1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ሳይንስ

ተንቀሳቃሽ ስልክ ያላቸው ገበሬዎች የተሻለ ያመርታሉ - ጥናት  

ረቡዕ፣ ሐምሌ 18 2010

የኢትዮጵያ መንግስት የኢትዮ-ቴሌኮምን የተወሰነ ድርሻ ለባለሀብቶች ለማስተላለፍ ውሳኔ ማሳለፉ ይታወሳል። በኢትዮጵያ ለአርሶ አደሩ ሌላው ቢቀር መደበኛ የተንቀሳቃሽ ስልክ አገልግሎት ቢዳረስ በግብርና ምርት ላይ ለውጥ እንደሚታይ ጥናቶች ያሳያሉ። በስንዴ አምራቾች ላይ የተደረገ ጥናት አገልግሎቱን የሚጠቀሙቱ ከፍ ያለ ምርት እንደሚያገኙ አመላክቷል።

https://p.dw.com/p/323fc
Uganda  ITEL Feature Phone
ምስል DW/S. Leidel

ተንቀሳቃሽ ስልክ ለኢትዮጵያውያን ገበሬዎች ምርታማነት ያለው አስተዋጽኦ

የኢትዮጵያ ገዢ ፓርቲ ኢህአዴግ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ባለፈው ግንቦት ወር መጨረሻ ባደረገው ስብሰባ ያሳለፋቸው ውሳኔዎች ያልተጠበቁ የፖሊሲ አቅጣጫዎች የታዩበት ነበር። አነጋጋሪ ከነበሩት ውሳኔዎቹ መካከል መንግስት የሚቆጣጠራቸዉ  እንደአየር መንገድ እና ኢትዮ-ቴሌኮም ያሉ ተቋማትን የአክሲዮን ድርሻ ለግል ድርጅቶች ለመሸጥ መታቀዱ ይገኝበታል። በህዝብ ዘንድ ብዥታ ፈጥሮ የነበረው ይህ ውሳኔ በተወካዮች ምክር ቤት አባላትም ዘንድ ተንጸባርቋል። የምክር ቤት አባላቱ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ እንዲያቀርቡ ባለፈው ወር በጠሯቸው ወቅት የተቋማቱ ጉዳይ ተነስቷል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ የቴሌኮሚዩኒኬሽን አገልግሎትን አስመልክቶ ለምክር ቤት አባላት እንዲህ ብለው ነበር።

“ቴሌኮምዩኒኬሽንን ብንመለከት ቴሌኮምዩኒኬሽን በ21ኛው ክፍለዘመን የሚፈለገው  የሞባይል ስልክ እንዲያበራክት ብቻ አይደለም። የሞባይል ስልክ መብዛት አንዱ ውጤት እንጂ አጠቃላይ ውጤት አይደለም። ዋናው ከቴሌኮም ኢንዱስትሪ የሚፈለገውኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂን ማሳደግ ነው። ምን ማለት ነው? የጤና ስርዓት፣ የትምህርት ስርዓት፣ የመንግስት e-governance፣ የገቢ ስርዓት automate ማድረግ፤ ህዝቡ የሚያማርርበትን አገልግሎት የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂን ተጠቅሞ ማሻሻል እና ማሳለጥ መቻል ነው። ከዚህ አንጻር የት ጋር እንዳለን ለዚህ የተከበረው ምክር ቤት መግለጽ ያለብኝ አይመስለኝም። ከፍተኛ ስራ የሚፈልግ አካባቢ ስለሆነ” ሲሉ ለተወካዮች ምክር ቤት አባላት ነግረዋቸዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ ማብራሪያቸው ኢትዮጵያ ውስጥ በአሁኑ ወቅት ከ1,000 እስከ 1,200 ሰዎች በየቀኑ አዳዲስ ሲም ካርድ እንደሚጠይቁ ጠቅሰዋል። ከእነዚህ ውስጥ በገጠሪቱ የኢትዮጵያ ክፍል ያሉ አርሶ አደሮች ቁጥር የማይናቅ እንደሆነ ጥናቶች ያሳያሉ። ለእነዚህ አርሶ አደሮች ጠቅላይ ሚኒስትሩ የዘረዘሯቸው ዘመናዊ የቴሌኮሚዩኒኬሽን አገልግሎቶች «ጽድቁ ቀርቶ በወጉ በኮነነኝ» አይነቶች መሆናቸውን ያመለክታሉ። መደበኛውን የተንቀሳቃሽ ስልክ አገልግሎት እንኳ በቅጡ ማግኘት ቢችሉ በግብርና ህይወታቸው ላይ ለውጥ እንደሚያመጡ በቁጥር እና ዝርዝር መረጃ አስደግፈው ያሳያሉ።

Äthiopien Premierminister Abiy Ahmed
ምስል picture-alliance/AA/M.W. Hailu

በኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ተመራማሪ የሆኑት አቶ ካሌብ ቀለሙ ለጉዳዩ ሁነኛ ጥናት ያካሄዱ ባለሙያ ናቸው። የዛሬ ሁለት ዓመት ገደማ በእውቅ የሳይንስ ጆርናሎች ላይ ያሳተሙት ጥናት የተንቀሳቃሽ ስልክ በስንዴ አምራቾች ላይ ያመጣውን በጎ ተጽእኖ የፈተሸ ነው። ጥናቱ በአማራ፣ ኦሮሚያ፣ ትግራይ እና ደቡብ ክልሎች ውስጥ ዋና ስንዴ አብቃይ የሚባሉ አካባቢዎችን አካልሏል። ከሁለት ሺህ የሚልቁ ገበሬዎችን ያሳተፈው ይህ ጥናት ማጠንጠኛው ምን እንደነበር ተማራማሪው ያብራራሉ።

“የጥናቱ መነሻ hypothesis ምንድነው? ሞባይል የሚጠቀሙ አርሶ አደሮች ከማይጠቀሙ ሞባይል ከሌላቸው አርሶ አደሮች አንጻር በአሰራር ውጤታማነት (technical efficiency) ልዩነት ይኖራል ወይ? [የሚል ነው]።  የTechnical efficiency ማለት አርሶ አደሩ የግብዓት አጠቃቀሙን ይበልጥ ውጤታማ አድርጎ ከፍተኛ ምርት ማምረት የሚችልበትን ሁኔታ የሚዳስስ ጥናት ነው ማለት ነው። ይህ ማለት የተቻለውን ያህል ከፍ ያለ የስንዴ ምርት በአንድ ሄክታር ላይ ማግኘት ማለት ነው። እና ሞባይል የሚጠቀሙ አርሶ አደሮች በሚገባ የሚታይ የአሰራር ውጤታማነት ልዩነት እንዳለ ያው የስታትስቲክስ ትንተና ውጤቱ ያሳያል።

ያ ምን ማለት ነው? አንድ ገበሬ ሞባይል አለው። ሞባይል ማግኘት እና መጠቀም መቻሉ የተለያዩ የመረጃ ውጤቶችን መለየት መቻል እና መጠቀም ይችላል ማለት ነው። ለምሳሌ ከልማት ጣቢያ ሰራተኛ ጋር በየጊዜው መነጋገር ይችላል። ከነጋዴዎች ጋር ግንኙነት ሊኖረው ይችላል። ሌላ አካባቢ ካሉ አርሶ አደሮች ጋር መረጃ ሊለዋወጥ ይችላል። ዋናው ትንታኔው ግብዓት ሊያገኝ የሚችልበት ትክክለኛውን ወቅት፣ ዋጋ እንደዚህ አይነት ነገሮችን በቀላሉ ሊያገኝ የሚችልበት ዕድል ይፈጥርለታል ነው። ዝም ብለን ስታቲክሱን ስንሰራው እና ሞባይል ያላቸው አርሶ አደሮች ከሌላቸው ላይ በግልጽ ይህ ልዩነት ታየ” ይላሉ አቶ ካሌብ።       

ተመራማሪው  የተጠቀሙበት መረጃ የተሰበሰበው ከ26 ዞኖች ከተውጣጡ አርሶ አደሮች ነው። የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ከዓለም አቀፉ ስንዴ እና በቆሎ ተቋም ጋር በመተባበር የሰበሰቡትን ይህን መረጃ አቶ ካሌብ በራሳቸው የትንተና ማዕቀፍ በዝርዝር አጥንተውታል። በ61 የተለያዩ ወረዳዎች ውስጥ ባሉ 122 ቀበሌዎች ውስጥ በሚኖሩ አርሶ አደሮች መካከል የታየው ልዩነት በእርግጥም ተንቀሳቃሽ ስልክ ከመጠቀም እና ካለመጠቀም ጋር የተያያዘ መሆኑ በምን ተፈተሸ?  አቶ ካሌብ ይመልሳሉ።  “አሁን እዚያ ላይ የተጠቀምነው  የትንተና ሞዴል ምንድነው የሚያደርገው? እነዚህ ሁለት የገበሬዎች ቡድን፤ ሞባይል ያላቸው እና የሌላቸውን ገበሬዎች፤  technical efficiency ላይ ተጽእዕኖ የሚያደርጉ ሌሎች ተመሳሳይ ምክንያቶች ያሏቸውን አርሶ አደሮች ነው የሚያወዳድረው። አንዱ ሞባይል አለው፤ አንዱ ደግሞ የለውም። ስለዚህ ምን ሆነ ማለት ነው? የእዚህ የtechnical efficiency ልዩነት የመጣው በሞባይል ምክንያት ነው ማለት ነው። በእኔ እና በአንተ መካከል technical efficiency ላይ ተጽእኖ የሚያሳድሩ ነገሮች አንድ አይነት ሆነው ማለት ነው።

Äthiopien Windpark
ምስል Getty Images/AFP/J. Vaughn

[ተጽእኖ የሚያሳድሩ ሌሎች ምክንያቶች የሚባሉት] ለምሳሌ ከልማት ሰራተኛ ጋር ያለ ግንኙነት መጠን፣ ሌሎች ከአካባቢህ ውጭ ያሉ የዘመዶችህ ብዛት፣ የምታውቃቸው የነጋዴዎች ቁጥር ብዛት፣ ቴሌቪዥን ወይም ሬድዩ አለህ ወይስ የለህም? የሚሉት ናቸው። እነዚህ ነገሮች በሙሉ የመረጃ ምንጮችናቸው። በእነዚህ መለኪያዎች እኔ አንተ ተመሳሳይ ነን ማለት ነው። አሁን ከእነዚህ ከሁለት ሺህ አርሶ አደሮች ውስጥ ሶፍትዌሩ ሁለት ተመሳሳይ የሆኑ ገበሬዎችን ያወጣልኛል። ሁለቱ ያወጣልኝን ገበሬዎች control እና treatement ቡድን ብሎ ለማነጻጸር ይለይልኛል። እነዚህ ሞባይል ያላቸው እና የሌላቸው ማለት ነው። ስለዚህ technical efficiency ላይ ተጽዕኖ በሚያደርጉ ምክንያቶች በሙሉ ተመሳሳይ የሆኑ ቡድኖች ፈጠረልኝ። እነዚህ ቡድኖች የሚለያዩበት አንድ ነገር ምንድነው? ሞባይል አላቸው ወይስ የላቸውም የሚለው ብቻ ነው።”

በጥናቱ ለሁለት የተከፈሉት አርሶአደሮች የማዳበሪያ፣ የምርጥ ዘር፣ የጸረ-አረም ተመሳሳይ ግብዐት ቢጠቀሙም አዝመራ ሲሰበስቡ ግን ተንቀሳቃሽ ስልክ የሚጠቀሙቱ በሄክታር የሚያገኙት ምርት የተሻለ ሆኖ ተገኝቷል። “ይህ ልዩነት ሊከሰት የቻለው” ይላሉ አቶ ካሌብ “ተንቀሳቃሽ ስልክ ያላቸው አርሶ አደሮች የአሰራር ውጤታማነታቸውን የተሻለ ለማድረግ በመረጃ ላይ የተመሰረተ የግብዓት አጠቃቀም በመከተላቸው ነው።”

Symbolbild Smartphone & Kommunikation in Afrika
ምስል picture-alliance/Robert Harding World Imagery

እኚህኛዎቹ አርሶ አደሮች በሚያገኙት መረጃ ላይ ተመርኩዘው የዘር መዝሪያ ጊዜያቸውን ከፍ ወይም ዝቅ ማድረጋቸው ለልዩነቱ መከሰት አንዱ ምክንያት እንደሆነ ተመራማሪው ያስረዳሉ። ግብዓት በወቅቱ አምጥቶ መጠቀም መቻላቸው፣ የማዳበሪያ አጠቃቀማቸውን በምክር ላይ ተመስርተው ማድረጋቸው ሌላኛው ምክንያት ነው ይላሉ። እኒህ ቀላል የሚመስሉ የመረጃ ልውውጦች እና ምክሮች በአርሶ አደሮቹ የምርት መጠን ላይ ቀጥተኛ ተጽዕኖ እንዳላቸው ጥናታቸውን ጠቅሰው አቶ ካሌብ ያብራራሉ።      

“በነገራችን ላይ እነዚህ የሞባይል ተደራሽነት ያላቸው አርሶ አደሮች ራሱን ሞባይሉን ተከታትለው፣ አግኝተው፣ ገዝተው ለመጠቀም የሚፈልጉበት ምክንያት ዘመድን ለመጠየቅ ወይም ለማህበራዊ ጉዳይ ብቻ አይደለም። ዋና መሳሪያ አድርገው የሚጠቀሙበት የአርሶ አደሩ መሰረት የሆነውን የግብርና ስራ በተቀላጠፈ ሁኔታ ለመተግበር እንዲያስችላቸው ነው። ገበሬ ሁልጊዜ ስራዎቹን ሲሰራ ሁሌ መረጃ ላይ ይመረኮዛል። መረጃ ይጠይቃል። የዘር ወቅቱ ከመድረሱ በፊት በትክክል ግብዓቱን እንዴት እንደሚያገኝ ይጠይቃል። ደውሎ ግብዓቱን በጊዜ መጥቼ ልውሰድ ወይ ላክልኝ ይላል። ዘር እጁ ላይ ከሌለ ቀጥሎ ካለው አርሶ አደር ደውሎ ‘እባክህ እጅህ ላይ ያለ ዘር ካለ ላክልኝ’ ብሎ ቶሎ አስመጥቶ ይጠቀማል።

በተለይ የእርሻ ጊዜ በሚደርስበት ወቅት በሞባይል ያለህበት ቦታ ሆነህ  ብዙ ነገር ማስተካከል ትችላለህ።  ሞባይል ባይኖርህ ግን ምንድነው የምታደርገው? በእግርህ መንቀሳቀስ ይኖርብሃል፤ ሩቅ ቦታ ሄደህ እዚያ አግኝተህ እስክትመጣ ድረስ ብዙ ክንውኖች ሊያልፉህ ይችላሉ። ብዙ ነገሮች አሉ። እና የሞባይል ስልክ መስፋፋት  በቀጥታ አጠቃላይ የግብርና ልማቱን ለማሳደግ ትልቅ ሚና እንዳለው በግልጽ የሚያመለክት ነው” ሲሉ አቶ ካሌብ አጽንኦት ይሰጣሉ።

Mobile Telefon von King ok558
ምስል Tesfalem Waldyes Erago

የኢትዮጵያ መንግስት የቴሌኮምንኬሽንን አገልግሎት በራሱ ይዞታ ለማቆየት በዋና ምክንያትነት ከሚጠቅሳቸው መከራከሪያዎች አንዱ አገልግሎቱን ለአርሶ አደሩ ለማዳረስ በሚል ነው። አገልግሎቱን ለማስፋፋት ከጎርጎሮሳዊው 2000 ዓ. ም. ወዲህ ባለው አስር ዓመት ብቻ 15 ቢሊዮን ዶላር ወጪ ማድረጉን መረጃዎች ያሳያሉ። ብቸኛው የአገልግሎቱ አቅራቢ ኢትዮቴሌኮም ባለፈው ግንቦት ወር በሰጠው መግለጫ የሞባይል ተጠቃሚዎቹ ቁጥር 66 ሚሊዮን መሻገሩን ገልጿል።

መንግስት ለዘርፉ የሚያወጣው ወጪ በየጊዜው እያሻቀበ ቢመጣም እና የየተንቀሳቃሽ ስልክ ተጠቃሚዎችን ቁጥር በከፍተኛ መጠን አሳድጌያለሁ ቢልም  ትኩረት አድርግበታለሁ በሚለው በአርሶ አደሩ ዘንድ አገልግሎቱ ያመጣውን ተጨባጭ ለውጥ በጥናት ሲፈትሽ አይስተዋልም። እንደ አቶ ካሌብ ያሉ ተመራማሪዎች የካሄዷቸው በጣት የሚቆጠሩ ጥናቶችም የሚገባዉን ትኩረት ያገኙ አይመስሉም። የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩቱ ተመራማሪ ጥናታቸውን ለፖሊሲ ቀረጻ ግብዓትነትም ሆነ ለሌላ ጥቅም ፈልጎ ያነጋገራቸው አካል እንደሌለ ይናገራሉ።

ተስፋለም ወልደየስ 

ነጋሽ መሐመድ