1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ሳይንስ

በሶስት ዓመት ለተጠቃሚዎች ይደርሳል ተብሏል 

ረቡዕ፣ ጳጉሜን 1 2009

በዓለም ላይ ለሚሊዮኖች ህልፈተ ሕይወት ምክንያት ከሆኑ በሽታዎች አንዱ ወባ ነው፡፡ የጀርመኑ ቱቢንገን ዩኒቨርስቲ ተመራማሪዎች ወባን ለመዋጋት ለሚደረገው ጥረት ተስፋን የፈነጠቀ አዲስ ዜና ይዘው መጥተዋል፡፡ በሙከራ ደረጃ የሚገኘው ምርምራቸው ለወባ የሚሆን ክትባት እና አዲስ መድኃኒት ለማስገኘት ጫፍ ደርሷል ተብሏል፡፡

https://p.dw.com/p/2jSht
Mosquito Mücke
ምስል picture-alliance/AP Photo/J. Miller

መድኃኒቱ በ3 ዓመት ለተጠቃሚዎች ይደርሳል ተብሏል 

በደቡብ ጀርመን የምትገኘው ቱቢንገን ለክፍለ ዘመናት በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መናኸሪያነቷ ትታወቃለች፡፡ ስሟን የተዋሰው የቱቢንገን ዩኒቨርስቲ እንኳን ከተመሠረተ ስምንት ክፍለ ዘመናትን ተሻግሯል፡፡ በአውሮጳ ካሉ፣ አንቱታን ካተረፉ የምርምር ዩኒቨርስቲዎች አንዱ የሆነው የቱቢንገን ዩኒቨርስቲ 400 ፕሮፌሰሮች እና ሁለት ሺህ ገደማ የአካዳሚክ ሠራተኞች አሉት፡፡ መቶ ዓመቱን ባለፈው ሰኔ የደፈነው የዩኒቨርስቲው የሞቃታማ አካባቢዎች መድኃኒት ተቋም ትኩረቱን በተላላፊ በሽታዎች ላይ አድርጎ ምርምር ያደርጋል፡፡  

የዩኒቨርስቲው የህክምና ትምህርት ክፍል አካል የሆነው ይሄው የምርምር ተቋም በወባ ላይ በሚያደርገው ምርምር ተደጋግሞ ስሙ ይነሳል፡፡ የምርምር ተቋሙ በአፍሪካ ዋና ገዳይ በሽታዎች ከሚባሉት ውስጥ የሚመደበውን ወባ ለማጥፋት ከጋቦን እስከ ኮንጎ፣ ከቤኒን እስከ ቶጎ ካሉ ተቋማት ጋር በትብብር ይሠራል፡፡ ተቋሙ ወባን በተመለከተ ለዓመታት የደከመበት ምርምር ዕውቅና አግኝቶ በታዋቂው “ኔቸር” የሳይንስ መጽሔት (ጆርናል) ላይ የታተመው ባለፈው የካቲት ወር ነበር፡፡ 

Tübingen Institut für Tropenmedizin Peter Kremser
ምስል picture-alliance/dpa/Michael Latz

የምርምሩ ዋና አላማ በተለያዩ ተመራማሪዎች ተደጋጋሚ ሙከራ ሲደረግበት የቆየው ለወባ በሽታ ክትባት ማስገኘት ነው፡፡ ተቋሙ ምርምሩን ሲያካሄድ የቆየው ከዚህ በፊት በወባ በሽታ ባልተጠቁ 67 ሰዎች ላይ ነበር፡፡ ተመራማሪዎቹ ለክትባት ያሰቡትን መድኃኒት ለእነዚህ ሰዎች በየጊዜው በመስጠት ውጤታቸውን ሲከታተሉ ቆይተዋል፡፡ ከሰዎቹ ውስጥ በሽታውን የመቋቋም አቅም በከፍተኛ ሁኔታ ያሳዩት ክትባቱን በየአራት ሳምንት ልዩነት ለሦስት ጊዜያት ሲወስዱ የነበሩ ዘጠኝ ሰዎች ነበሩ፡፡ 

ፒተር ክሬምስነር በቱቢንገን ዩኒቨርስቲ የሞቃታማ አካባቢዎች መድኃኒት ተቋም ዳይሬክተር ናቸው፡፡ የመጀመሪያው የክትባት ሙከራ ያመጣውን  ውጤት እንዲህ ያስረዳሉ፡፡ “ጥናት ስናደርግ ነበር የቆየነው፡፡ ሰዎችን ከወባ ለመከላከል በመከተብ ረገድ አዲስ አቅጣጫ ነው የተከተልነው፡፡ ሁለቱም ውጤታማ ሆነዋል፡፡ ውጤታማ ሆነ ስንል ከፍተኛ የክትባት መጠን ከሰጠናቸው ዘጠኝ ሰዎች ዘጠኙም ከበሽታው ተጠብቀዋል” ይላሉ  ክሬምስነር፡፡ 

ዳይሬክተሩ ይህን የተናገሩት የተቋማቸው የምርምር ውጤት በሳይንስ መጽሔት ላይ መታተሙን ምክንያት በማድረግ ነበር፡፡ ከሰባት ወር በኋላ ምርምሩ ቀጥሎ የደረሱበትን ውጤት ደግሞ በዚህ ሳምንት ለዶይቸ ቬለ አጋርተዋል፡፡ “የሙከራችን ሁለተኛ ምዕራፍ የመድኃኒቱን የመከላከል አቅም ለመጀመሪያ ጊዜ አሳይቶናል፡፡ አሁን በርካታ ቁጥር ያለውን በሽተኛ አሊያም በጎ ፍቃደኛ በመጠቀም ሶስተኛ ምዕራፍ ማካሄድ ይገባናል፡፡ ምክንያቱም ይህንን እየሞከርን ያለነው በጤናማ ግለሰቦች ላይ ነው፡፡ መድኃኒቱ አደጋ የማያስከትል፣ በአግባቡ የሚቀበሉት አይነት እና በትልቅ መጠን ውጤታማ መሆኑን ለማሳየት ተስፋ አለን፡፡ አሁን ያለውም እንደዚያ ይመስላል” ብለዋል ዳይሬክተሩ፡፡ 

በአዲስ መድኃኒት የሙከራ ሂደት ውስጥ ውጤታማነቱን ማስመስከር መቻል ወሳኝ እንደሆነ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡ በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የበሽታዎች መከላከል እና መቆጣጠር ዳይሬክቶሬት የወባ ማስወገድ አስተባባሪ አቶ ደረጀ ድሉ አስተያየትም ተመሳሳይ ነዉ፡፡ የቱቢንገን ዩኒቨርስቲ አይነት ሙከራዎች በተለያዩ ቦታዎች በየጊዜው እንደሚካሄዱ የሚገልጹት አቶ ደረጀ ብዙዎቹ በመከላከል አቅም ሲመዘኑ አነስተኛ ውጤት እንደሚያስመዘግቡ ይናገራሉ፡፡ 

Universität Tübingen
ምስል picture-alliance/dpa

“በዓለም አቀፍ ደረጃ ብዙ ነገሮች እንሰማለን፡፡ ከክትባት ጀምሮ ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ ክትባት ሙከራ ላይ እንደሆነ እንሰማለን ግን እስካሁን የመከላከል አቅሙ 50 በመቶ አላለፈም፡፡ አሁን ሶስት የአፍሪካ ሀገሮች ላይ የሙከራ ስራ እንደሚሰራ አውቃለሁ፡፡ እንደ ዛምቢያ እና ጋና እንዲዘህ ትልልቅ ስራዎች፣ የክትባት ሙከራ እየተካሄደ ነው፡፡ ግን አሁንም መድረስ የሚገባቸውን አቅም እየደረሱ አይደለም ተብሎ ነው የሚታሰበው፡፡ ወባን ለማስወገድ ትልቅ ታሳቢ ያደረግነው እና ተስፋ ሰጪ ነው ብለን የምናስበው አንድ ዕድል የመድኃኒቶች ረጅም ጊዜ የመቆየት አቅም (long acting drugs) ያላቸው መድኃኒቶች በአለም አቀፍ ደረጃ በፈጠራ እየመጡ ነው እና እነዚህ ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖራቸዋል የሚል እምነት ነው ያለኝ” ብለዋል፡፡

አቶ ደረጀ ከተወሰደ በኋላ አርባ አምስት ቀን ደም ውስጥ የሚቆይ አዲስ የወባን መድኃኒት በምሳሌነት ያነሳሉ፡፡ ይህ መድኃኒት ወባን ለ45 ቀናት እንደመከላከያ ሆኖ እንደሚያገለግልም ያስረዳሉ፡፡ እንደዚህ አይነት መድኃኒቶች የወባ ስርጭትን በመገደብ ትልቅ ሚና ይኖራቸዋል የሚል እምነትም አላቸው፡፡ በቱቢንገን ዩኒቨርስቲ ተቋም በሙከራ ያለው አዲሱ የወባ ክትባት የመከላከል አቅሙ እስካሁን ያለው ውጤት መቶ በመቶ ነው መባሉ “እጅግ ተስፋ ሰጪ ነው” ይላሉ፡፡ የዩኒቨርስቲው ተቋም ዳይሬክተርም ተመሳሳይ ተስፋ ይታያቸዋል፡፡ 

“ይህ መድኃኒት በትልቅ መጠን ተሞክሮ ውጤታማ ከሆነ  ለአጭር ጊዜ ጎብኚዎች በሽታውን በመከላከያነት ማገልገል ይችላል፡፡ ወባ በተስፋፋባቸው በሞቃታማ አካባቢዎች ለበርካታ ወራት ለሚደረግ ቆይታም ጠቃሚ ሊሆኑ ይችላል፡፡ ለወባ በሽተኞች ተጨማሪ ማከሚያ መሳሪያ ሊሆንም ይችላል፡፡ በበሽታው የሆነ ምዕራፍ ላይ ለበሽተኞች ሊሰጥ ይችላል” ይላሉ ክሬምስነር፡፡ 

ኢትዮጵያን ጨምሮ በርካታ የአፍሪካ ሃገራት በሞቃታማ የምድር አካባቢ እንደመገኘታቸው ለወባ በሽታ መጋለጣቸው እሙን ነው፡፡ የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ እንደሚያሳየው በ95 ሃገራት የሚገኙ 3.2 ቢሊዮን ሰዎች በወባ በሽታ የመጠቃት አደጋ ተደቅኖባቸዋል፡፡ በጎርጎሮሳዊው 2015 ብቻ በዓለም አቀፍ ደረጃ 214 ሚሊዮን ሰዎች በወባ በሽታ መያዛቸውን መረጃው ያመለክታል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ 438 ሺህ በወባ ምክንያት ሕይወታቸውን አጥተዋል፡፡ ከሟቾቹ ውስጥ 90 በመቶው በአፍሪካ አህጉር መገኘታቸው በሽታው ምን ያህል  የአህጉሩ ራስ ምታት እንደሆነ ያሳያል፡፡

2016_12_13_Karte_Welt-Malaria-Bericht_EN

በኢትዮጵያ ከአራት አመት በፊት የነበረው የወባ በሽታ ህሙማን ቁጥር 3.3 ሚሊዮን ነበር፡፡ ወባን ለመከላከል በኢትዮጵያ መንግሥት እና አጋሮቹ በተደረገ ርብርብ ባለፈው የጎርጎሮሳዊው 2016 ዓመት ቁጥሩ ወደ 1.8 ሚሊዮን መውረዱን  በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የወባ መስወገድ አስተባባሪው አቶ ደረጀ ይናገራሉ፡፡ ኢትዮጵያ የወባ በሽታን  በጎርጎሮሳዊው 2030 ለማጥፋት አልማ እየተንቀሳቀሰች እንደሆነ የሚናገሩት አቶ ደረጀ ሀገሪቱ የራሷን ፍኖተ ካርታ ማዘጋጀቷንም ያስረዳሉ፡፡ የጀርመን ዩኒቨርስቲው አይነት የምርምር ውጤቶች በፍኖተ ካርታው ተገቢውን ቦታ እንደተሰጣቸውም አመልክተዋል፡፡

“ይሄን ወባን ማጥፋት በተመለከተ በምዕራፍ በምዕራፍ የተከፋፈለ ነው፡፡ በመጀመሪያው መዕራፍ በስድስት ክልሎች፣ 18 ዞኖች፣ 239 ወረዳዎች ናቸው የተመረጡት፡፡ እነዚህ  ታሳቢ ያደረገ በየክልሉ ይፋዊ የማስጀመር ስራ ተካሄዷል፡፡ በሀገር አቀፍ ደረጃም ይፋዊ የማስጀምር ስራው በአዳማ ከተማ በየካቲት ወር ይፋ ተደርጓል፡፡ በዚህ ፍኖተ ካርታ ትልቅ ትኩረት የተሰጠው አሁን በአለም ደረጃ ያሉ ዕድሎችን መጠቀም ነው፡፡  ዕድሎች ስንል በምርምር፣ በፈጠራ ሊሆን ይችላል፡፡ አሁን ትልልቅ ጥናቶች በኬሚካልም፣ በመድኃኒቱም፣ በመመርመሪያ መሳሪያዎችም እየተደረጉ ነው፡፡ እነዚህ ጥናቶችን በእኛ ሀገር ሁኔታ እንዲዋሃዱ አድርጎ መቀበል የስልታዊ አካሄዳችን አካል ነው፡፡ ስለዚህ እንደዚህ አይነት ጥናቶች ትልቅ ዋጋ አላቸው ምክንያቱም 14 ዓመት ሊወስድብን የሚችለውን የወባን ማስወገድ ጉዞ ምናልባትም በአጭር ጊዜ ውስጥ ለማሳካት ይረዱናል፡፡ እንደዚህ አይነት ጥናቶች ፋይዳቸው ቀላል የሚባል አይደለም” ይላሉ አቶ ደረጀ፡፡

በሙከራ ደረጃ ያለው የቱቢንገን ዩኒቨርስቲ የወባ ክትባት ተጠቃሚዎች ዘንድ ለመድረስ ቢያንስ ከዚህ በኋላ ሦስት ዓመት እንደሚወስድ ተመራማሪዎች ጠቁመዋል፡፡ በኢትዮጵያ ተገቢውን ማረጋገጫ እስኪያገኝ ደግሞ ቢያንስ አንድ ዓመት እንደሚወስድ ባለሙያዎች ያስረዳሉ፡፡ አዲስ ነገር ማምጣት የማይታክታቸው ተመራማሪዎች እስከዚያው ሌላ መድኃኒት ይዘው ይመጡ ይሆን?፡፡ ተስፋ ሰንቆ መጠበቅ ነው፡፡   

 

ተስፋለም ወልደየስ 

ሸዋዬ ለገሠ