1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አፄ ቴዎድሮስ 200 ኛ የልደት በዓል አከባበር

ሐሙስ፣ ጥር 9 2011

እንደ ሃገር ለማደግ አንድ መሆን አለብን። በየስርቻዉ በዘር በኃይማኖት፤ በቋንቋ እየተከፋፈለ እኔ ልግዛ የሚል ለትንንሽ ፈርኦን ገብሮ መኖር ሃገሪቱን ሊያሳድጋት አይችልም። እንደዚህ ሃገርን የሚጠብቁ መሪዎች ባይኖሩ ኖሮ ወራሪ ይገዛን ነበር። አፄ ቴዎድሮስ ታሪክ ለአሁንዋ ኢትዮጵያ ያለዉ መልክት በአንድ ስርዓት መተዳደር፤ አንድነት ነዉ።»

https://p.dw.com/p/3Bk84
Äthiopien Atse Tewodros 200. Jahrestag
ምስል DW/G. Alemenew

የታሪክ ፀሐፊዎች አፄ ቴዎድሮስን የዘመናዊት ኢትዮጵያ አባት ይሉዋቸዋል

«አፄ ቴዎድሮስን ስናነሳ ጎንደር ይወለዱ እንጂ፤ ጀግንነታቸዉ በአጠቃላይ የሰሩት ነገር ሁሉ ለሃገራቸዉ ለአንዲት ኢትዮጵያ ነዉ።  እንደሚታወቀዉ በመሳፍንት ተከፋፍላ የነበረች ኢትዮጵያን በዉድም በግድም አስገብረዉ፤ አንድ አድርገዉ፤ አሁን ያለቸዉን ኢትዮጵያን ያወረሱን አፄ ቴዎድሮስ ናቸዉ። እንደሚታወቀዉ በአሁኑ ጊዜ በተለያዩ አጋጣሚዎች ተቧድነን እየተጣላንበት ያለንበት ክፉ ወቅት ላይ ነዉ የምንገኘዉ። አፄ ቴዎድሮስ ታሪክና ዝናንን በማስታወስ ለአንድ ኢትዮጵያ አንድ በሚያደርገን ነገር ላይ አንድ ሆነን ሃገራችንን ለማሳደግ ፤ ከአፄ ቴዎድሮስ ጀግንነት ሩህሩህነት ቁርጠኝነት እና ጀግንነት ለኢትዮጵያ አንድነት ያሳዩትን ሥራ ሁላችንም መዉሰድ ነዉ የሚገባዉ።»   

Äthiopien Atse Tewodros 200. Jahrestag
ምስል DW/G. Alemenew

በጎንደር የዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ 200ኛ ዓመት የልደት ክብረ በዓልን አስመልክቶ፤ የጎንደር ባህል ማዕከል ሥራ አስኪያጅ  አቶ ወልዳረጋይ ደሌ የሰጡን አስተያየት ነበር ።  ከያዝነዉ ሳምንት ሰኞ ጀምሮ ኢትዮጵያዉያን የዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስን የ200ኛ ዓመት የልደት በዓል በተለያዩ ዝግጅቶች እያሰቡ እና እያከሩ ነዉ። በተለይ በጎንደርና አካባቢዋ ብሎም በባህር ዳር የተለያዩ የሥነ-ጽሑፍና እና የመነባንብ መድረኮችን በማዘጋጀት አስበዋል። ዛሬም ጎንደር ከተማ ላይ አንድ የግጥም እና የመነባንም ምሽት እንዳለ ሰምተናል። የጎንደር ባህል ማዕከል ሥራ አስኪያጅ  አቶ ወልዳረጋይ ደሌ፤ በከተማዋ ስለነበረዉ የአከባበር ሥነ-ስርዓት ደማቅ እንደነበር ተናግረዋል።

« ጎንደር ላይ የአፄ ቴዎድሮስ ዘንድሮ 200ኛ ዓመት የልደት ክብረ በዓል ነዉ የተከበረዉ። ለዚህም በጎንደር ከተማ በልደታቸዉ ዋዜማ ማለትም ጥር 5 ቀን ፤ የፓናል ዉይይት ነበረን፤ ተወያዮቹ ከዩናይትድ ስቴትስ ነዉ የመጡት ። አንድኛዉ ስለ አፄ ቴዎድሮስ ታሪክ የፃፉ ዶ/ር ገበየሁ ተፈሪ እንዲሁም፤ አፄ ቴዎድሮስ አራተኛ የልጅ ልጅ፤ አቶ ብዩ በለዉ ተገኝተዋል። በዚሁ ዉይይት ላይ የጎንደር ዩንቨርስቲ ተባባሪ ፕሮፊሰር ግርማ በተገኙበት ጥሩ ዝግጅት ተካሂድዋል።  አፄ ቴዎድሮስ 200ኛ ዓመት የልደት ክብረ በዓል እለት ማለትም ጥር 6 ቀን በጎንደር አፄ ቴዎድሮስ አደባባይ ፤ ፒያሳ ላይ ማለት ነዉ የሻማ ማብረት ዝግጅት ተካሂዶአል። በከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ እንዲሁም በጀግኖች አርበኛ አባቶች አማካኝነት የአበባ ጉንጉን አስቀምጠዋል። የከተማዉ ወጣት ተወካዮችም የአበባ ጉንጉን አስቀምጠዋል። በአጋጣሚ አርቲስት መሃሪ ደገፋዉ በዝግጅቱ ላይ ተገኝቶ የአበባ ጉንጉን አስቀምጦአል። ከዚህ ባሻገር ወጣቶች የ«ሴባስቶፖል መድፍ»ን የመሰለ ተሰርቶ ከጋፋት እስከ መቅደላ የተሰኘ ትርኢት መሰል ጉዞም ተደርጎአል። በዚህ ጉዞ ላይ አፄ ቴዎድሮስ  የመሰለ አልባሳት የለበሱ ተዋናዮች ጎራዴና ጋሻ ታጥቀዉ ትርኢት አሳይተዋል። ከባህርዳር የመጣዉ ማርሽ ባንድ የሙዚቃ ትርኢትም አሳይቶአል፤ ደስ የሚል ፕሮግራም ነዉ የተከበረዉ። 

Äthiopien Atse Tewodros 200. Jahrestag
ምስል DW/G. Alemenew

በጎንደር ነዋሪ የሆኑትና በከተማዉ የተለያዩ የሥነ-ግጥም እና ሥነ ጽሑፍ ዝግጅቶች ላይ ተሳታፊ የሆኑት በሪሁን አሰፋ አበበ የዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስን የ200ኛ ዓመትን በተመለከተ  እንኳንም ለንስሃ ሞት አበቃኸኝ በሚል ርዕስ ከጻፉት መነባነብ የተቀነጨበዉን አስደምጠዉናል።  በሪሁን አሰፋ አበበ በጎንደር ከተማ ከሰኞ እለት ጀምሮ ዝግጅት እንደነበር ማክሰኞ እለትም ፊደል በተባለ የዩንቨርስቲዉ የባህል ማዕከል የተለያዩ ዝግጅቶች መካሄዳቸዉን ፤ ረቡዕ ዕለትም የተለያዩ የሥነ-ጽሑፍና የታሪክ መድረኮች እንደነበሩ ተናግረዋል። የዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ የተወለዱት ጥር ጥር ስድስት ነዉ ይላሉ።

«እንደሚታወቀዉ አፄ ቴዎድሮስ የተወለዱትም የሞሩትም በቀን ስድስት ነዉ። ይህ ማለት በቁስቋም እለት ነዉ። ቀኑ ደግሞ ለጥምቀት ታካኪ የሆነ፤ ከጥምቀት በዓል ጋር ድምቀት የሚጨምር ስለሆነ ብዙ እንግዶችም በዓሉን ፈልገዉ ስለሚመጡ ፤ በአጋጣሚም ከህዝቡ ልብ ዉስጥም የነበረ ነገር ስለነበር እና ካሰብነዉ ዉጭ ነዋሪዉ አፄ ቴዎድሮስን ሴባስ ቶፖል መድፍን እያስገፋ ፤ እንደ አፄ ቴዎድሮስ ጎራዴና ጋሻዉን አድርጎና በአልባሳት ተዉቦ፤ ነዉ ተከብሮ የዋለዉ።»

በጎንደር በተከበረዉ የዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ ልደት በዓል ላይ ተሳታፊ የነበሩት ሕክምና ባለሞያዉ ዶክተር ገበየዉ ተፈሪ ፤ በሚኖሩበት በዩናይትድ ስቴትስ የተላላፊ በሽታዎች ባለሞያ ናቸዉ። ዶክተር ገበየዉ ተፈሪ መቅደላ በተሰኘ አንድ የአሜሪካዊ ጋዜጠኛ የፃፈዉን መፅሐፍ በመተርጎምና ሌሎች ታሪኮችን በማካተት  «መቅደላ የቴዮድሮስ እጣ በሚል በቅርቡ በዩናይትድ ስቴትስ ለአንባብያን አቅርበዋል። አሁን ደግሞ ይህንኑ መጽሐፋቸዉን በኢትዮጵያ እያስተዋወቁ  ነዉ ። ዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ  የተወለዱት ይላሉ ዶክተር ገበየዉ ተፈሪ፤

« አፄ ቴዎድሮስ የቋራዉ ባላባት፤ የወልደጊዮርጊስ ልጅ፤ የኃይሉ ልጅ ናቸዉ። በአባታቸዉ የንጉሳዊ ቤተሰብ ናቸዉ። እናታቸዉ ወ/ሮ አጠገብ ይባላሉ። እሳቸዉም ቢሆን አሁን በተገኘዉ መረጃ ከዳሞት ከጎንደር ባላባት የሚወለዱ ሴት ናቸዉ። አፄ ቴዎድሮስ ሲወለዱ ካሳ ነበር የሚባሉት። ሲጀምሪ በሽፍትነት በኋላ እሳቸዉ ጋር በጠቅላይ ሚኒስትርነት ያገለገልዋቸዉ እንግዳ የሚባሉ ሰዉዬ ፤ የሳቸዉ ልጅ ገሠሰች ትባላለች፤ ገሠሰች እንግዳ ወርቅን አግብተዉ ሁለት ልጆችን ወልደዋል።  ልጆቹ አልጣሽ እና መሸሻ ይባላሉ። በኋላ ግን ለፖለቲካ ሲባል ሚስትህን ፍታና የኛን ልጅ አግባ ብለዉ እቴጌ ተዋበችን አግብተዉ ነበር። እቴጌ ተዋበች የራስ አሊ ልጅ ናቸዉ። እቴጌ ተዋበች ከሞቱ በኋላ ግን ከተለያዩ ሴቶች ተጨማሪ አራት ልጆች ወልደዋል።  አንድዋ የወለዱላት የጁ ኦሮሞ ሴት ነች። ጠቅላላ ስድስት ልጆች ነበርዋቸዉ።

አፄ ቴዎድሮስ ወደ ስልጣን እንዴት ሊመጡ ቻሉ?

Äthiopien Atse Tewodros 200. Jahrestag
ምስል DW/G. Alemenew

«መጀመርያ በሕጻንነታቸዉ እንደማንም ባላባት ልጅ ወደ ገዳም እና ቤተ ክርስትያን ሄደዉ ነዉ መፃፍና ማንበብን የተማሩት ፊደል የቆጠሩት። ነብስ ሲያዉቁ ግን ታላቅ ወንድማቸዉ ከሌላ እናት የሚወለዱት ደጃችማች ክንፉ በጣም ታዋቂ ሰዉ ነበሩ፤ በምዕራብ ጠረፍ ግብፆችን ሁሉ የሚዋጉ ነበሩ፤ ክንፉ ካይሮ ድረስ እንደሚታወቁ ነበር። በክንፉ ቤት አገልግለዉ ክንፉ ሲሞቱና ልጆቻቸዉ እርስ በርስ ሲጣሉ አፄ ቴዎድሮስ ፤ ወደ ደጃች ጎሹ ቤት ሄዱ፤ ይሄን እያደረጉ እያሉ፤ ከጎንደር ቤተ-መንግሥት በመጣዉ ጭነት ምክንያት ሸፈቱ። ከዝያ ቋራ ነዉ የኖሩት። ከዝያ ነዉ ከቋራ በእርቅ ከነራስ አሊም፤ ከእቴጌ መነንም ጋር ከቀረቡ በኋላ፤ በደል ሲበዛ እንደገና ሁለተኛ ጊዜ ሸፈቱ፤ የወንድሜን ግዛት ካልሰጣችሁኝ አልገባም ብለዉ፤ ራስ አሊ ቋራን እና ደንብያን ሰጥዋቸዉ። በኋላ እንደገና እያየሉ ሲሄዱ፤ የራስ አሊ እናት እቴጌ መነን ይሄን ሰዉዬ በቅርብ ልያዘዉ ብለዉ ልጃቸዉን ዳሩላቸዉ። ልጃቸዉን ከዳሩላቸዉ በኋላ ግን ጽሑፎች እንደሚያስረዱት ቴዎድሮስን በዝያን ጊዜ ካሳ ነበር የሚባሉት፤ ካሳን ለማዋረድ ግዛታቸዉን አንድ በአንድ እየቀሙ ለሌሎች ይሰጡ ጀመር። አንዱ እንደዉም የጎጃሙ ደጃች ጎሹ ናቸዉ። »          

ዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ ስንት ዘመን ነገሱ፤ የንግሥና ዘመናቸዉስ ምን ይመስል ነበር?

« ሃገሪቱ ተከፋፍላ ለ 71 ዓመታት በመሳፍንት እጅ ስር ነበረች።  ሃገሪቱ በዉጭ ወራሪዎች ተከባ አደጋ ላይ ነበረች። አፄ ቴዎድሮስ ጠቅላላ የነገሱት ለ 14 ዓመታት ነዉ።  በንግስናቸዉ ዘመን ያደረጉት ብዙ ነገር ቢኖር፤  አንደኛ ሕዝቡ በራሱ እንዲዳኝ ምክንያቱም ቀደም ሲል ወታደሮች ነበር የሚዳኙት ። ወታደሮች ደግሞ ከሌሎች ወታደሮች ጋር እርስ በርስ እየተዋጉ ገበሪዉም ነጋዴዎችም ተበድሎ ነበር። ገበሪዉንም ነዋሪዉንም ባለህበት እርጋ አሉ። ግብር ቀነሱ። በፊት ገበሪዉ ለባላባቱ  ግብር ይከፍል ነበር ። ወታደሩ ገበሪዉን እየዘረፈ ይበላ ስለነበረ ፤ ይሄ ሊሆን አይችልም በደምወዝ የሚተዳደር ሰራዊት መኖር አለበት አሉ። ጋብቻም ገንዘብ ለሌለዉ ሁሉ እየከፈሉ ያጋቡ ነበር። ቤተክርስትያንዋ ብዙ ሃብት ንብረት ነበራት ቀሳዉስትም በየቤተክርስትያኑ ሆነዉ በገበሪዉ ጀርባ ሲኖሩ ስለነበር፤ የለም ቄስና ዲያቆኑ በየቤተክርስትያኑ ቁጥሩ አነስተኛ  መሆን አለበት ብለዉ ወሰኑ። ሌላዉ የዉጭ ጠላቶቻቸዉ እነማን እንደሆኑ ስላወቁ መሳርያ መስራት ፈልጉ። በዝያን ጊዜ ግን ቱርኮች ምፅዋን አንቀዉ ይዘዉ ምንም የሚወጣ የሚገባ ነገር አልነበረም። ለዝያም ነዉ አፄ ቴዎድሮስ የራሳቸዉን መድፍ ማሰራት የጀመሩት። እና ብዙ ደብዳቤዎችን ወደ ዉጭ ሲልኩ የእጅ አዋቂ ይምጣልኝ እኔ ቄስ አልፈልግም ። ደሞዝ እከፍላለሁ እያሉ ሃገሪቱን ማልማት ነዉ ያሰቡት፤ የፈለጉት። ሌላዉ ቢቀር ከደብረታቡር ወደ መቅደላ፤ ከደብረታቡር ጎንደር ፤ ከደብረታቡር የሚወስድ ሰገራ ሊሄድበት የሚችል መንገድ ያሰሩ ነበር። አፄ ቴዎድሮስ ደሃን ይወዱ ነበር። ድህነትን በተመለከተ ከዉጭ ሰዉ ጋር ሲነጋገሩ እኔ ራሴ ደሃን ነበርኩ። ደሃን ባልረዳ ለፈጣሪ ይነግሩብኛል እያሉ የሚያሳድጉዋቸዉ ወላጅ የሌላቸዉ ሕጻናት ነበሩ፤ እስከለተ ሞታቸዉ የሚጦርዋቸዉ አዛዉንቶችም ነበሩ። ነገር ግን ይህ ስልጣናቸዉ የተቀማባቸዉ ባላባቶች በዘር እየተደራጁ አንዳንዴም በዉጭ ጠላት እየታገዙ፤ እየሸፈቱ አደከምዋቸዉ።»      

አፄ ቴዎድሮስ ሴባስቶፖል መድፍና ሌሎች የጦር መሳርያዎችን የት ሃገር ነዉ ያሰሩት?

« አፄ ቴዎድሮስ ሴባስቶፖል መድፍን ያሰሩት እዚሁ ኢትዮጵያ ዉስጥ ጋፋት የሚባል ቦታ ነዉ። ጋፋት ላይ አንድ የብረት ማቅለጫ ነበር። ሴባስቶፖል ብለዉ የሰየሙበት ምክንያት ደግሞ በዝያን ጊዜ ቱኮች እንጊሊዞች ፈረንሳይ ሆነዉ፤ ራሽያኖችን ሲወጉ፤ራሽያኖቹ  አሁኑ ክሪምያ የሚባል ቦታ ሴባስቶፖል ከተማ ዉስጥ ሆነዉ መሽገዉ ይከላከሉ ነበር። እናም አፄ ቴዎድሮስ እንደራሽያኖቹ ነዉ ራሳቸዉን ያዩት። ይህ ሁሉ ጥቃት የመጣብን በቱርክ በእንጊሊዝ እና በፈረንሳይ ነዉ ብለዉ ነዉ ያመኑት እናም ሴባስቶፖል መድፍ ጨምሮ እዚሁ ጋፋት በሚገኙ የብረት ማቅለጫ ቦታ ነዉ የተሰሩት።  

ይህ የአፄ ቴዎድሮስ ታሪክ ለአሁንዋ ኢትዮጵያ ምን አይነት መልክት ያስተላልፋል?

Äthiopien Atse Tewodros 200. Jahrestag
ምስል DW/G. Alemenew

« ቀደም ብዩ እንደጠስኩት የአሁንዋ ኢትዮጵያ በዝያን ጊዜ  ለ 71 ዓመታት በመሳፍንት ተከፋፍላ ስትገዛ ነበር። ሸዋ ለብቻዉ ነበር። ወሎም እንደዚሁ፤ በሁለት ባላባቶች ነበር የሚገዛዉ። ጎጃም፤ በጌምድር፤ ደንብያ ተብሎ ለብቻ ተከፋፍሎ ነበር። ይህ ታድያ ለሃገሪቱ ስልጣኔ መድከም ፤ በዝያን ጊዜም የቅኝ ግዢ መስፋፋት ስለነበር፤ በዉጭ ሃይል የመወረሩና መሪት የማጣቱ እድል ከፍተኛ ነበር። አፄ ቴዎድሮስ አንድ ሁለቴ ከሸፈቱ በኋላ ሃገሪቱን አንድ ለማድረግ ቆርጠዉ ተነስተዉ፤ ሃገሪቱን አንድ በማድረጋቸዉ አሁን ያሉ የታሪክ ፀሐፊዎች የዘመናዊት ኢትዮጵያ አባት ይሉዋቸዋል። ኢትዮጵያ በዝያን ጊዜ የነበራትን ትልቅነት መልሳ አላገኘችም። እና መልክቱ እንደሃገር ለመኖር እንደ ሃገር ለማደግ እና ብልፅግናን ለማግኘት የግድ አንድ መሆን አለብን። በየጎጡ በየስርቻዉ በዘር በኃይማኖት፤ በቋንቋ እየተከፋፈልን እኔ ልግዛ በሚል ለትንንሽ ፈርኦን ገብሮ መኖር ሃገሪቱን ሊያሳድጋት አይችልም። መልክቱ እሱ ነዉ። በርግጥ አፄ ቴዎድሮስ ሃገሪቱን ያገናኙት በኃይል ነዉ። ከፍተኛ ችግርም ነበረባቸዉ። እሳቸዉ የተኩዋቸዉ አፄ ዮሃንስም ድንበር ለድንበር ሲዋጉ ቆይተዉ ነዉ ሃገሪቱን ጠብቀዉ ያቆዩት። የአፄ ምኒሊክም የምናዉቀዉ ነዉ። እንደዚህ ሃገርን የሚጠብቁ መሪዎች ባይኖሩ ኖሮ ፈረንሳይ መሪት ይወስድብን ነበር። ጣልያንም ኢትዮጵያ ላይ የነበረዉ ፍላጎት ግልፅ ነዉ። ሁለት ጊዜ ነዉ ለወረራ የመጣብን። የአፄ ቴዎድሮስ ታሪክ ለአሁንዋ ኢትዮጵያ ያለዉ መልክት በአንድ ስርዓት መተዳደር አንድነት ብቻ ነዉ።»

አዜብ ታደሰ

ተስፋለም ወልደየስ