1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ከቤንሻንጉል የተፈናቀሉ መምህራን ቅሬታ

ሰኞ፣ ኅዳር 10 2011

ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የተፈናቀሉ የአማራ ክልል ተወላጅ መምህራን በክልሉ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ተመድበው እንዳይሰሩ የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ትምህርት ቢሮ ከለከለን ሲሉ ቅሬታቸውን አሰሙ።  

https://p.dw.com/p/38XWW
Äthiopien Amhara EducationBüro in Bahrdar
ምስል DW/A. Mekonnen

የተፈናቃይ መምህራን ቅሬታ

 በአማራ ክልል የአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ትምህርት መምሪያ ደግሞ መምህራኑ የሰለጠኑበት የትምህርት መስክ ለአማራ ክልል ህፃናት በአፍ መፍቻ ቋንቋነት አያገለግልም ሲል ራሱን ተከላክሏል፡፡ ሆኖም የሁለቱ ክልሎች ስርዓተ ትምህርት ከተገመገመና ተመሳሳይነት ካለው፣ መምህራኑ ከአንደኛ ደረጃ በላይ ባሉ ትምህርት ቤቶች የሚመደቡበት ሁኔታ ሊኖር ይችላል ብሏል፡፡
አስተያየታቸውን ለDW የሰጡ መምህራን እንደገለፁት ለመምህርነት የሚያበቃቸውን ስልጠና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ግልገል በለስ በተባለ የመምህራን ማሰልጠኛ ተቋም ወስደውና ተመርቀው በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በተለያዩ ትምህርት ቤቶች ተቀጥረው ሲያስተምሩ ቆይተዋል፡፡ ይሁን እንጂ በተለያዩ ጊዚያት በክልሉ በተፈጠሩ ግጭቶች ምክንያት የክልል ተወላጅ አይደላችሁም ተብለው ከየነበሩበት ወደ አማራ ተፈናቅለዋል፡፡
መምህራኑ እንደሚሉት እድሉን አግኝተን በግልገል በለስ ተምረን በአካባቢው ስራ መያዝ ብንችልም የክልሉ ተወላጆች አይደላችሁም በሚል ተባርረናል፤ እናም የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ትምህርት ቢሮ እንደ ክልል ተወላጅነታችን ተቀብሎ በክልሉ በሚኙ ትምህርት ቤቶች ሊመድበን ይገባል ይላሉ
የአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ትምህርት መምሪያ አቶ ዓለሙ ክህነት ጉዳን አስመልክተው በሰጡት ምላሽ መምህራኑ የሰለጠኑት በእንግሊዝኛ ቋንቋ በመሆኑ ይህ ደግሞ ለአማራ ክልል ህፃናት በአፍ መፍቻነት ሊያገለግል ባለመቻሉ መምህራኑን ተቀብሎ ለማስተናገድ አስቸጋሪ ብለዋል፡፡
ሆኖም የሁለቱ ክልሎች ስርዓተ ትምህርት ከተገመገመና ተመሳሳይነት ካለው፣ መምህራኑ ከአንደኛ ደረጃ በላይ ባሉ ትምህርት ቤቶች የሚመደቡበት ሁኔታ ሊኖር እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡
የአማራ ክልልትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ይልቃል ከፍአለም ቢሆን መምህራኑ በአማራ ክልል በአፍ መፍቻ ቋንቋ ለማስተማር በአማራ ክልል ከሚነገሩ ቋንቋዎች ቢያንስ በአንዱ መሰልጠን እንዳለባቸው አመልክተዋል፡፡
ከቅርብ ጊዚያት ወዲህ በተለያዩ አካባቢዎች ከሚነሱ ግጭቶች ጋር በተያያዘ በማንነታቸው ከክልል ወደ ክልል ተፈናቅለው በካምፖች በድንኳኖችና በተለያዩ መጠለያዎች በችግር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ቁጥር በርካታ ነው፡፡


ዓለምነው መኮንን 

አርያም ተክሌ

ማንተጋፍቶት ስለሺ