የተፈናቀሉባት ሀገር በመሆን የመጀመሪያዉን ደረጃ መያዟን አስታዉቋል። ከትናንት ጀምሮ በሀዋሳ ከተማ እየተካሄደ ከሚገኜዉ 11 ኛዉ የኢህአዴግ ጉባኤም ይህንን ችግር የሚፈታ ዉሳኔ ብዙዎች የሚጠብቁት ይመስላል።

Äthiopien Somalia Vertriebene Menschen
ምስል DW/B. Girma
Äthiopien Somalia Vertriebene Menschen
ምስል DW/B. Girma

ሙሉ ቅንብሩን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነዉ ያድምጡ።

 

ፀሀይ ጫኔ

አዜብ ታደሰ