1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ትጥቅ አልፈታም ያለው ኦነግና የቤተመንግሥቱ ክስተት

ዓርብ፣ ጥቅምት 2 2011

ወደ 240 የሚጠጉ ወታደሮች ከነትጥቃቸው ወደ ቤተመንግሥት ማቅናታቸው መነገሩ በሳምንቱ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ሰፊ የመነጋገሪያ ርእስ ኾኗል። የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ወኃደሮቹ ትጥቅ እንደማይፈቱ መግለጡ ሌላኛው ዐቢይ ርእስ ነበር። 

https://p.dw.com/p/36OTs
Äthiopien Ministerpräsident Abiy Ahmed wandte sich an einige Mitglieder der äthiopischen Streitkräfte
ምስል Fitsum Arega/Chief of Staff/Prime Minister's Office of Ethiopia

«አንዱ ትጥቅ የሚፈታ አንዱ የሚያስፈታ ይመስላል»

ኦነግ ትጥቅ አልፈታም ማለቱ፤ እንዲሁም የታጠቁ የመከላከያ ሠራዊት አባላት ወደ ቤተመንግሥት ማቅናታቸው ሰሞኑን በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች መነጋገሪያ ከኾኑ ጉዳዮች ዋነዎቹ ናቸው። የኦነግ እና የመንግሥት የቃላት ግብግብ ወደ ሌላ እንዳያመራ የሰጉ በርካቶች ናቸው። ቁጥራቸው ወደ 240 ይጠጋል የተባሉ የመከላከያ ወታደሮች በቤተመንግሥቱ አካባቢ ግር ብለው ሲጓዙ የሚታይበት ፎቶግራፍ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች መሰራጨቱ በበርካቶች ዘንድ ስጋትን አሳድሮ ቆይቷል። ወታደሮቹ «ለደሞዝ ጭማሪ ጥያቄ ነው ቤተመንግሥት ያቀኑት» መባሉን ብዙዎች አልተቀበሉትም። ይልቁንም የሀገሪቱ የጸጥታ ኹኔታ አጠያያቂ ነው ሲሉ አስተያየት ሰጥተዋል።

እያደር አዲስ ክስተት የማይታጣበት የኢትዮጵያ ወቅታዊ ኹኔታ ባለፉት ጥቂት ቀናት አስደንጋጭ እና ከባድ የሚባሉ ክስተቶችን አስተናግዷል። ረቡዕ መስከረም 30 ቀን 2011 ዓም አዲስ አበባ የኢንተርኔት አገልግሎት ተቋርጦ ቆይቶ ነበር። የዚህ ምክንያቱ ደግሞ «የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት የልዩ ኃይል አባላት» ናቸው የተባሉ ከሁለት መቶ በላይ ወታደሮች ረፋዱ ላይ ወደ ቤተመንግሥት ማቅናታቸው እንደሆነ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ተጠቅሷል። የተባሉት ወታደሮች ወደ ቤተመንግሥት ሲያቀኑ የሚያሳዩ ናቸው የተባሉ ፎቶግራፎችም በስፋት ተሰራጭተዋል።

አባ ባህረይ የተባለ የፌስቡክ ተጠቃሚ የረቡዕ ዕለት ክስተቱን በተመለከተ 10 ጥያቄዎችን አስፍሯል። «የትናንቱ የአጋች ታጋች አማተር ድራማ» በማለት ነው የሚንደረደረው። ድርጊቱንም አንድ ሁለት እያለ ይዘረዝራል። «1. ኢንተርኔት ከጠዋት ጀምሮ ለምን አጠፉት...2. የመከላከያ ደህንነት ስራው ምንድን ነበር? የትስ ነበሩ? ምን ሰሩ? 3. የሲቪል ደህንነት...በተለምዶ ደህንነት የባለው ምን ሰራ? 4. ኢታማዠር ሹሙ ምን ነበር ስራቸው? የት ነበሩ? ምን ሰሩ? 5. መከላከያ ሚ/ሩ የት ነበሩ? ምን ሰሩ?...» እያለ በማብራራት እስከ ተራ ቁጥር ዐሥር ይዘልቅና በስተመጨረሻ «ሁሉም ነገር አስቀያሚና ተልካሻ ድራማ ነው!!!» ሲል ይደመድማል።

Äthiopische  Generäle Adem Mohammed und Seare Mekonen
የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄኔራል ሠዓረ መኮንን እና የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ጄነራል አደም ሞሐመድምስል Nahom Tesfaye

ወታደሮቹ ቤተመንግሥት ከደረሱ በኋላ ከጠቅላይ ሚንሥትር ዐቢይ አህመድ ጋር ስለደሞዝ ጭማሪ ነው የተወያዩት መባሉን ማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ላይ ብዙዎች አልተቀበሉትም። ሠይፈስላሴ ገበረመስቀል ጓንጉል ፌስቡክ ላይ ባሰፈረው ጽሑፉ፦ «ድራማው ቀጥሏል፣ደመወዝ ጭማሬ ለመጠየቅ ከመጡ ሰራዊቶች ጋር ጠቅላይ ሚኒስተሩ በቤተመንግስት ተወያዩ ይሉሀል» በማለት ይነደረደርና ነገሩ እንዳልተዋጠለት «እኔምለው» ሲል ይዘረዝራል። «እኔምለው:240 የሚሆኑ የመከላከያ ሠራዊት አባላት ከእነ ትጥቃቸው ወደ ቤተ መንግሥት ሄደው -ቤተመንግስት የሚወስዱ ዋናዋና ወደ መገዶች ተዘግተው -የከተማው ኢንተርኔት ተዘግቶ ነው እንዴ የደመወዝ ጭማሬ ስብሰባ የሚካሄድው በማለት አጠይቆ ጽሑፉን፦ « የማይመስል ነገር ለሚስትህ አትንገር» ሲል ደምድሟል።

«አጉል ቀልድ መሣይ ነገር» ያለው ደግሞ ሰዒድ የሱፍ ዓሊ ነው። «ቤተመንግስት ድረስ ታጥቆ ሊገባ የነበረ ወታደር በፑሻፕ ተታለ፤ ትጥቁን ፈትቶ ከሄደ ልብ ያለው መንግስት ይቺን አንቀጽ መጥቀስ ይችላል» በማለት በፎቶግራፍ የተነሳ አንቀጽን አያይዟል።  እንዲህ ይነበባል።

«አንቀጽ 299 ወታደራዊ አመጽ። 1 ማንኛውም የመከላከያ ሠራዊት አባል ከሌሎች ወታደሮች ጋር በመተባበር ሕጋዊ ባልሆነ ስብሰባ በመካፈል ወይም በማናቸውም ሌላ ሁኔታ በበላይ አለቃ ወይም ወታደራዊ ባለሥልጣን ላይ፣ ወይም የበላይ አለቃን ወይም ወታደራዊ ባለሥልጣንን በመቃወም በተፈጸመ ያለመታዘዝ፣ የተቃውሞ፣ የዛቻ፣ የኃይል ድርጊት ወይንም የእጅ እልፊት እንቅስቃሴ ውስጥ ተካፋይ እንደሆነ ከአሥራ አምስት ዓመት በማይበልጥ ጽኑ እስራት ይቀጣል።»

ሚካኤል አሥራት ጽሑፉን የሚጀምረው በሳቅ የሚያነባ የፌስቡክ ምስል በማያያዝ ነው። «እንዲ ስናጠፋ ፑሽ አፕ አሠርቶ ራት ጋብዞ በፍቅር የሚቀጣ አለቃ ያብዛልን» የሚል አጭር መልእክት አስፍሯል። ወታደሮች እና ጠቅላይ ሚንሥትር ዐቢይ ፑሽ አፕ ሲሠሩ የሚያሳይ ፎቶግራፍ አያይዟል። በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የተሠራጨው የቪዲዮ ምስል ነጭ ሸሚዝ የለበሱት ጠቅላይ ሚንሥትሩ የደንብ ልብስ እና ቀይ መለዮ ካደረጉ ወታደሮቹ ጋር ፑሽ አፕ ሲሠሩ ይታያል።

በዋትስአፕ የደረሰን መልእክት እንዲህ ይነበባል፦ «DW ሰላም ናችሁ ትናንት ቤተመንግስት ልዩ ሃይሎች ያቀረቡት አቤቱታ እኛ ጋምቤላ ያለ ነው በየግዜው ጥቆማ እንደሰጠናችሁ የኢ/ያለ ሰላም አስከባሪ የላቡን እያገኘ አይደለም የሚመለከተውን ሀላፊ ጠይቃችሁ መልስ እንደምትሰጡን ተስፋ እናደርጋለን UN ከሚከፍለው ደመውዝ 56% ይቆረጣል የግለሰብ ላብ ነው በሀገሪቱም ህግ ከማንኛውም ገቢ ግብር ብቻ ነው ግደታ የሚለው ለሁሉም ሰላም እንሁን»

ቤተመንግሥት ያቀኑትን ወታደሮች በተመለከተ ጠቅላይ ሚንሥትር ዐቢይ ከተናገሩት የተቀነጨበ ድምጽ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች በስፋት ተንሸራሽሯል።

Äthiopien Abiy Ahmed Premierminister
የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንሥትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር)ምስል picture-alliance/AP Photo/Saudi Press Agency

ትዊተር ላይ ከተጻፉ አስተያየቶች መካከል ሸዋረግ አሰፋ፦ «ግራ የገባው ለውጥ ግራ የሚያጋባ ጊዜ! ከነትጥቁ ቤተመንግስት የተከሰተ ጦር በፑሻፕ ተሸኘ በሺዎች የሚቆጠሩ ያዲሳባ ወጣቶች ባልሰሩት ወንጀል አንድ ወር በነዚሁ ቀይ መለዮ ለባሽ ኃይሎች ይታሻሉ ስልጠና የሚያስፈልገው የፖሊስ ኮሚሽነሩ ነው» ብሏል።

ገረመው ይልማ ደግሞ፦ «ከነትጥቁ ቤተመንግስት የሄደ ...መብት ጠያቂ! ባዶ እጁን ብሶቱን ለመናገር አደባባይ የወጣ የአዲስ አበባ ሰው ...አደገኛ ቦዘኔና ወሮ በላ!! ድንቄም መብት!!» ሲል ተችቷል።

«የደህንነት መስሪያ ቤቱ ኃላፊና የሻለቃዎቹ አመራር ማን ናቸው? የወታደሮቹ ጥያቄ እንዴት ቀድሞ አልተሰማም? መቼም ባንድ ማታ ተሰባስበው ቤተመንግስት ለመሄድ የወሰኑ አይመስለኝም። የሆነ የሚሸት ነገርማ አለ፥ ጉዳዪ በደንብ ይጣራ» ሲል የጠየቀው አዛርኪያ አባዲ ነው።

አሸናፊ ካሳሁን ኢዶሳ «በ"ፑሽ-አፕ" ቢያለባብሱ በሌላ መግለጫ ይመለሱ» ሲል በአጭሩ ጽፏል። 

ሌላው በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች በርካቶችን ያነጋገረው ጉዳይ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ትጥቅ ያለመፍታት ጉዳይ ነው። «ኦነግ ትጥቅ እንዲፈታ ማስጠንቀቂያ ተሰጠው» የሚል ርእስ የያዙ በርካታ መልእክቶች በስፋት ተሰራጭተዋል።

ከጠቅላይ ሚንሥትሩ ንግግር ባሻገርም የኦነግ ሊቀመንበር ንግግር በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ላይ በርካቶች ተቀባብለውታል። ኦነግ «ትጥቁን እንደማይፈታ ሊቀ መንበሩ አቶ ዳውድ ኢብሳ ማምሻውን አስረግጠው ተናግረዋል» ያለው ናሁሰናይ በላይ፦ «ኦነግ የፈለገው ነገር ቢያደርግ መንግስት ደፍሮ እንደማይከሰው ያውቃል፡፡ ዛሬ አይደለም ሃገሪትዋን ቤተ መንግስትህንም መጠበቅ አትችልም የሚል አደገኛ መልእክት ተላልፏል፡፡ በወታደራዊ ፍርድ ቤት የሚያስጠይቅ ወንጀል በአብሽር አብሽር የፑሽአፕ ምት መታለፉ የጨዋታውን ባለቤትና የድርጊቱ ሰለባ ተልፈስፋሽነት ለመለየት ይጠቅመናል፡፡ ድራማው ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ ያለ ምክንያትና ያለ ዋና ባለቤት የሚሆን አንዳች ነገር የለም» ሲል ጽፏል።

ጋዜጠኛ አርጋው አሽኔ፦ «ኦነግ የወታደሮቹን ትጥቅ ላለማስፈታት አሻፈረኝ ካለ በኋላ ግንባሩ እና የኢትዮጵያ መንግሥት ወደ ወታደራዊ ፍጥጫ እያመሩ ነው። በውይይት ካልተፈታ በጠቅላይ ሚንሥትር ዐቢይ የለውጥ አጀንዳ ብርቱው የደህንነት ማሽቆልቆል ይኾናል» በማለት ትዊተር ላይ በእንግሊዝኛ ጽፏል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አርያም ተክሌ