1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በጉራጌ ዞን በተቀሰቀሰ ግጭት በርካታ ሰዎች ሞተዋል ተባለ

ቅዳሜ፣ መስከረም 5 2011

በጉራጌ ዞን መስቃን ወረዳ ኢንሴኖ ከተማ በተቀሰቀሰ ግጭት "በሁለት ቀናት ከ20 ያላነሰ ሰው ሞቷል። በማረቆ ወረዳ ፖሊስ ጣቢያ የሟቾችን አስከሬን አሁን አንቡላንስ እየሰበሰበው ይገኛል" ሲሉ የዐይን እማኝ ተናግረዋል። በግጭቱ የሰዎች ሕይወት መጥፋቱን ያረጋገጡ የማረቆ ወረዳ አስተዳዳሪ "ይኸን ያህል የሚል የለንም። እየለየን ነው" ብለዋል።

https://p.dw.com/p/34vQK
Karte Sodo Ethiopia ENG

በደቡብ ክልል በጉራጌ ዞን መስቃን ወረዳ በምትገኘው ኢንሴኖ ከተማ በተቀሰቀሰ ግጭት በርካታ ሰዎች መሞታቸውን የአይን እማኞች ተናገሩ። የአይን ዕማኝነታቸውን ለDW የሰጡ የአካባቢው ነዋሪ የማረቆ ወረዳ ዘጠኝ ቀበሌዎች ወደ መስቃን ወረዳ መካከላቸውን በመቃወም ከትናንት በስቲያ ሐሙስ በተቀሰቀሰ ግጭት ከ20 በላይ ሰዎች ሞተዋል። አንድ የአካባቢው ባለስልጣንም ግጭት መፈጠሩን እና ሰዎች መሞታቸውን አረጋግጠዋል። 

በማረቆ ወረዳ ቆሼ ከተማ የሚኖሩ የአይን ዕማኝ በሰዎች ላይ ጥቃት ሲፈጸም፣ የመኖሪያ ቤቶች ሲቃጠሉ መመልከታቸውን አስረድተዋል። "ጥቃቱን ለማስቆም ብንሞክርም አልተሳካልንም" ያሉት የአይን እማኙ "በሁለት ቀናት ሐሙስ እና አርብ ግፋ ቢል ከ20 ያላነሰ ሰው ሞቷል። በማረቆ ወረዳ ፖሊስ ጣቢያ የሟቾችን አስከሬን አሁን አንቡላንስ እየሰበሰበው ይገኛል። ግማሹ በወራጅ ወሐም ተወርውሯል" ሲሉ አስረድተዋል።

የማረቆ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ በለጠ ደራሮ ግጭቱ "የግል ፍላጎት ባላቸው አካላት እንደተቀሰቀሰ" ተናግረዋል። ግጭቱ "በመስቃን እና በማረቆ" መካከል የተፈጠረ አይደለም ያሉት አቶ በለጠ "መነሻው አልገባንም" ሲሉ ለDW አስረድተዋል። "በሰውም ላይም ጉዳት ደርሷል። በንብረትም ላይ ከፍተኛ የሆነ ጉዳት ደርሷል። በማረቆ አካባቢ በርካታ መስቃኖች አሉ። ምንም አይነት ጉዳት አልደረሰባቸውም። ሽማግሌዎቹ፤ አመራሮቹ እነሱን መንካት እኛን መንካት ነው። እነሱ አልበደሉንም በስመ መስቃን ማንም መነካት የለበትም በሚል በትክክል ሐብቱ የሰው ማንነቱ ተከብሮ የመስቃን ተወላጅ ምንም አልተደረገም። የማረቆ ተወላጅ ግን መስቃን ውስጥ ጥቃት እየደረሰበት ነው። በንብረቱም ላይ በሕይወቱም ላይ ከፍተኛ ጥቃት እየደረሰበት ነው" ሲሉ ተናግረዋል። በግጭቱ ምን ያክል ሰዎች እንደሞቱ የተጠየቁት አቶ በለጠ "ይኸን ያህል የሚል የለንም። እየለየን ነው ያለንው" ሲሉ ተናግረዋል።

አቶ በለጠ "የመንግሥት አካላት ሰራዊት በመላክ ጉዳዩ እየረገበ ነው። ልዩ ኃይሎችም አሉ። መከላከያዎችም አሉ። እነዚህ ንብረትም ሕይወትም የማዳን ሥራ ከፍተኛ ርብርብ በማድረግ ከህዝቡ ጎን በመቆም ከዱርየው ጥቃት ሕዝቡን እያዳኑ ነው ያሉት" ሲሉ አክለዋል።

የቆሼው ከተማ ነዋሪ የመከላከያ ሰራዊት አባላት እና የጸጥታ አስከባሪዎች በአካባቢው መሰማራታቸውን ገልጸዋል። "የጸጥታ አስከባሪዎች ወደ ቦታው ከተሰማሩ በኋላ የሰው ሕይወት እየጠፋ አይደለም" ያሉት አቶ በለጠ በበኩላቸው ውጥረቱ አሁንም እንዳልረገበ አስረድተዋል። ግጭቱ የተቀሰቀሰባት የኢንሴኖ ከተማ ከአዲስ አበባ በ211 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ከምትገኘው ቡታጅራ አቅራቢያ ትገኛለች። በጉራጌ ዞን ሥር የሚገኙት መስቃን እና ማረቆ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በአንድ ወረዳ ሥር ይተዳደሩ ነበር።

እሸቴ በቀለ

ተስፋለም ወልደየስ