1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ስጋት በኢትዮጵያ

ማክሰኞ፣ መስከረም 23 2010

ኢትዮጵያን ጨምሮ 8 የአፍሪካ ሀገራት እንደ ካንሰር፣ ልብና ስኳርን በመሳሰሉ ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች በርካታ ሰዎች ከሚታመሙባቸዉ ሀገራት ተርታ እንደሚገኙ አንድ ጥናት አመለከተ። «ክሊኒክ ኮምፔር» የተባለ ድርጅት ከሰሞኑ ይፋ ባደረገዉ ጥናት ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን  በተመለከተ የዓለም ሀገራት ያሉበትን የስጋት ደረጃ አመላክቷል።    

https://p.dw.com/p/2l9yv
Karte Ethiopia und Eritrea ENG

Non-communicable disease threat in Ethiopia - MP3-Stereo

«ክሊኒክ ኮምፔር»  የስጋት ደረጃዎችን «በከፍተኛ ደረጃ የጤና ችግር ያለባቸዉ» እና «የጤና ችግር ያለባቸዉ» በሚል በሁለት ደረጃ አስቀምጧል።  ስድሳ በመቶ የሚሆነዉን የሞት መጠን ይይዛሉ የተባሉትን እነዚህን በሽታዎች ለመቀነስ መንግስታት ትኩረት ሰጥተዉ ሊሰሩ እንደሚገባም  ድርጅቱ አሳስቧል።

የካንሰር፣ የልብና ስኳርን የመሳሰሉ ተላላፊ  ያልሆኑ በሽታዎች  በገዳይነታቸዉ ግንባር ቀደም ከሚባሉት በሽታዎች ዉስጥ እንደሚመመደቡ የዘርፉ ባለሙያዎች ይገልጻሉ። እነዚህ በሽታዎች በዓለም ዙሪያ ከ 36 ሚሊዮን በላይ ሰዎችን በየዓመቱ ለህልፈተ ህይወት እንደሚያበቁ መረጃዎች ያመለክታሉ። ጤነኛ ያልሆነ አመጋገብ፣ የአኗኗር ዘይቤዎች፣ ሲጋራ ማጨስ፣ አልኮል መጠጣት፣ በቂ የአካል እንቅስቃሴ አለማድረግ ለእነዚህ በሽታዎች መንስዔ ተደርገዉ ይጠቀሳሉ። በዚህም የተነሳ በሽታዎቹ በዓለም ዓቀፍም ይሁን በሀገር ዓቀፍ ደረጃ ልዩ ትኩረት የሚፈልጉ ናቸዉ።  በአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ የጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የዉስጥ ደዌ ሀኪምና የዓለም ዓቀፍ የስኳር ህመምተኞች ፌደሬሽን የአፍሪቃ ሪጅን ሊቀመንበር ዶክተር አህመድ ረጃ።

ይሁን እንጅ ሀገራት  በሽታዎቹን ለመቆጣጠርና ለመከላከል የሚያደርጉት ጥረት የአሳሳቢነታቸዉን ያህል እንዳልሆነ  የዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት በምህጻሩ WHO በቅርቡ ባወጣዉ ዘገባ አመልክቷል። «ክሊኒክ ኮምፔር» የተባለ ለንደን የሚገኝ የጤና ተቋምም፤ ከዓለም ዓቀፉ የጤና ድርጅት WHO፣ ከአሜሪካዉ ማዕከላዊ የስለላ ድርጅት CIA እና ከዓለም ዓቀፍ የሳንባ ጤና ድርጅት አገኘሁት ባለዉ መረጃ መሰረት፤ የዓለም ሀገራት ከበሽታዎቹ  ጋር ተያይዞ  ያሉበትን የስጋት ደረጃ ከሰሞኑ ይፋ አድርጓል። በዚህም መሰረት ከፍተኛ የጤና ችግር ያለባቸዉና የጤና ችግር ያለባቸዉ በሚል በሁለት  ምድብ አስር አስር ሀገሮችን በቀዳሚነት አስቀምጧል።

በመጀመሪያዉ ምድብ ማለትም ከፍተኛ የጤና ችግር  ያለባቸዉ 10 ሀገራት የተካተቱ ሲሆን  ሲጋራ በማጨስ ና አልኮል በመጠጣት  ቼክንና ስሎቫኪያን የመሳሰሉ በአብዛኛዉ የምስራቅ አዉሮፓ ሀገራት  በዚህ ዝርዝር ተቀምጠዋል።  ዩኤስ አሜሪካ  ከልክ ባለፈ ዉፍረት የተነሳ 35 በመቶ የሚሆኑት  ዜጎቿ  ጤንነታቸዉ ስጋት ላይ ነዉ በሚል  በዚህ ምድብ ዉስጥ የተካተተች  ብቸኛዋ አዉሮፓዊ ያልሆነች ሀገር ነች።

Karte Meereschutzgebiete weltweit Deutsch

በሁለተኛዉ ምድብ ማለትም የጤና ችግር ካለባቸዉ 10 የዓለም ሀገራት   ዝርዝር ዉስጥ አፍጋኒስታንና ኔፓል በዚህ ዝርዝር የተቀመጡ ብቸኛወቹ  የኤዥያ ሀገራት ሲሆኑ  ኢትዮጵያን ጨምሮ በአብዛኛዉ የአፍሪካ ሀገራት የተካተቱበት ነዉ። ከሀገራቱ መካከል ጊኒ፣ ኒጀር፣ ኮንጎ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ፣ ኤርትራ፣ ማላዊ፣ ሶማሊያ እና ሞዛምቢክ ይገኙበታል። ኢትዮጵያ ደግሞ በ10ኛ ደረጃ ተቀምጣለች።  

በእነዚህ የአፍሪካ  ሀገራት ከደረጃዉ ዝርዝር አንጻር ሲታይ ስጋቱ መለስተኛ ይምሰል እንጅ በተለይ በኢትዮጵያ የካንሰር፣የልብና የስኳር በሽታወችን የመሳሰሉ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታወች እየጨመሩ መምጣታቸዉ ይነገራል ።በተለምዶ  የሀብታም ሀገራትና ሰዎች  ችግር ተደርገዉ ይወሰዱ የነበሩት  እነዚህ በሽታዎች አሁን  መካከለኛ ገቢ ያላቸዉንና ድሃ የሚባሉት ሀገራትና  ሰወችም  እያጠቃ መምጣቱ እየተነገረ ነዉ። ለዚህ ደግሞ ጤነኛ ያልሆነ የአመጋገብና የአኗኗር  ዘይቤ የአልኮል መጠጥና የአደንዛዥ ዕጾች አጠቃቀም በድሃ ሀገራት እየተበራከተ መምጣቱ  የበሽታወቹ ስጋት እንዲጨምር ማድረጉን ባለሙያዎች ይናገራሉ።

በኢትዮጵያ ከከተሞች እድገት ጋር ተያይዞ በከተማ የሚገኙ  ወጣቶች በተለይም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና የ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪወችም ሳይቀር ጫትና ሺሻ እንዲሁም በአልኮል መጠጥ ሱስ መጠመድ እየተለመደ መምጣቱ ይነገራል።በሀገሪቱ በቂ የስፖርት ማዘዉተሪያና የመዝናኛ ቦታወች አለመኖርም ችግሩን እንዳባባሰዉ ይስተዋላል። ጤናማ ያልሆኑ የምግብ ሸቀጣሸቀጦች ለገበያ መቅረብም ሌላዉ የጤና ስጋት እየሆነ መምጣቱን ብዙወች ይገልጻሉ። ዶክተር አህመድ ረጃ እንደሚሉት ለችግሩን ለመፍታት የተቀናጀ ጥረት ይጠይቃል።

እንደ ዓለም ዓቀፉ የጤና ድርጅት መንግስታት የዜጎቻቸዉን የአኗኗር ዘይቤ እንዲሻሻል በማድረግ በበሽታወቹ ሳቢያ የሚደርሰዉን ጉዳት ለመቀነስ በርትተዉ ሊሰሩ ይገባል። በጉዳዩ ላይ የጤና ጥበቃ ምንስቴርን ለማነጋገር ያደረግነዉ ጥረት አልተሳካም።

ፀሐይ ጫኔ

ነጋሽ መሀመድ