1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

እኛም የለዉጡ ተሳታፊዎች መሆን አለብን

ማክሰኞ፣ ኅዳር 25 2011

በኢትዮጵያ በተጀመረዉ የለዉጥ ጎዳና እኛም ድርሻችን እንድናበረከት እና የለዉጡ አካል እንድንሆን ትኩረት ሊሰጠን ይገባል ሲሉ በኢትዮጵያ የአካል ጉዳተኛ ተወካዮች ገለፁ። ይህ ጥሪ የመጣዉ ትናንት በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ 27ኛ ጊዜ ታስቦ የዋለዉን ዓለም አቀፍ የአካል ጉዳተኞች ቀንን ተከትሎ ነዉ።

https://p.dw.com/p/39S2B
Äthiopien - Internationaler Tag der Menschen mit Behinderung 2018
ምስል Abayeneh Goju

የአካል ጉዳተኞች ጉዳይ ከማኅበረሰቡ ሊነጠል አይገባዉም

ቀኑ በኢትዮጵያ ለ 26 ኛ ጊዜ ታስቦ የዋለ ሲሆን ለመጀመርያ በደቡብ ክልል፤ ሃዋሳ ላይ ከፍተኛ ባለሥልጣናት በተጋበዙበት በደማቅ ሥርዓት መከበሩን በኢትዮጵያ የአካል ጉዳተኞች ብሔራዊ ማኅበራት ፌደሬሽን ለ«DW»ገልፀዋል።

የዘንድሮዉ በዓለም አቀፍ ደረጃ ታስቦ የዋለዉም የአካል ጉዳተኞች ቀን መርህ «አካል ጉዳተኞችን በማብቃት አካታችነትን እና እኩልነትን እናረጋግጥ» የሚል ነዉ። በዝግጅቱ ላይ ተካፋይ የነበሩት «ላይት ት ፎር ዘወርልድ» በተሰኘ ዓለም አቀፍ የአካል ጉዳተኞች ድርጅት የበላይ አማካሪ ሆነዉ የሚያገለግሉት ወ/ሮ የትነበርሽ ንጉሤ ዝግጅቱ እጅግ ጥሩ እንደነበር ተናግረዋል። 

«ትናንት አዋሳ ላይ የደቡብ ክልል መስተዳድር ነዉ ይህን በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚከበርን ቀን ያሰናዳልን። በሚቀጥለዉ ዓመት ይህ ቀን ኦሮሚያ ላይ እንዲከበር ስምምነት ላይ ተሰድርሶ ከደቡብ ክልል ኃላፊነቱን ኦሮምያ ተቀብሎ ትናንት በጣም ደማቅ በሆነ ሁኔታ የደቡ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዲሁም የሠራተኛ እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትሯ  ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ በተገኙበት በጣም በጥሩ ሁኔታ ተከብሮአል።»    

Logo l Äthiopien - Föderation  nationaler Vereinigungen der Menschen mit Behinderungen in Äthiopien

እንዲያም ሆኖ የአካል ጉዳተኞች ጉዳይ ከማኅበረሰቡ ጋር በጋራ መነሳት ያለበት እንጂ ሊነጠል አይገባዉም ሲሉ የተናገሩት የአካል ጉዳተኞች ከፍተኛ አማካሪ የትነበርሽ ንጉሤ በኢትዮጵያ በኤኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ዘርፎች ተደረጉ በተባሉ መሻሻሎች አልያም ለዉጦች የአካል ጉዳተኞች ምን ያህል ተካተዋል፤ ምን ያህልስ ተጠቃሚ ናቸዉ ብለን መንግሥትን ልንጠይቅ ይገባል ብለዋል። 

«እንግዲህ እስካሁን ባለኝ መረጃ አዲሱ የኢትዮጵያ አመራር የተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ለማነጋገር ሞክሮአል። ምን ያህል የአካል ጉዳተኞችን እንዳሰበ አላዉቅም። በአንድ ወቅት ጉዳዩ ተነስቶ እንደነበር አዉቃለሁ። ግን ከዝያ በኋላ ቅድምያ የሚሰጣቸዉ ነገሮች መጡ እና ቀረ። የሚያዋጣዉ የአካል ጉዳተኞችን ጉዳይ ልክ እንደ አንድ ዝርዝር በያዘ ካርድ ላይ እንደ አንድ ምርጫ አድርጎ ከመዉሰድ በየአንዳንዱ ሂደት ዉስጥ አካል ጉዳተኞች መካተታቸዉን ማረጋገጥ ያስፈልጋል። ያንን የሚያረጋግጥ ቁርጠኝነት ያስፈልጋል። ስለዚህ በወጣቶች ዙርያ በኪነ-ጥበብ ሰዎች ዙርያ ሲወሰድ ለምሳሌ በኪነ-ጥበብ ዙርያ ያሉ ችግሮችን አልያም አስተዋፆኦችን ስናይ አካል ጉዳተኛ የኪነ-ጥበብ ሰዎችን በዚያ ማካተት ይኖርብናል።»     

በኢትዮጵያ 18 ሚሊዮን የአካል ጉዳተኞች እንዳሉ ይገመታል፤ እንዲያም ሆኖ ምንም የተጣራ መረጃ እስካሁን የለንም ያሉት፤ በኢትዮጵያ የአካል ጉዳተኞች ብሔራዊ ማኅበራት ፌደሬሽን ዋና ዳይሬክተር አቶ አባይነህ ጉጆ ፤ አካል ጉዳተኞች በሀገራችን የለዉጡ አካል ናቸዉ ብለን የምንወስደዉ ነገር የለም ባይ ናቸው።  

እንደ አጠቃላይ የአካል ጉዳተኞች በለዉጡ ሂደት ባለቤቶች ናቸዉ፤ የለዉጡ አካላት ናቸዉ፤ ብለን በአሁኑ ሰዓት የምንወስደዉ የተጨበጠ ነገር የለም። የለዉጡ አካል እንዲሆኑ ግን መሰራት ያለባቸዉ ነገሮች እንዳሉ፤ እየተነገረ ነዉ። ነገር ግን ብዙም የተሰራ ነገር የለም። በተለይ መንግሥት ቱክረት ሰጥቶ ፤ ለምሳሌ በኢትዮጵያ ዉስጥ ከ 18 ሚሊዮን አካል ጉዳተኛ አለ ተብሎ ይገመታል፤ እና ይህን የአካል ጉዳተኛ ያሳተፈ የለዉጥ ጎዳና ነዉ መጀመር ያለበት። ለዉጥ ስንጀምር ሁሉን ያካተተ ለዉጥ እንጂ እንደገና የአካል ጉዳተኞችን ለብቻ የያዘ ለዉጥ መሰራት የለበትም፤ የሚል እምነት ነዉ ያለን።»    

Äthiopien Gewinnerin des alternativen Nobelpreises, Yetnebersh Nigussie
ምስል privat

ገና ማለዳ ላይ በሚገኘዉ በኢትዮጵያ በሚታየዉ የለዉጥ እንቅስቃሴ የአካል ጉዳተኞችን ለማካተት መልካም ፈቃድ እንዳለ ቢታይም የአካል ጉዳተኞችን ሁኔታ ለማወቅ እና ከኅብረተሰቡ ጋር እኩል ተጠቃሚዎች እንዲሆኑ፤ ከኪነ-ጥበቡ ማኅበረሰብ እንዲሁም ከጋዜጠኞች ጋር ዉይይት እንደተደረገ ሁሉ አካል ጉዳተኞቹን በቀጥታ መጠየቅ እንደሚያስፈልግ ወ/ሮ የትነበርሽ ተናግረዋል።      

« አሁንም መንግሥት እየሄደበት ያለዉ አካሄድ በበጎ ፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ ነዉ፤ አካል ጉዳተኞች ምንጉዳይ አላችሁ ተብሎ እንኳን በጠቅላይ ሚኒስትሩ ፤ በሠራተኛ እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ደረጃ እንኳ ምክክር ሲደረግ አላዉቅም። በዚህም ተጨባጭ የሆኑ ርምጃዎችን መንግሥት መዉሰድ ይኖርበታል። በኢትዮጵያ ሕዝብ፤ በኢትዮጵያ መንግሥት የሚሰራ ማንኛዉም ነገር፤ ሁሉንም ማኅበረሰብ እንዲያካትት ጠንካራ የሕግ እና የአስተዳደር ማዕቀፍ ማካተት የሚያስፈልግ ይመስለኛል። እኛ የተለየ ትምህርት ቤት ሳይሆን የሚያስፈልገን፤ ያለዉን ትምህርት ቤት ለአካል ጉዳተኞች ምቹ የሚያደርግ መንግሥት ነዉ የሚያስፈልገን ።»  በዚህም ብለዋል ያነጋገርናቸዉ የአካል ጉዳተኛ ኢትዮጵያዉያን ተወካዮች፤ መንግሥት አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ ያረገ በቂ ሥራ እስካልሰራ ድረስ ትች ማቅረባችንን እንቀጥላለን።

 

አዜብ ታደሰ

ሸዋዬ ለገሠ