1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ችግር ዉስጥ ነን፤ የምስራቅ ጉጂ ዞን ተፈናቃዮች 

ሰኞ፣ ጥቅምት 5 2011

በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ጉጂ ዞን በተከሰተው ግጭት ተፈናቅለው በመጠለያ ጣቢያዎች የሠፈሩ ነዋሪዎች በከፍተኛ ችግር ውስጥ እንደሚገኙ እየተናገሩ ነው፡፡ ተፈናቃዮቹ መንግሥት ወደ ቀድሞ አካባቢያቸው ለመመለስ የገባውን ቃል ተግባራዊ ባለማድረጉ ለተጨማሪ እንግልት መዳረጋቸውን ገልጸዋል፡፡

https://p.dw.com/p/36aWg
Äthiopien ethnische Minderheit der Gedio
ምስል DW/Shewngizaw Wegayehu Aramdie

ተፈናቃዮች «ለስቃይ አየተዳረግን እንገኛለን»

በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ጉጂ ዞን በተከሰተው ግጭት ተፈናቅለው በመጠለያ ጣቢያዎች የሠፈሩ ነዋሪዎች በከፍተኛ ችግር ውስጥ እንደሚገኙ እየተናገሩ ነው፡፡
ተፈናቃዮቹ መንግሥት ወደ ቀድሞ አካባቢያቸው ለመመለስ የገባውን ቃል ተግባራዊ ባለማድረጉ ለተጨማሪ እንግልት መዳረጋቸውን ገልጸዋል፡፡ በዲላ ከተማ አቅራቢያ በጅምር በሚገኝ የመንግሥት ህንጻዎች ውስጥ ተጥልለው ከሚገኙት ተፈናቃዮች መካከል አብዛኞቹ ሴቶች፤ ህጻናትና አረጋዊያን ይገኙበታል፡፡ ተፈናቃዮቹ እንደሚሉት ቀደምሲል ወደ መኖሪያቸው አካባቢያቸው እንደሚመለሱ በመንግሥት በኩል ቢገለጽላቸውም እስከአሁን ግን ገቢራዊ አልሆነም፡፡ በዚህም ምክንያት በመጠለያ ካምብ ውስት ምቹ ባልሆነ ሁኔታ ለአንግልትና ለስቃይ አየተዳረጉ እንደሚገኙ ነው ለዲ ደብሊው ሬዲዮ የገለጹት ፡፡ 
ካነጋገረኳቸው መካከል አብዛኞች ወደ ቀድሞ ቀዬያቸው የመመለስ ፍላጎት እንዳላቸው ይናገራሉ፡፡ በአንጻሩ ግን ከደህንነት ሥጋት ጋር የተያያዘ የፍርሃት ድባብ በፊታቸው ይነበባል፡፡ ከሰባት ልጆቻቸው ጋር በቄራ የመጠለያው ጣቢያው ተጠልለው ከሚገኙት እናቶች መካከል አንዷ ወይዘሮ ሲርቤ ጉዮ  አንዷ ናቸው፡፡  ወይዘሮ ሲርቤ ያሉበትን አስቸጋሪ ሁኔታ ሲናገሩ
“ መንግሥት ችግራችንን ሊያይልንና ሊረዳን ይገባል፡፡ እንደበፊቱ በሰላም ሰርተን የምንኖርበት ሁኔታን እንፈልጋለን ፡፡አዚህ ከህጻናት ጋር በችግር ውስጥ ሆነን መቆየትን አንመርጥም ፡፡ ህግ ተከብሮልን ፤ ሰላማችን ተጠብቆ መኖር እንፈልጋለን ፡፡ “
በተፈናቃዮቹ ቅሬታ ዙሪያ ያነጋገርኳቸው በጌዲዮ ዞን አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና መምሪያ ተወካይ አቶ ትዕግስቱ ገዛኋኝ እንዳሉት ፤ ከኦሮሚያ ክልል ምስራቅና ምዕራብ ጉጂ ዞኖች ተፈናቅለው ከሚገኙት ዜጎች መካከል እስከአሁን ከ300 ሺህ በላይ የሚሆኑትን ወደ አካባቢያቸው የመመለስ ሥራ ተከናውኗል ፡፡ ይሁንእንጂ ከምስራቅ ጉጂ ሶስት ወረዳዎች የተፈናቀሉ ነዋሪዎች ግን አስከአሁን አለመመለሳቸው ትክክለ መሆኑን በመግለጽ እስከአሁን ተፈናቃዮችን ወደ አካባቢያቸው መመለስ ያልተቻለው የምዝገባና የማጣራት ሥራ በተያዘው ፍጥነት ባለመከናወኑ መሆኑን በምክንያትነት ጠቅሰዋል፡፤
ይሁንእንጂ ሂደቱ እንዳለቀ ተፈናቃዮችን በጥቂት ሳምንታት ወደ አካባቢያቸው የመመለስ ሥራ ይካሄዳል ብለዋል አቶ ትዕግስቱ ፡፡ ተፈናቃዮቹ ወደ ቀድሞው ቀዬቸው ሲመለሱ የደህንነት ችግር እንዳያጋጥማቸው ከገዳ አባቶች ጋር በመሆን የሰላም ሥራዎች በመሰራት ላይ እንደሚገኙም አመልክተዋል፡፡ ከወራት በፊት በኦሮሚያ ክልል ምስራቅና ምዕራብ ጉጂ ዞኖች ተከስቶ በነበረው ግጭት  ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ዜጎች መፈናቀላቸው ይታወሳል ፡፡ የክልሉ መንግሥት በግጭቱ አጃቸው አለበት ያላቸውን እንዳንድ የወረዳ ሹማምንቶችን ይዞ ሲያስር ፤ ከፊሎቹን ደግሞ ከሃላፊነት ማንሳቱም የሚታወቅ ነው ፡፡ 

Äthiopien ethnische Minderheit der Gedio
ምስል DW/Shewngizaw Wegayehu Aramdie

ሸዋንግዛው ወጋየሁ
አዜብ ታደሰ 
ሸዋዬ ለገሠ