1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

እስራኤል ቀሪ ኢትዮጵያዊ ይሁዲዎችን ማጓጓዝ ጀመረች

ሐሙስ፣ ሰኔ 1 2009

ተቋርጦ የነበረዉ ኢትዮጵያዊ ይሁዲወችን ወደ እስራኤል የማጓጓዝ ስራ ወይም «አሊያህ» እንደገና ተጀመረ።የጉዞዉ መጀመር በሀገሪቱ የሚገኙና  ለበርካታ አመታት ከቤተሰቦቻቸዉ  ተለያይተዉ ለቆዩ ኢትዮጵያዊ  ይሁዲወች ደስታ ፈጥሯል።

https://p.dw.com/p/2eMCb
Bete Israelis in Gondar
ምስል DW/G. Tedla

Ethiopian Immigrants arrive in Israel - MP3-Stereo


በጎርጎሮሳዊዉ የዘመን ቀመር ከ2013  አንስቶ የእስራኤል የሀገር ዉስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር በኢትዮጵያ የሚገኙ ከ 9 ሺህ በላይ ቀሪ የኢትዮጵያ የቤተ እስራኤል አባላትን ለማጓጓዝ እቅድ መያዙን  ሲገልጽ ቆይቷል።ይህ እቅድ ከ2 ዓመታት ቆይታ በሁዋላ በ2015 በሀገሪቱ ምክር ቤት የፀደቀ ቢሆንም የበጀት እጥረት አጋጥሟል በሚል ሳቢያ የማህበረሰቡ አባላት ወደ እስራኤል የሚያደርጉት ጉዞ በታቀደዉ መሠረት ሳይከናወን ቆይቶ ነበር።
የተለያዩ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶችና ግለሰቦች እንዲሁም በሀገሪቱ የሚገኙ የኢትዮጵያ ቤተ እስራኤሎች በተለያዩ ጊዜያት የጉዞውን መዘግየት ሲቃወሙ ቆይተዋል።  
ተቃዉሞዉን ተከትሎ የሀገሪቱ መንግስት በየ ወሩ 100 ኢትዮጵያዊ መሰረት ያላቸዉን ቤተ እስራኤላዉያን  ለማጓጓዝ የሚያስችል በጀት ለማፈላለግ  በጎርጎሮሳዊዉ ሚያዚያ  2016 አ/ም ስምምነት ፈርሟል።በተያዘዉ አመትም በሺህ የሚቆጠሩ ሰወች ይገባሉ ተብሎ በጀት መያዙንም  ለማህበረሰቡ አባላት መብት የሚታገለዉና « ጠበቃ» የተባለዉ  ድርጅት ስራ አስኪያጅ አቶ ፋንታሁን አሰፋ  ለዶቼ ቬለ ገልጸዋል።

በዚህም መሰረት ከ7 ወራት ወዲህ የመጀመሪያ ናቸዉ የተባሉ ከ70 በላይ የሚሆኑ የማህበረሰቡ አባላት በዚህ ሳምንት ማክሰኞ ምሽት እስራኤል መግባታቸዉን የተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።  የተነጣጠሉ ኢትዮጵያዊ ይሁዲ ቤተሰቦች እንዲገኛኑ ሲታገሉ መቆየታቸዉን የገለጹት አቶ ፋንታሁን  ለበርካታ አመታት የተለያዩ ቤተሰቦች መገናኘታቸዉ አስደስቷቸዋል።
በአሁኑ ጎዞ   ቤተሰቦቻቸዉ ወደ እስራኤል ከመጡላቸዉ መካከል  አቶ እያዩ ወርቁ አንዱ ናቸዉ።እሳቸዉ እንደሚሉት ቀደም ሲል ከእህትና ወንድሞቻቸዉ ጋር 7 ሆነዉ ለጉዞ ቢነሱም  ሁለቱ  እህቶቻቸዉ ግን ኢትዮጵያ ዉስጥ ቀርተው ነበር።አንዷ እህታቸዉም ጉዞ በመጠባበቅ እያለች በሞት ተለይታለች ።  ይሁን እንጅ የአሁኑ ጉዞ ከሟች እህታቸዉ ልጆች ጋር እንዲገናኙ ረድቷቸዋል።
ከ 20 አመታት በላይ በእስራኤል ሀገር እንደቆዩ የሚናገሩት አቶ ቴወድሮስ ዘዉዴ በበኩላቸዉ በቆዩባቸዉ አመታት ሁሉ ለኢትዮጵያዊ ይሁዲዎች መብት ሲታገሉ መቆየታቸዉን ገልጸዋል። አሁን የተጀመረዉ የተለያዩ  ቤተሰቦችን የማገናኘት ስራም የሚያስመሰግን ነዉ ብለዋል።
በአሁኑ ጊዜ እስራኤል ውስጥ ከ135ሺህ በላይ ኢትዮጵያዊ መሰረት ያላቸዉ ቤተእስራኤላዉያን ይገኛሉ። ከነዚህም ዉስጥ ወደ 22 ሺህ የሚጠጉት በጎርጎሮሳዊዉ 1984 እና 1991 በተካሄደዉ ዘመቻ ሙሴና ዘመቻ ሰሎሞን ወደ ሀገሪቱ የገቡ መሆናቸዉን መረጃወች ያመለክታሉ። 

Israel Festnahmen bei Demonstration äthiopischstämmiger Israelis
ምስል Reuters/B. Ratner

ፀሐይ ጫኔ

ሽዋዬ ለገሠ