1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኢትዮጵያ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቶቿን ቁጥር ልትቀንስ ነው

ሐሙስ፣ ጥቅምት 1 2011

የኢትዮጵያ መንግሥት የካቢኔ አባላትን ቁጥር ከ28 ወደ 20 ዝቅ የሚያደርግ ረቂቅ ሕግ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መላኩን አስታውቋል። ጠቅላይ ምኒስትር አብይ አሕመድ "ምኒስትሮቹንም ቀነስ፣ ተቋሞቻችንን ቀነስ" ለማድረግ የተገደዱት በወጪ ሳቢያ መሆኑን ጠቁመዋል። በረቂቅ ሕጉ መሠረት የሚዋሐዱ እና አዲስ የሚቋቋሙም ይኖራሉ።

https://p.dw.com/p/36KvO
Äthiopien Abiy Ahmed Premierminister
ምስል picture-alliance/AP Photo/Saudi Press Agency

የኢትዮጵያ ሚኒስትሮች ምክር ቤት የአገሪቱን ሥራ አስፈፃሚ አወቃቀር ለመከለስ የቀረበውን ረቂቅ ሕግ አፅድቆ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መላኩን የጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት ኃላፊው አቶ ፍጹም አረጋ አስታውቀዋል። 

አቶ ፍጹም እንዳሉት በረቂቅ ሕጉ መሠረት የካቢኔ አባላት ቁጥር ከ28 ወደ 20 ዝቅ ይላል። አሁን ካሉት መሥሪያ ቤቶች መካከል የሚቀላቀሉ መኖራቸውን ያስታወቁት አቶ ፍጹም አዲስ የሚዋቀሩ መኖራቸውንም ጠቁመዋል። 

በሚኒስትሮች ምክር ቤት ውሳኔ መሠረት አቶ መላኩ አለበል የሚመሩት የንግድ ሚኒስቴር እና አቶ አምባቸው መኮንን (ዶ/ር) የሚመሩት የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ተዋሕደው የንግድ እና የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የተባለ ተቋም ይቋቋማል። 

አቶ ጌታሁን መኩሪያ (ዶ/ር) የሚመሩት የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር እና ወይዘሮ ኡባሕ መሐመድ የሚመሩት የመገናኛ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ከሚዋሐዱት መካከል ይገኙበታል። የሁለቱ ተቋማት የተናጠል ህልውና ሲያከትም የኢኖቬሽን እና የቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ይቋቋማል።

በአቶ ጃንጥራር አባይ የሚመራው የከተማ ልማት እና ቤቶች ሚኒስቴር እና ወይዘሮ አይሻ መሐመድ የሚመሩት የኮንስትራክሽን ሚኒስቴር አሁን ባላቸው ሕልውና አይቀጥሉም። በምትኩ የከተማ ልማት እና የኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ተብለው አንድ ተቋም ይሆናሉ። አቶ ፍጹም አረጋ  "ሌሎች ተጠሪ ተቋማትም በተመሳሳይ ሁኔታ እንዲዋሃዱ ውሳኔ እየተሰጠባቸው ይገኛሉ" ብለዋል። 

አቶ ፍጹም የሰላም ሚኒስቴር የተባለ ተቋም እንዲቋቋም መወሰኑንም ገልጸዋል። ተቋሙ "በአገር ውስጥ ሰላም እና የሕግ የበላይነት እንዲሰፍን በሕዝቡ ፈቃድ ላይ የተመሰረተ አንድ የፖለቲካ ማህበረሰብ በጋራ መገንባት ላይ ትኩረት ሰጥቶ የሚሰራ" እንደሆነ ገልጸዋል። 

አሁን ትምህርት ሚኒስቴር በመባል የሚታወቀው ተቋም በአገሪቱ የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎችን፣ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚንስቴር ስር የሚገኙት ሁለቱን ዩኒቨርሲቲዎች በመጨመር "የከፍተኛ ትምህርትና የሳይንስ ሚንስቴር" ተብሎ እንዲደራጅ ውሳኔ ተላልፏል።

በምኒስትሮች ምክር ቤት ውሳኔ መሠረት የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ወደ ሁለት ይሰነጠቃል። አቶ ፍጹም እንዳሉት አዲስ የሚቋቋሙት "የገቢዎች ሚኒስቴር እና ለሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ተጠሪ የሆነ የጉምሩክ ኮሚሽን" ናቸው። 

በውሳኔው መሠረት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተላከው ረቂቅ ሕግ ከጸደቀ አሁን የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ሚንስቴር ተብሎ የሚጠራው እና በአምባሳደር ተሾመ ቶጋ የሚመራው ተቋም ሕልውና ያበቃል። በምትኩ "የመንግስት የልማት ድርጅቶችን ለማስተዳደር መሰረታዊ ሚናቸው ንግድ የሆኑትን በመለየት የመንግስትን የባለቤትነት ሚና በተገቢው ሁኔታ የሚያስተዳደር “የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ኤጀንሲ” በገንዘብ ሚኒስቴር ሥር እንዲቋቋም" መወሰኑን አቶ ፍጹም አረጋ በፌስቡክ ገፃቸው ባሰፈሩት መረጃ ጠቁመዋል። 

መንግሥታቸው የሚኒስትሮቹን እና የተቋሞቹን ቁጥር ለመቀነስ ውሳኔ ላይ መድረሱን ጠቅላይ ምኒስትር አብይ አሕመድ አረጋግጠዋል። በአዲስ አበባ ከተማ ዙሪያ ጥበቃ ላይ ከነበሩ ባለ ቀይ ቆብ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ጋር ውይይት ካደረጉ በኋላ በሰጡት መግለጫ መንግሥታቸው የአስፈፃሚ አካላትን እና ተቋማትን ቁጥር ለመቀነስ የወሰነው በወጪ ምክንያት መሆኑን ጠቆም አድርገው አልፈዋል። ጠቅላይ ምኒስትሩ "ምኒስትሮቹንም ቀነስ፣ ተቋሞቻችንን ቀነስ የምናደርግበት ምክንያት ወጪ እንቀንስ፤ አብዛኛውን ነገር ልማት ላይ እናውል" በሚል መሆኑን አስረድተዋል። 

የመንግሥት መዋቅሩን የመከለሱ ጉዳይ ጠቅላይ ምኒስትር አብይ አሕመድ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ በአለፍ አገደም የሚነሳ ጉዳይ የነበረ ቢሆንም በይፋ ያረጋገጡት ግን ፕሬዝዳንት ሙላቱ ተሾመ ናቸው። የኢትዮጵያ መንግሥት በ2011 ዓ.ም. "በዜጎች ተዓማኒነት ያላቸው ተቋማት እንዲኖሩና ያሉትም እንዲጠናከሩ" ይሰራል ያሉት ፕሬዝዳንቱ የፌደራል አስፈጻሚ አካላት አወቃቀር ማሻሻያ አንዱ መሆኑን ባለፈው ሰኞ ተናግረው ነበር። 

የሕዝብ ተወካዮች እና የፌደሬሽን ምክር ቤት 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን የጋራ ስብሰባ የመክፈቻ ሥነ-ስርዓት ላይ ንግግር ያደረጉት ፕሬዝዳንት ሙላቱ "መንግስታዊ ተቋማት ግልጽ ዓላማ ያላቸው፣ በቅንጅት የሚሰሩ፣ ውጤታማና ወጪ ቆጣቢ እንዲሆኑ ለማድረግ የፌዴራል መንግስት መስሪያ ቤቶችን በጥልቀት በማጥናት ተገቢውን ማሻሻያ በማድረግ ረቂቅ አዋጅ አዘጋጅቶ" መጠናቀቁን ገልጸው ነበር። 

እሸቴ በቀለ
አርያም ተክሌ