1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በፈቃደኝነት ራሳቸው የሚያጋልጡ ከሕግ ተጠያቂነት ይድናሉ ተብሏል

ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 19 2010

የአዲስ አባባ ከተማ አስተዳደር በሃሰተኛ የትምህርት ማስረጃ የተቀጠሩና የማይገባቸውን ቦታ ይዘው ሲሰሩ በቆዩ ሰራተኞች እና የትምህርት ተቋማት ላይ እርምጃ እንደሚወስድ አስታወቀ። ማንኛውም በሃሰት ማስረጃ የማይገባውን ቦታ ይዞ የሚገኝ ሰራተኛ እራሱን እንዲያጋልጥ የሰጠውንም የጊዜ ገደብ እስከ ታህሳስ 30 ቀን 2010 ዓ.ም. አራዝሞታል።

https://p.dw.com/p/2q4Ob
Stadtansicht von Addis Abeba Hauptstadt von Aethiopien
ምስል Imago/photothek

የቀነ ገደቡ እስከ ታህሳስ 30 ተራዝሟል

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከ105 ሺህ በላይ ሰራተኞች እንዳሉ መረጃዎች ይጠቁማሉ ። ይሁን እና እስካሁን በትክክለኛ ማስረጃ የተቀጠሩ የመኖራቸውን ያህል በመላው ሃገሪቱም ሆነ በከተማው አስተዳደር ከተለያዩ የትምህርት ተቋማት እና ሃሰተኛ ሰነድ ከሚሰሩ ግለሰቦች ህገ-ወጥ የትምህርት ማስረጃዎችን በማቅረብ የተቀጠሩ የማይገባቸውን ቦታ በመያዝ የስራ እንቅፋት የፈጠሩ እና ጥቅም እያገኙ  በወንጀል ተግባር የተዘፈቁ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰራተኞች መኖራቸው በተለያዩ መረጃዎች እና ጥቆማዎች እንደተደረሰበት አስተዳደሩ በመግለጫው አስታውቋል። ይህ ደግሞ በከተማው ለዓመታት ለተንሰራፉት የስራ ብቃት ማነስ እክሎች የመልካም አስተዳደር እጦት የተቀላጠፈ አገልግሎት ችግር እና ብልሹ አሰራር መንስኤ ሆኖ መቆየቱም ተመልክቷል።

የከተማው አስተዳደር የህዝባዊ አገልግሎት እና የሰው ሃይል ልማት ቢሮ ለማህበረሰቡ የሚሰጠውን የአገልግሎት እና የአስተዳደር ጥራት ለማሻሻል ሃሰተኛ የትምህርት ማስረጃ በማቅረብ ያለአግባብ ጥቅም ሲያገኙ የቆዩ ሰራተኞች እና ሃላፊዎች ሁሉ በፈቃደኝነት እራሳቸውን እንዲያጋልጡ የሰጠውን የጊዜ ገደብም እስከ ታህሳስ 30, 2010 ዓ.ም ማራዘሙን የቢሮው ሃላፊ አቶ ይስሃቅ ግርማይ ገልጸውልናል :: ሃላፊው የይቅርታ እና ምህረት አማራጩ የተፈለገው እና ሁሉንም ጥፋተኞች ለህግ ማቅረብ ያልተፈለገው በሺዎች የሚቆጠሩ ጥፋተኞች ተመልሰው የሃገሪቱ ሸክም እናዳይሆኑ በማሰብ ነው ሲሉም አስረድተዋል :: የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በሰጠው የጊዜ ገደብ መሰረት ራሳቸውን በፈቃደኝነት ለሚያጋልጡ ጥፋተኞች በህግ የመጠየቅ ከለላ እንደሚሰጣቸው ምህረት እንደሚያደርግላቸውና አቅማቸው በሚመጥነው የስራ ቦታም መልሶ እንደሚመድባቸው አቶ ይስሃቅ ጨምረው ጠቁመዋል ::
ከአዲስ አበባ መስተዳድር የተገኘው መረጃ እንደሚጠቁመው እስካሁን የጊዜ ገደቡን ተጠቅመው ራሳቸውን ያጋለጡ ሰራተኞች ቁጥር ከ 100 አይበልጥም። ቀጣዩ እርምጃ በከተማው አስተዳደር ስር በሚገኙ መስሪያ ቤቶች ውስጥ በተቋቋሙ የአጣሪ ኮሚቴዎች ምርመራ አካሂዶ በሚሰበሰቡ ጥቆማዎች እና መረጃዎች መሰረት ጥፈተኞች እስካሁን አለአግባብ ያገኙትን ጥቅም እንዲከፍሉ እንደሚደረግ እና በህጉም መሰረት ቅጣት እንደሚወሰንባቸው ተመልክቷል። መስተዳድሩ ሲቭል ሰርቪሱ ግልጽ እና የተቀላጠፈ አሰራር እንዲኖረው አላደረገም የሚሉ አንዳንድ አስተያየት ሰጭዎች ከዚህ በፊትም ብዙዎች በሃሰተኛ ማስረጃ የማይገባቸውን ቦታ እና ጥቅም ሲያገኙ እንደነበር መረጃዎች እና ጥቆማዎች ሳደርሱት ቀርቶ ሳይሆን ትክክለኛ ሙያ እና እውቀት ያላቸውን ባለሙያዎች በሚመጥናቸው ቦታ ላይ መድቦ ከማሰራት ይልቅ ለድርጅታዊ ታማኝነት ከፍተኛ ቦታ እና ትኩረት ይሰጥ ስለነበር ነው ሲሉ ቅሬታቸውን ያሰማሉ ።አቶ ይስሃቅ ግን በዚህ አይስማሙም።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አሁን የጀመረው በሃሰተኛ ሰነድ የተቀጠሩ ወንጀለኞችን የማጥራት ዘመቻ ተራውን ሰራተኛ ብቻ ሳይሆን በአመራር ደረጃ የሚገኙትንም ጭምር እንደሚመለከት ነው የተገለጸው:: ሆኖም አስተዳደራዊ ይቅርታው ጥፋታቸውን በግልጽ ለሚያምኑ ሰራተኞች እንጂ የሃሰት ሰነድ የሚሰጡ የትምህርት ተቋማት ከፍርድ እንዳማያመልጡ ተመልክቷል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የጀመረው ወንጀለኞችን ለፍርድ የማቅረብ እንዲሁም ህግ እና ሥርዓትን የማስያዝ እርምጃ በሁሉም የስልጣን እርከን ላይ በሚገኙ አመራሮች እና በተለያዩ ክልሎችም ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ሲሉ በርካታ አስተያየት ሰጭዎች ይገልጻሉ።

Äthiopien - Addis Abeba - City Churchill Road
ምስል DW/Y. Geberegziabehr

እንዳልካቸው ፈቃደ

ነጋሽ መሐመድ