1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጀርመን የአፍሪቃ መርህ

ዓርብ፣ ኅዳር 28 2011

መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል ባለፈው ጥቅምት አጋማሽ በርሊን ውስጥ ታዋቂ የጀርመን ባለሀብቶችን እና አፍሪቃውያን መሪዎችን ያሳተፈ ጉባኤ በርሊን ቢያካሂዱም በጉባኤውም በአፍሪቃ በአነስተኛ እና መካከለኛ ውረታ ለሚሰማሩ ኩባንያዎች አንድ ቢሊዮን ዩሮ የኢንቬስትመንት ድጋፍ እንደሚሰጥ ቢገለጽም ምንም አድናቆት አላተረፈም።

https://p.dw.com/p/39goI
"Compact with Africa"-Konferenz in Berlin
ምስል picture-alliance/dpa/B. von Jutrczenka

የጀርመን የአፍሪቃ መርህ

የጀርመን መንግሥት የአፍሪቃ መርህ ከተለያዩ ወገኖች ትችቶች ይቀርቡበታል። በዚህ ዓመት በጥቅምት  አጋማሽ ላይ ጀርመን ርዕሰ ከተማ በርሊን በተካሄደው የጀርመን አፍሪቃ ጉባኤ ላይ ጀርመን በተወሰኑ የአፍሪቃ ሀገራት አንድ ቢሊዮን ዩሮ ለመወረት ቃል ገብታለች። የተገባው ቃል ግን በወረቀት ከመስፈሩ በስተቀር ተግባራዊ ለመሆኑ ጀርመናውያን ባለሀብቶች ይጠራጠራሉ ። አፍሪቃውያን የዘርፉ ባለሞያዎችም ደግሞ ከዚያ ይልቅ ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡ ሌሎች ጉዳዮች አሉ ይላሉ። የዶቼቬለው ዳንኤል ፔልስ ላጠናቀረው ዘገባ ኂሩት መለሰ።
የጀርመን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ቮልፍጋንግ ሾይብለ ባለፈው የጎርጎሮሳውያኑ ህዳር ወር መጨረሻ ላይ ለሁለት የአካባቢ ጥበቃ ባለሞያዎች ጀርመን ለአፍሪቃውያን በዘርፉ የምትሰጠውን ሽልማት ሲያበረክቱ በአጋጣሚው ከአፍሪቃ ጋር የተያያዙ መልዕክቶችን አስተላልፈው ነበር። «የጀርመን መጻኤ እድል፣  የአውሮጳ መጻኤ እድል የሚቀረጸው በአፍሪቃ እድገት ነው።» የሚለው አንዱ ነበር። « ስደት ከምትጎራብተን ክፍለ ዓለም ጋር በአዲስ መንገድ እንድንሰራ አስገድዶናል።» ያሉትም ሌላው ስለ አፍሪቃ እና ጀርመን ያነሱት ነጥብ ነበር። ሾይብለ የጀርመን የገንዘብ ሚኒስትር ሳሉ በጎርጎሮሳዊው 2017 ዓመት ነበር ኮምፓክት ዊዝ አፍሪቃ የተባለው አዲሱ የጀርመን እና የአፍሪቃ ትብብር ይፋ የሆነው።  ከዚህ የትብብር መርሃ ግብር አርቃቂዎች አንዱ ሾይብለ በመርሃግብሩ ከጀርመን የሚጠበቀውን እና የአፍሪቃንም ድርሻ ገልጸው ነበር።
« በ2017 ቱ ኮምፓክት ዊዝ አፍሪቃ አዲስ የምጣኔ ሀብት ትብብር መስርተን ነበር። በዚህ ትብብርም ከመንግሥት ሌላ ከምንም በላይ የግሉ ዘርፍ ውረታም አስፈላጊ ነው። ለዚህም የአፍሪቃ መንግሥታት  አስፈላጊዎቹን ቅድመ ሁኔታዎች ማመቻቸት አለባቸው። ለግል ውረታን ለማስፋፋት ደግሞ ምቹ ሁኔታዎች ያስፈልጋሉ። እዚህ ጋ ነው የኮምፓክት ዊዝ አፍሪቃ ድርሻ።»
የዛሬ 2 ዓመት ከኮምፓክት ዊዝ አፍሪቃ ጎን ለጎን የጀርመን የልማት እና ትብብር ሚኒስቴር መስሪያ ቤት «የአፍሪቃ ማርሻል ፕላን» ፣የጀርመን የኤኮኖሚ ጉዳዮች ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ደግሞ ፕሮ አፍሪቃ »የተባሉትን መርሃ ግብሮች ቀርጸው ነበር። በመርሃግብሮቹም የጀርመን ኩባንያዎች አትራፊ ገበያ ያገኛሉ፤ ለአፍሪቃውያንም የሥራ እድሎች ይፈጠራሉ የሚል እሳቤ ነበር። መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል ባለፈው ጥቅምት አጋማሽ በርሊን ውስጥ ታዋቂ የጀርመን ባለሀብቶችን እና አፍሪቃውያን መሪዎችን ያሳተፈ ጉባኤ በርሊን ቢያካሂዱም በጉባኤውም በአፍሪቃ በአነስተኛ እና መካከለኛ ውረታ ለሚሰማሩ ኩባንያዎች አንድ ቢሊዮን ዩሮ የኢንቬስትመንት ድጋፍ እንደሚሰጥ ቢገለጽም ምንም አድናቆት አላተረፈም። የጀርመን ማርሻል ፕላን ለአፍሪቃ መርሃ ግብር የዛሬ ሁለት ዓመት በይፋ ቢጀመርም በፌደራል መንግሥት ደረጃ የጋራ ስልት አለመኖሩ ይተቻል። በዚህ ማርሻል ፕላን ጀርመን ከጋና አይቮሪ ኮስት እና ቱኒዝያ ጋር «የተሃድሶ አጋርነት» ስምምነት አድርጋለች።የጀርመን መንግሥት ለእነዚህ 3 ሀገሮች ለኃይል አቅርቦት፣ ለባንክ ዘርፍ እና ባለሀብቶችን እንዲስቡ ለማስቻል የሚያግዝ የ365 ሚሊዮን ዩሮ እርዳታ ይሰጣል። ይህ እርዳታም የግሉን ዘርፍ ባለማካተቱ ይተቻል። በሌላ በኩል በአፍሪቃ የሚካሄዱ ተጨማሪ ውረታዎች ለተራው አፍሪቃዊ ይህ ነው የሚባል ጥቅም አለማስገኘታቸውም ያጠያይቃል። ትኩረታቸውን ትርፍ ላይ ያደረጉ መንግሥታት ምን ያህል ለህዝቦቻቸው መብቶች የቆሙ ስለመሆናቸው የመከታተያ ስርዓት አለመዘርጋቱ ፊያን የተባለው ኡጋንዳ እና ዛምቢያ ውስጥ የሚንቀሳቀሰው የሰብዓዊ መብት ድርጅት ባልደረባ ግሎሪ ሉዎንግ ከሚተቿቸው ጉዳዮች አንዱ ነው።
«ሁኔታዎችን ለባለሀብቶች ምቹ ማድረግ ብቻ ነው የሚፈልጉት። ለህዝቦቻቸው መብቶች ብዙም አያስቡም። በመንግሥትም ይሁን በግል ባለሀብቶች ከሚታገዙ ውረታዎች ለምሳሌ የጀርመን መንግሥት መርሃ ግብሮቹ የተገለሉ የህብረተሰብ ክፍሎችን መብቶች አለመጋፋታቸውን የሚቆጣጠርበት ስልት የለም።»
ሉዌንግ በተለይ በግብርናው ዘርፍ የሚደርሱ የመብት ጥሰቶችን ነው የሚያነሱት። የሚተቹትም መንግሥትን ብቻ አይደለም። የጀርመን ኩባንያዎችን እና ድርጅቶችንም ጭምር እንጂ ። ለጀርመኑ የጥሬ ቡና አቅራቢ ድርጅት ኖይማን መሬት ለመስጠት የኡጋንዳ ጦር ሰራዊት በሺህዎች የሚቆጠሩ የአካባቢውን ነዋሪዎች ማፈናቀሉ ይነገራል። በኮንጎም እንደዚሁ ለጀርመን ድርጅት ውረታ ሰዎች ከአካባቢያቸው እንዲለቁ ተደርጓል። ተችዎች እነዚህን ስምምነቶችች ህገ ወጥ ነው የሚሏቸው። በጎርጎሮሳዊው 2019 የጀርመን ኩባንያዎች በአፍሪቃ ተጨማሪ ውረታዎችን ማድረግ አለማድረጋቸው እነዚህ ውረታዎችም ብልጽግና ማምጣታቸውም ሆነ ሥራ መፍጠራቸው እንዴት እንደሚቀጥል የጀርመን የአፍሪቃ መርህ ተችዎች እና ደጋፊዎች በጉጉት የሚከታተሉት ጉዳይ ይሆናል።  
ኂሩት መለሰ
ሸዋዬ ለገሠ
 

Compact with Africa - Teilnehmer beim Bundespräsidenten
ምስል picture-alliance/dpa/B. von Jutrczenka
Deutschland Afrika-Gipfel bei Bundeskanzlerin Angela Merkel
ምስል Reuters/A. Schmidt
Conflict Zone mit Wolfgang Schäuble
ምስል DW/M. Martin