1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አዲሱ የደቡብ ሱዳን የሰላም ስምምነት ይከበር ይሆን?

ቅዳሜ፣ ሰኔ 23 2010

በደቡብ ሱዳን ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ የርስበርስ ጦርነት እንደቀጠለ ይገኛል። በጦርነቱ በአስር ሺህ የሚቆጠሩ ደቡብ ሱዳናውያን ሞተዋል፣ ብወደ አራት ሚልዮን የሚጠጉም ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል፣ ወደ ጎረቤት ሀገራትም ተሰደዋል። ተፋላሚዎቹ ወገኖች የተኩስ አቁም ደንብም ደርሰዋል። የተኩስ አቁም ደንብ ይፀና ይሆን? ብዙዎች ተጠራጥረውታል።

https://p.dw.com/p/30ZIY
Südsudan  Friedenstreffen - Präsidenten Salva Kiir und Rebellenführer Machar
ምስል Reuters/M. Nureldin Abdallah

«ስምምነቱ አዎንታዊነት ይታይበታል።»

የደቡብ ሱዳን ፕሬዚደንት ሳልቫ ኪር እና የዓማፅያኑ መሪ ሪየክ ማቸር ከሶስት ቀን በፊት፣ በጎርጎርዮሳዊው ረቡዕ ሰኔ 27፣ 2018 ዓም  የሰላም ስምምነት ተፈራርመዋል። ፕሬዚደንት ኪር እና የቀድሞ ምክትላቸው ሪየክ ማቸር በካርቱም የሱዳን ፕሬዚደንት በተገኙበት ስነ ስርዓት በፈረሙት የሰላም ስምምነት መሰረት፣ ተፋላሚዎቹ ወገኖች ዘላቂ የተኩስ አቁም ደንብ  በ72 ሰዓታት ውስጥ ተግባራዊ  ያደርጋሉ። ተቀናቃኞቹ ወገኖች መሪዎች የተኩስ አቁሙን ደንብ ባፋጣኝ ተግባራዊ ከማድረግ ጎን፣ የሰብዓዊ ርዳታ ለማቅረብ የሚያስችል መተላለፊያ ለመክፈት፣ የፖለቲካ እስረኞች ለመፍታት እና ከአራት ወር በኋላ የሽግግር መንግሥት ለማቋቋም ጭምር የደረሱት ይህ  ስምምነት በሀገሪቱ ሕዝብ ዘንድ ደቡብ ሱዳንን ያዳቀቀውን ጦርነት ላንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ያበቃል የሚል ተስፋ ፈንጥቋል። እርግጥ፣ ካሁን ቀደም የተደረሱ ብዙ ስምምነቶች በመጣሳቸው ይህ ከጥቂት ጊዜ በፊት የተፈረመው የሰላም ስምምነት በርግጥ ወደ ሽግግር መንግሥት ምሥረታ ማምራቱን ብዙ የደቡብ ሱዳን ዜጎች አሁንም  ቢጠራጠሩትም፣ ኪር እና ማቸር ስምምነቱ በተቀናቃኞቹ ወገኖች መካከል አሁንም የሚታዩ ልዩነቶችን ለማስወገድ መንገዱን ምቹ ያደርጋል ብለው እንደሚያምኑ በስምምነቱ ፍረማ ላይ የሰጡት ቃላቸው ስምምነቱ በአዎንታዊነት ሊታይ መቻሉን የጠቆመ መሆኑን የብሪታንያውያኑ ቻተም ሀውስ የፖለቲካ ጥናት ተቋም ተንታኝ አህመድ ሶሊማን ገልጸዋል። 
« ስምምነቱ አዎንታዊነት ይታይበታል። በደቡብ ሱዳን አጠቃላይ እና ዘላቂ ይሆናል ተብሎ ተስፋ የተጣለበትን የተኩስ አቁም ደንብ እንደገና ተግባራዊ ማድረግ የሚቻልበትን መንገድ የሚያመቻች ማዕቀፍ ነው። የተኩስ አቁሙን ተግባራዊ በማድረጉ ሂደትም ወቅት በአመራር እና በፀጥታ ፣ እንዲሁም፣ የሽግግር መንግሥት በማቋቋሙ ጉዳዮች ላይ የሚታዩ ልዩነቶችን የማስወገድ ስራ ሊሰራ ይችላል።»
አህመድ ሶሊማን እንዳሉት፣ በካርቱም ድርድር ላይ የተገኙት የተፋላሚዎቹ ወገኖች ተወካዮች ያሳዩት ስሜት ከሌሎቹ ጊዚያት ሁሉ ለየት ያለ እና የሚያበረታታ ቢሆንም፣  ሕዝቡ መጠራጠሩ አልቀረም።
« ብዙ የኃይል ርምጃ ማስቆሚያ ስምምነቶች ተፈርመው አይተናል፣ ግን አንዱም አልተከበረም። አሁን ያለው መንፈስ ልዩ ነው ይላሉ፣ ሳልቫ ኪር እና ሪየክ ማቸር የሰጧቸው አስተያየቶችም አዎንታዊ ናቸው። ይሁንና፣ የተፈናቀሉት እና የተሰደዱት ደቡብ ሱዳናውያን የመሪዎቻቸውን አነጋገር፣  በተግባር ተተርጉሞ እስከሚያዩት ድረስ ፣ ማመን ይከብዳቸዋል። »
ይህ ቢያንስ ውዝግቡን ለማብቃት ያለውን ፅኑ ፍላጎት የሚያጎላ አንድ ወደፊት የሚያስኬድ ርምጃ ሆኖ ተቆጥሯል፣  በሰላም ሂደት ወቅት፣ ቴክኒካዊ ዝርዝሮችን ለመጀመር ይህ ዓይነቱ አሰራር አስፈላጊ መሆኑንም ነው ሶሊማን ያስረዱት። የደቡብ ሱዳን ተቀናቃኞች በተፈራረሙት የሰላም ስምምነት መሰረት፣ የአፍሪቃ ህብረት  እና የምሥራቅ አፍሪቃ ማህበረሰብ የተኩስ አቁሙ ደንብ መከበርን ይቆጣጠራሉ። ምንም እንኳን ፕሬዚደንት ሳልቫ ኪር እና የዓማፅያኑ መሪ ሪየክ ማቸር ሰላም ስምምነት ቢፈራረሙም፣ የፖለቲካ በጎ ፈቃድ እና በመካከላቸው መተማመን በመጓደሉ ፕሬዚደንቱ በሽግግሩ መንግሥት ከማቸር ጋር ስልጣን መጋራታቸው አጠያያቂ ነው።
በአፍሪቃ ህብረት ቋሚ የደቡብ ሱዳን ተጠሪ፣ እንዲሁም፣ በኢትዮጵያ እና በጅቡቲ የደቡብ ሱዳን አምባሳደር ጄምስ ፒቲያ ሞርገን ከአራት ወር በኋላ ስለሚቋቋመው የሽግግር መንግሥት ምሥረታ አዎንታዊ አመለካከት ነው ያላቸው። 
« በዚሁ የሽግግር ዘመን ውስጥ በስምምነቱ የሰፈሩ አንዳንዶቹ ነጥቦች ተግባራዊ ይሆናሉ። ይሁንና፣ ማቸር ራሳቸው በሽግግሩ መንግሥት ውስጥ ስለመስራታቸውን ወይም ከጦር አዛዦቻቸው መካከል አንዱን ወይም ባልተቤታቸውን ስለመሰየማቸው እስካሁን ምንም የምናውቀው ነገር የለም።  ፕሬዚደንት ኪር ለሀገሪቱ እና ለሕዝባቸው ሲሉ ከማቸር እና ከቡድናቸው ጋር እንደገና ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውን አስታውቀዋል።»
ይሁንና፣ ከሰላሙ ስምምነት ፍረማ በኋላ ሱዳናዊው የውጭ ጉዳይ ሚንስትር አል ድርድሪ መሀመድ አህመድ እንዳመለከቱት፣ ተቀናቃኞቹን ወገኖች አሁንም ያላስማሙዋቸው አንዳንድ ነጥቦች አሉ።ለምሳሌ፣  ለስልጣን ክፍፍል እንዲያመች ሲባል የሽግግሩ መንግሥት አንድ ፕሬዚደንት፣ ሶስት ምክትል ፕሬዚደንቶች እና በርካታ ሚንስትሮች ይኑሩት የሚለው ሀሳብ ላይ በተለያዩት ቡድኖች መካከል ልዩነት አለ። ይህን ልዩነት በተመለከተ ምክክሩ ወደፊት እንደደሚቀጥል አምባሳደር ጄምስ ፒቲያ ሞርገን ለዶይቸ ቬለ ተናግረዋል።
« ቀጣይ ውይይት በቅርቡ በኬንያ ይደረጋል፣ በምሥራቅ አፍሪቃ የልማት በይነ መንግሥታት፣ ኢጋድ ሸምጋይነት በኬንያ ከሚካሄደው ውይይት በኋላ ተጨማሪ መረጃዎች ማቅረብ ይቻላል። በኬንያው ውይይት የሚደረሱት ተጨማሪ ውሳኔዎች ለመጨረሻ ፊርማ ወደ አዲስ አበባ ይወሰዳሉ። »
የተመድ በደቡብ ሱዳን ተፋላሚ ወገኖች ላይ ማዕቀብ ለመጣል ማሰላሰል በያዘበት ወቅት ነበር ሳልቫ ኪር እና ሪየክ ማቸር በምሥራቅ አፍሪቃ ሀገራት መሪዎች ሸምጋይነት ባለፈው ረቡዕ በካርቱም የሰላም ስምምነት የተፈራረሙት ። ከሁለት ዓመት ወዲህ ባለፈው ሳምንት በአዲስ አበባ ለመጀመሪያ ጊዜ ፊት ለፊት ተገናኝተው የተነጋገሩት ፕሬዚደንት ኪር እና የዓማፅያኑ መሪ ሪየክ ማቸር ለአምስት ዓመቱ የርስበርስ ጦርነት መፍትሔ እንዲያፈላልጉ ብርቱ ግፊት ነው ያረፈባቸው።

Südsudan Kämpfer
ምስል picture alliance/AP Photo/J. Lynch
Südsudan Flüchlinge suchen Schutz
ምስል picture-alliance/dpa/G. Fischer

አርያም ተክሌ

እሸቴ በቀለ