1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አወዛጋቢው በአማራና በትግራይ ክልሎች ያለው  የአስተዳደር ወሰን

ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 25 2011

በአማራና በትግራይ ክልሎች ያለውን  የአስተዳደር ወሰንና በየጊዜው የሚነሳውን የማንነት ጥያቄ በዘላቂነት ለመፍታት በህዝብ ነፃ ፍላጎት ላይ የተመሰረተ አከላለል አንደገና ሊካሄድ እንደሚገባ ምሁራንና የህግ ባለሙያዎች አመለከቱ።

https://p.dw.com/p/3Azul
Karte Äthiopien Amhara, Tigray, Oromia Englisch

አወዛጋቢው በአማራና በትግራይ ክልሎች ያለው  የአስተዳደር ወሰን

በትግራይና በአማራ ክልሎች መካከል የተፈጠሩ የወሰንና የማንነት ጥያቄዎች ለግጭት መነሻ የሆኑት ከዚህ በፊት የህዝብን ፍላጎት  ያላማከለ የአከላለል ሥራ መከናወኑ እንደነበርም ተገልጧል፡፡ አዲስ የተቋቋመው  የአስተዳደር ወሰንና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን የህዝቦችን ፍላጎትና ታሪክን መሰረት በማድረግ የሚያከናውነው  ጥናትና የሚያቀርበው  የውሳኔ ሀሳብ ተግባሪዊ ከሆነ በዚህ ረገድ ያለው የሁለቱ ክልሎች እሰጣ ገባ መፍትሄ እንደሚያገኝም አመልክተዋል፣ የኮሚሽኑ ሥራ  ተግባራዊነት ግን አስቸጋሪ አንደሚሆነ ስጋቶችም ተነስተዋል፡፡

በአማራና በትግራይ ክልሎች አዋሰኝ አካባቢዎች ከወሰን አከላለልና ከማንነት ጥያቄ ጋር በተያያዙ በየወቅቱ በሚነሱ ግጭቶች መካከል ብዙዎች ተፈናቅለዋል፣ አክል ጎድሏል ህይወት ጠፍቷል፣ ንብረትም ወድሟል፡፡ ለዚህ ችግር የተለያየ መነሻ ቢኖረውም ዋናው ግን በ1984 ዓ.ም የተደረገው ህዝብን ያላማከለ የአስተዳደር ወሰን አከላለል የህዝብን ፍላጎት መሰረት አለማድረጉ እንደሆነ የህግ ባለሙያውና የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ የድርጅት ጉዳይ ኃላፊ አቶ ደሴ ጥላሁን ይናገራሉ፡አዲሱ የአስተዳደር ወሰንና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን ዘላቂ ሰላም ያመጥል ብለው ግን ያምናሉ፡፡
አቶ መርሐጽድቅ መኮንን በቢሮ ኃላፊ  ማዕረግ የአመራ ክልል ርእሰ መስተዳድር ዋና የህግ አማካሪ ናቸው፡፡ እርሳቸውም ቢሆን ህገመንግስቱ ከመጽደቁ በፊት የተዋቀረው የአስተዳደር ወሰን በወቅቱ የፖለቲካ የሀይል ሚዛን በነበረው አካል የተካለለ በመሆኑ የአስተዳደርና የማንነት ጥያቄ ማስነሳቱን ያብራራሉ
በመሆኑም የተቋቋመው የአስተዳደር ወሰንና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን ችግሮችን ከታረሪክ፣ ከባህል፣ ከህዝቦች ፍላጎትና ሌሎችንም ጉዳዮች በጥልቀት አጥንቶ በሚያቀርበው ውጤት መሰረት የአስተዳደር ወሰንና የማንነት ጥያቄዎች ምላሽ ያገኛሉ ብለዋል፣ ተቋሙ የፌደሬሽን ምክር ቤትን የሚተካ ሳይሆን ለምክር ቤቱ አጋዥ መሳሪያ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡
በሲቪል ሰርቪስ ዩኒቭረሲቲ በህዝብ ስራ አመራር የዶክተሬት ድገሪያቸውን እያጠኑ ያሉት አቶ ቹቹ አለባቸው ደግሞ ሁሉም አካላት ባልተስማሙበት ሁኔታ የኮሚሽኑ ተግባራዊነት ከባድ መሆኑን ይናገራሉ፡፡
ስለጉዳዩ አስተያየት እንዲሰጡኝ ወደ ትግራይ ክልል የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ ወ/ሮ ሊያ ካሳ የእጅ ስልክ ላይ በተደጋጋሚ ብደውልም ስልኩ ባለመነሳቱ የክልላዊ መንግስቱን ሀሳብ ለማካተት አልተቻለም፡፡

ዓለምነው መኮንን

አርያም ተክሌ

ማንተጋፍቶት ስለሺ