1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ስደተኞችን ወደበረሃ የምትወረውረው አልጀሪያ

ዓርብ፣ ሰኔ 29 2010

አሸዋ እና ሙቀት ብቻ ነው ሰሜን ኒዠር በሚገኘው በቴኔሬ በረሃ ያለው። በዚህ ስፍራ የአልጀሪያ የፀጥታ ኅይሎች ያባረሯቸው በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ፈላስያን እና ስደተኞች ይገኛሉ። ውሐም ሆነ ምግብ የላቸውም፤ የወደፊት እጣቸውም ምን እንደሆነ አያውቁም

https://p.dw.com/p/30wsN
Algerien Geflüchtete in Wüste ausgesetzt
ምስል picture-alliance/dpa/J. Dennis

ስደተኞችን ወደበረሃ የምትወረውረው አልጀሪያ

 
አልጀሪያ ለወራት በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩ ስደተኞችን ኒዠር እና አልጀሪያ መሀል በሚገኝ በረሃ በመወርወር እየተወቀሰች ነው። በሕይወት የተረፉ እንደሚናገሩት ሙቀቱ ከ40 ዲግሪ ሴንቲግሬድ በላይ በሆነው በዚህ በረሃ የሚደረገው ጉዞ ቀናት ይወስዳል። በዚህ ጉዞ የበርካታ ሰዎች ሕይወት ጠፍቷል።የአውሮጳ ህብረት በሰሜን አፍሪቃ ሀገራት የተገን ጠያቂዎች ማቆያ ማዕከላት እንዲቋቋሙ ይፈልጋል። ሆኖም በአልጀሪያ ያለው ሁኔታ በእቅዱ ላይ ጥቁር ጥላ ያጠላበት ይመስላል። ወደፊት በአልጀሪያ የፈላስያን እና የስደተኞች እጣ ፈንታ እያነጋገረ ነው። የዶቼቬለ የሰሜን ምዕራብ አፍሪቃ ወኪል ዱንጃ ሳዳኪ ያላከውን ዘገባ ኂሩት መለሰ አጠናቅራዋለች። 
አሸዋ እና ሙቀት ብቻ ነው ሰሜን ኒዠር በሚገኘው በቴኔሬ በረሃ ያለው። በዚህ ስፍራ የአልጀሪያ የፀጥታ ኅይሎች ያባረሯቸው በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ፈላስያን እና ስደተኞች ይገኛሉ። ውሐም ሆነ  ምግብ የላቸውም፤ የወደፊት እጣቸውም ምን እንደሆነ አያውቁም ይላል የኦሶስየትድ ፕሬስ ዘገባ። በሞት ስጋት ውስጥ ሆነው ለቀናት በማያውቁት አካባቢ ሲጓዙ የነበሩት ስደተኞች ድንገት ሊጠጉ የሚችሉበት መንደር ያያሉ። ዴኒስ በዚህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ሆነው በበረሃ ሲጓዙ ከነበሩት እና በሕይወት ከተረፉት ስደተኞች አንዱ ነው። ዴኒስ በእጅ ስልኩ የቀረጸው ይህ አሰቃቂ ጉዞ አሁን በመገናኛ ብዙሀን እየተሰራጨ ነው።   
«አሁን የምዘግበው በቀጥታ አልጀሪያ እና ኒዠር መካከል ከሚገኝ በረሃ ነው። እንደማየው ይህ ወደዚያ የሚሄድ ተሽከርካሪ ነው። ጥቁሮች በብዛት በተሽከርካሪው ምንም ዓይነት ነገር ሊደርስ ወደሚችልበት ምድረ በዳ እየተወሰዱ እየተጣሉ ነው። በተሽከርካሪው ውስጥ ሴቶች እና ህጻናትም ይገኙበታል።»
ይላል ዴኒስ በሰዎች በታጨቀ መኪና በበረሃ ውስጥ እየተጓዘ። ከጥቂት ጊዜያት በኋላ ስደተኞቹ በረሃ ውስጥ ይጣላሉ።  እድል የቀናቸው አሳማካ ይደርሳሉ። አሳማካ ኒዠር ውስጥ የምትገኝ አነስተኛ የበረሃ መንደር ናት። በዚያ ውሐም ሆነ እርዳታ ይገኛል። ኒዠር ዋነኛ የስደተኞች መነኻሪያ ናት። ከሰሀራ በስተደቡብ ከሚገኙ ሀገራት የሚመጡ ስደተኞች ከኒዠር ተነስተው በሊብያ ወይም በአልጀሪያ በኩል ወደ አውሮጳ ለመሻገር ይሞክራሉ። ሆኖም አሳማካ የደረሱት ሁሉ ይህ ይሳካላቸዋል ማለት አይደለም። ምክንያቱም በጉዞ ላይ የሰውነታቸው ውሐ የሚያልቅና  እና ነፍሳቸውን የሚስቱ በርካቶች ናቸው። አንዳንዶቹ ፣ የአልጀሪያ የፀጥታ ኃይሎች ስደተኞቹ የያዙትን ገንዘብ እንዲሁም የእጅ ስልኮቻቸውን እንደሚቀሟቸው ይናገራሉ።ዴኒስ በቪድዮው መተረኩን ቀጥሏል። 
«ፍጹም ምድረ በዳ ውስጥ ነው የነበርነው። ስድስት ሰባት ሰዓታት ተጉዘናል። እግሬ ከኔ ጋራ የለ ሆኖ አይሰማኝም። አቅሜ ሁሉ ተሟጧል።»
በአሁኑ ጊዜ ችግሩ ዓለም አቀፍ ትኩረት ስቧል። ጉዳዩን ሲከታተሉ ከቆዩ ድርጅቶች አንዱ ዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች ጉዳይ ድርጅት በምህጻሩ IOM ነው። የድርጅቱ ቃል አቀባይ ፍሎረንስ ኪም ችግሩን አሳሳቢ ይሉታል።
« የምናገረው ሥልጣኔ ከሚታይባቸው አካባቢዎች 30 ኪሎ ሜትር ርቆ አውላላ ሜዳ ላይ ስለሚጣሉ ሰዎች ነው። ከመስከረም ወዲህ ብቻ ለዚህ ዓይነቱ ሁኔታ የተዳረጉ 10 ሺህ ናይጀሪያውያንን ቆጥረናል። ይህ አሳሳቢ ነው። ወንዶች ብቻ አይደለም የምናየው ፤ነፍሰ ጡር ሴቶች እና ህጻናትም ካለወላጅ የሚሰደዱ ታዳጊዎችንም ጭምር ነው።በጣም አሰቃቂ ሁኔታ ውስጥ ነው ያሉት።ብዙዎቹ ይሞታሉ።»
ባልደረባቸው አልሆሳን አዱዋል እርዳታ የሚያሻቸውን ሰዎች ለመፈለግ በየጊዜው አልጀሪያ ድንበር ይሄዳል። ራሱን እየነቀነቀ ወደ በረሃው አቅጣጫ ያመለክታል። በሺህዎች የሚቆጠሩ ህጻናት እና ነፍሱሮች ጡሮች ጭምር ወደዚያ እንደሚመጡ ይናገራል። ከመካከላቸው ጃኔት ካማራ አንዷ ናት። በጉዞ ላይ ጽንስዋ ተጨናግፏል።
« ህጻን ልጃችንን አጣን ። ልጃችን ተገደለብን። ሴቶች፣ ወንዶች ሞተዋል። ምክንያቱም ውሐም ሆነ ምግብ ባለመኖሩ ተርበው ነው የሚሞቱት።ህዝባችን በሙሉ በረሃ ውስጥ እየጠፋ ነው። ምክንያቱም መንገዱን አያውቁትም።» 
የአልጀርስ ባለሥልጣናት ግን የሚቀርብባቸውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት ክስ ያስተባብላሉ። አልጀሪያ ስደተኞችን በህጉ መሠረት ነው የምታስተናግደው ነው የሚሉት። እንደ ባለሥልጣናቱ የምትመልሳቸውም ለደህንነት አስጊ ናቸው የምትላቸውን ከጎረቤት አገሮች ጋር ባደረገችው ስምምነት መሠረት ነው። ባለሥልጣናቱ ይህን ቢሉም የመብት ተሟጋች ድርጅቶች ግን አልጀሪያን በስደተኞች አያያዝ እንደተቹ ነው።  ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሀን በአልጀሪያ ላይ ወቀሳዎች ቢያቀርቡም የአውሮጳ ህብረት ፖለቲከኞች ግን ጆሮ ዳባ ልበስ ያሉ ነው የሚመስለው።

Algerien Geflüchtete in Wüste ausgesetzt
ምስል picture-alliance/dpa/J. Dennis
Karte Nordafrika Flüchtlinge DE

ኂሩት መለሰ

አርያም ተክሌ