1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አፍሪቃ ለተመላሾችዋ-የካሜሩን አብነት

ነጋሽ መሐመድ
ሰኞ፣ ሐምሌ 3 2009

በልጅነት ወይም በወጣትነታቸዉ ከየትዉልድ ሐገራቸዉ የተሰደዱ ብዙዎቹ አፍሪቃዉያን ወደየትዉልድ ሐገራቸዉ መመለስ አይፈልጉም።የተቀሩት መመለስ እየፈለጉ ነገሮች አልሟላ እያላቸዉ ይቀራሉ።ደፍረዉ የተመለሱት ደግሞ ለገዛ ወገናቸዉ አስተሳሰብ፤አኗኗርና አሰራር እንግዳ ሆነዉ ግራ ይጋባሉ።

https://p.dw.com/p/2gIQ6
Deutschland Beschäftigungstherapie für afrikanische Frauen
ምስል DW/A. B. Jalloh

 

እዚሕ ጀርመን የሚኖሩት ካሜሩናዊቷ ወይዘሮ ሚሪንዳ ኦቦን አፍሪቃዉያን ተመላሾችን ይጠቅማል ያሉትን መርሐ-ግብር ጀምረዋል። እስካሁን ያመጡት ተጨባጭ ዉጤት ግን የለም።

ኪሊያን ማዩዋ ወጣትነትን እየተሰናበተ ጎልማሳነትን በመቀበል ላይ የሚገኝ የካሜሩን ተወላጅ ነዉ።ከሐገሩ ከተሰደደ ቆይቷል።ሩቅ ግን አልሔደም።እዚያዉ ጎረቤት ነዉ-ሻገር ያለዉ።ናጄሪያ።በስደት ዘመኑ የኮምፒዉተር ሙያ ወይም IT ተማረ።በዚሁ ሙያ ሠራም።እዉቀቱ-በሠል፤ ጥሪቱ ጠርቀም ሲል ሐገሩ ገባ።

«ከጓደኛዬ ጋር ሆነን በ750 ሺሕ ፍራንክ የኮምፑተር አገልግሎት የሚሰጥ ድርጅት ከፈትን» ይላል ማዩዋ።«ብዙ ደንበኞች አገኘንም።» ቀጠለ።

Deutschland Beschäftigungstherapie für afrikanische Frauen
ምስል DW/A. B. Jalloh

«ለሥምንት ወራት ያክል ሠራን።ደንበኞቻችን ግን እናንተ ገና ወጣት ሥለሆናችሁ በአስር ሚሊዮን የሚቆጠር ፍራንክ አይገባችሁም አሉን።ለማግባባት ብዙ ሞከርን።አልሙንም።ከሰስናቸዉ።የሚገርመዉ ፍርድ ቤቱ እስካሁን ድረስ በጉዳዩ ላይ አልወሰነም።የቀረኝ ብቸኛ አማራጭ ኪሳራዬን እያሰላሁ፤ ለዳግም ስደት ሻንጣዩን መሸከፍ ብቻ ነበር።»

ማዩዋ አንዱ እንጂ ብቸኛዉ አይደለም።ወይዘሮ ኦቤን እንደሚሉት ጉቦ፤ሙስና፤ማጭበርበር እና ቢሮክራሲ አፍሪቃ ዉስጥ አለቅጥ ተንሰራፍተዋል።አፍሪቃዉያኑ ከየሐገራቸዉ ሲወጡ ልጅ ወይም ወጣት ሥለነበሩ እንዚሕ ነገሮች ብዙ አያዉቋቸዉም።ቢያዉቋቸዉም ያሁኑን ያክል ሥላልተንሰራፉ አሁን ሲያጋችማቸዉ ይደናገራቸዋል።የአፍሪቃ መንግስታት የሚጥሉት ግብርም ተመላሾቹ ዉጪ ሐገር ያጠራቀሙትን ገንዘብና ያገኙትን ዕዉቀት በየሐገራቸዉ ሥራ ላይ እንዳያዉሉት እንቅፋት ነዉ።

«ጉቦዉ፤ሙስናዉ፤የሥጦታ ጥያቄዉ ሁሉም ነገር ተዳምሮ ወደ ሐገራቸዉ ለመመለስ ከነበራቸዉy ፍላጎት ጋር ይቃረናል።ሁሉም አሠራር ለነሱ እንግዳ ነዉ።እራሳቸዉን ከሁኔታዉ ጋር ማጣጣም ይከብዳቸዋል።ሁለተኛዉ ግብር ነዉ።የግብር ሥርዓቱ እዚሕ በጣም ከፍተኛ ነዉ።አንዳዴu ከሚያስገቡት ይበልጥባቸዋል።»

Deutschland Beschäftigungstherapie für afrikanische Frauen
ምስል DW/A. B. Jalloh

ወይዘሮ ኦቦን የመሠረቱት ድርጅት አሁን ሥራዉን የጀመረዉ ለካሜሩን ተመላሾች መረጃ በመስጠት ነዉ።ሥለካሜሩን መንግስት ሕግ፤ ሥለመስሪያቤቶቹ አሠራር፤ሥለ ሕብረተሰቡ አስተሳሰብ፤ ትርፋማ ሥለሚሆኑ የሥራ መስኮች መረጃ ይሰጣል።ሥለቀናቸዉ ተመላሾች ታሪክም ያስረዳል።

«ወደ ሐገራቸዉ የሚመለሱበት ምክንያት ብዙ ነዉ።ግን ተመልሰዋል።እኔ ገና ያላደረግሁትን አንድ እርምጃ ወስደዋል።ይሕ ራሱ ግሩም ድንቅ እንድል ያደርገኛል።»

የአፍሪቃ መንግስታት ገንዘብና እዉቀት ይዘዉ ከዉጪ ለሚመለሱ ዜጎቻቸዉ ከቀረጥ ቅነሳ እስከ ልዩ ድጎማ የሚደርስ ማበረታቻ እንዲሰጡ የወይዘሮ ኦቦን ድርጅት ይመክራል።

ነጋሽ መሐመድ

ኂሩት መለሠ