1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኢትዮጵያውያን እስረኞች በኤርትራ

ሐሙስ፣ ሐምሌ 12 2010

የቤተሰቦቻቸው አባላት ኤርትራ እሥርቤት ውስጥ ይገኛሉ ብለው የሚገምቱት ኢትዮጵያውያን፣ መንግሥት በሌሎች አገራት እንዳደረገው እነዚህን ዜጎች አስፈትቶ ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ እንዲያደርግ ጠይቀዋል። ተቃዋሚው አረና ትግራይም በኤርትራ እሥር ቤቶች ይገኛሉ የተባሉ ኢትዮጵያውያን ጉዳይ መፍትሄ እንዲፈለግለት ጥረቱን እንደሚቀጥል ተናግሯል። 

https://p.dw.com/p/31mQt
Grenzkonflikt Eritrea Äthiopien Soldaten Eritrea
ምስል AP

ኢትዮጵያውያን እሥረኞች በኤርትራ

የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ጦርነት ሲጀመር እና ከዚያም በኋላ ኤርትራ ውስጥ የነበሩ እና እስካሁን ያሉበት የማይታወቅ ኢትዮጵያውያን ጉዳይ ችላ ተብሏል ሲሉ ቤተሰቦቻቸው ቅሬታቸውን ገለጹ። ዶቼቬለ ያነጋገራቸው፣ የቤተሰቦቻቸው አባላት ኤርትራ እሥርቤት ውስጥ ይገኛሉ ብለው የሚገምቱት እነዚሁ ኢትዮጵያውያን፣ መንግሥት በሌሎች አገራት እንዳደረገው እነዚህን ዜጎች አስፈትቶ ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ እንዲያደርግ ጠይቀዋል። ተቃዋሚው አረና ትግራይም በኤርትራ እሥር ቤቶች ይገኛሉ የተባሉ ኢትዮጵያውያን ጉዳይ መፍትሄ እንዲፈለግለት ጥረቱን እንደሚቀጥል ተናግሯል። 

ፈጣን ዛሬ የ44 ዓመት ጎልማሳ ነው። አድዋ ነው የተወለደው። ከአባቱ ከተለየ 20 ዓመታት ተቆጥረዋል። ከ20 ዓመት በፊት ኤርትራ እየተመላለሱ ይነግዱ የነበሩት አባቱ የኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ሲጀመር አስመራ ነበሩ። ያኔ ከኤርትራ ወደ ወደ ሀገራቸው ኢትዮጵያ ለመመለስ የተለያየ ሙከራ ቢያደርጉም መንገዱ ሁሉ በመዘጋጋቱ አልቻሉም። ከአንድ ዓመት በኋላ አንድ ቀን ግን ከቤታቸው እንደወጡ ሳይመለሱ መቅረታቸውን ፈጣን ይናገራል።
« ምሳ በልቶ እንደወጣ በዛው ነው የቀረው ብስክሌት ነበረው። ብስክሌቱ መንገድ ላይ ወድቃ ተገኘች። እን በአጋጣሚ ለጓደኛው ደወልኩለት ታስሯል አለኝ። የአባቴ ልጅ እህቴ እዛ አለች ምንም ወሬ የላትም።»
እንደ ፈጣን ሁሉ አቶ አብደላም የአጎታቸው ልጅ የት እንዳሉ አያውቁም ስለርሳቸው ከሰሙ  20 ዓመት አልፏል። የአቶ አብደላ የአጎት ልጅ አስመራ ውስጥ በንግድ ስራ ነበር የሚተዳደሩት። የአክሱም ተወላጅ የሆኑት እኚሁ ሰው የዛሬ 30 ዓመት ነበር ኤርትራ ሄደው እዚያው መኖር የጀመሩት። አቶ አብደላ እንደሚሉት ፣ የአጎታቸው ልጅ  እንደ ፈጣን አባት ከቤታቸው ወጥተው አልተመለሱም።
«90 ዓመተ ምህረት «ሰኞ ባድመ»አዋጅ እንደታወጀ ከቤት ወደ ሱቅ ሊሄድ እንደወጣ ተጠልፎ ነው የቀረው ባለቤቱ እና ልጆቹ ሲከታተሉ እና ሲጠይቁ የትም ሊያገኙት አልቻሉም። ከዜርትራ የሚመጡ አንዳንድ ሰዎችን ስንጠይቅ አለ ይባላል። ግን ወሬ ነው። »
እንደ ፈጣን አባት እና እንደ አቶ አብደላ የአጎት ልጅ ኤርትራ ውስጥ የት እንዳሉ ፣ ይሙቱ ይኑሩም የማይታወቅ ኢትዮጵያውያን በሺህዎች የሚቆጠሩ እንደሆነ ነው የሚነገረው። ቤተሰቦቻቸው በተለያዩ እስር ቤቶች ውስጥ ይገኛሉ ብለው ይገምታሉ። የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ አስመራን ጎብኝተው ሲመለሱ እነዚህን ዜጎችን ይዘው ይመለሳሉ ብለው አስበው እንደነበርም ይናገራሉ። ይህን ተስፋ ካደረጉት መካከል ፈጣን ይገኝበታል። 
«እኛ ተስፋ ነበረን በዶክተር ዐብይ ሳዑዲም ግብጽም ሱዳንም ሄደው ዜጎቻችንን አስፈትተው ሲመጡ እንደምናነበው እንደምንሰማው ጦርነት ላይ የነበሩ ሀገራት እሥረኛ ይለዋወጣሉ፣ምርኮና ይለዋወጣሉ፤እንዲህ አልተደረገም። እኔ ይህን ከዶክተር ዐብይ አልጠበቅኩም።»
ኤርትራ ውስጥ የት እንደደረሱ የማይታወቅ ኢትዮጵያውያንን ጉዳይ በየጊዜው እንደሚያነሳ  የገለጸው ተቃዋሚው አረና ትግራይም ይህንኑ ጠብቆ እንደነበር ነው የፓርቲው የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ አምዶም ገብረ ሥላሴ ለዶቼቬለ የተናገሩት። 
«ከኤርትራ በርካታ ኢትዮጵያውያን የታሰሩ እንዳሉ የተለያዩ መረጃዎች ይደርሱናል። ባለፈው ዶክተር ዐብይ እንደሄዱ ይፈታሉ ብለን ተስፋ አድርገን ነበር። እስካሁን የተፈታ ኢትዮጵያዊ የለም። ሲቪልም ይሁን በውትድርና የተማረኩም ይሁኑ በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ከድንበር አካባቢ የተወሰዱ በሺህዎች የሚቆጠሩ ዜጎች አሉ። እነርሱ እስካሁን አልተፈቱም እና እንደሚፈቱም ተስፋ እናደርጋለን። ካልተፈቱ ደግሞ ጥረት እናደርጋለን ማለት ነው።»
አቶ አምዶም ፓርቲያቸው አግኝቷል ባሉት መረጃ   የት እንዳሉ የማይታወቁ የታሰሩ እንዲሁም የሞቱም ኢትዮጵያውያን መኖራቸውን ገልጸዋል።ፓርቲያቸው ከጦርነቱ በፊት ኤርትራ ውስጥ ይኖሩ የነበሩ እና ከድንበር አካባቢም ታፍነው ተወስደዋል የሚባሉ ኢትዮጵያውያን የሚገኙበትን ሁኔታ የማጣራት ሙከራ አድርጎ እንደነበርም ተናግረዋል ። 
«እኛ በዝርዝር በዘመቻ መልኩም ጥረት አድርገን ነበር። በተለይ ከባድመ ፣ከኤሮብ፣ ከዛላ አንበሳ አካባቢ ያኔ የተወሰዱ እና ሌሎችም እንዲፈቱ እና ህልውናቸውም እንዲጣራ ከቀይ መስቀልም ተባብረን ለማጣራት ሙከራ አድርገን ነበር። እስካሁን አዎንታዊ ምላሽ አልተገኘም።»
ፈጣን እና አቶ አብደላ መንግሥት ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶ የጠፉት ቤተሰቦቻቸው እና ሌሎችም ኢትዮጵያውያን በምን ሁኔታ ላይ እንዳሉ እንዲያጣራላቸው ይጠይቃሉ የአረናም ጥሪም ተመሳሳይ ነው። ዶቼቬለ ስለ ጉዳዩ የኢትዮጵያ መንግሥትንም ሆነ የኤርትራን መንግሥት መልስ ለማግኘት ተደጋጋሚ ጥረቶች አድርጎ ነበር። ሆኖም፣ የሚመለከታቸውን ባለስልጣናት ማግኘት አልቻልንም። 

Grenzkonflikt Eritrea Äthiopien Soldaten Eritrea
ምስል AP
Eritrea Soldaten auf dem Weg zur Front
ምስል picture-alliance/dpa/S. Forrest

ኂሩት መለሰ

አዜብ ታደሰ