1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በደ/ኢትዮጵያ የመጥፋት ስጋት የተደቀነባቸው ቋንቋዎች

ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 25 2011

ዓለማችን ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በምጣኔ ሀብታዊ ትስስር ወደ እንድ ጎራ ለመምጣት በማያቋርጥ ሂደት ውስጥ ትገኛለች። በዚህ በዘመነ ዓ/አቀፋዊነት(ግሎባላይዜሽን)ጊዜ፤ በዓለማችን ከ7000 በላይ ቋንቋዎች እንደሚነገሩ ይታወቃል።በኢትዮጲያ ብቻ እስከ 80 የሚደርሱ ቋንቋዎች የሚነገሩ ሲሆን፤ ይህም አገሪቱ የብዙ ባህልና ቋንቋዎች ባለቤት መሆኗን ያሳያል።

https://p.dw.com/p/3B0PV
gefährdete Sprachen in Süd-Äthiopien
ምስል DW/S. Wegayehu

የመጥፋት ስጋት የተደቀነባቸው ቋንቋዎች

ይሁን እንጂ ፣ ዋነኛ የባህል መሠረት የሆኑት እነኝህ ቋንቋዎች በተገቢው መንገድ ባለመልማታቸው ምክንያት ፤ ቁጥራቸው ቀላል የማይበሉት ቋንቋዎች ሲከስሙ እንዳንዶቹ ደግሞ በከፍተኛ ጉዳት ውስጥ እንደሚገኙ ፤ የኢትዮጲያ ቋንቋዎች ጥናትና ምርምር ማዕከል በተለያዩ ጊዚያት ያካሄዳቸው ጥናቶች ያመለከታሉ፡፡
የስነ ቋንቋ ዘርፍ ባለሙያዎች እንደሚሉት ቋንቋ የሰዎችን ባህል ፤ ወግ ፤ አኗኗርና ውስጣዊ ስሜታቸውን ለመግለጽ የሚያገልግል መሳሪያ ነው ፡፡ ይህ ለሰው ልጆች ብቻ የተሰጠ የተግባቦት መሣሪያ ታዲያ ፤ እንዳንዴ ሊጎዳ ባስ ካለም ከእነአካቴው ጨርሶ ሊጠፋ ይችላል፡፡ የቋንቋ መዳከም ወይም መጥፋት በአንድ ማህበረሰቡ ውስጥ የሚገኙ ታሪካዊ ፤ ባህላዊና ትውፊታዊ ሀብቶችም አብረው እንዲጠፉ ያደርጋል፡፡ በተለይም ማህበረሰቦች በቋንቋቸው መጥፋት ወይም መሞት ምክንያት መሠረታዊ የባህል ማንነታቸውን በማጣት ማህበራዊ ቀውስ ውስጥ ሊገቡ ይቻላሉ ይታመናል።
በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ልሳንና የሥነ ተግባቢት መምህር የሆኑት ዶክተር ፈቀደ ምኖታ ከሰማኒያ በላይ ቋንቋዎች የሚነገሩባት ኢትዮጲያ የቋንቋዎች ጉዳት ወይም መጥፋት አደጋ ከተጋረጠባቸው አገራት ተርታ አንደምትገኝ ይናገራሉ ፡፡ ከቅርብ ዓመታት በፊት በኢትዮጲያ ቋንቋዎች ጥናትና ምርምር ማዕከል የተካሄደ ጥናት እንደሚያመለክተው በአሁኑወቅት በኢትዮጲያ ከሚነገሩ ቋንቋዎች መካከል 21 በመቶ ያህሉ የጉዳይ ወይም የመጥፋት አደጋ የተጋረጠባቸው ናቸው ፡፡ እንደዶክተር ፈቀደ ምኖታ ገላጻ ቀደም ባሉት ጊዚያት አገልግሎት ላይ የነበሩና በአሁኑ ወቅት ግን ሙሉ በሙሉ ከጠፉ መካከል በደቡብ ክልል ይነገሩ የነበሩ መስመስ ፤ አላንጋችና ሬር በሬ የተባሉ ቋንቋዎች ይገኙባቸዋል፡፡
በተጨማሪም በአማራ ክልል ጋፍትና ወይጦ እንዲሁም በኦሮሚያ ወለጋ አካባቢ ይነገር የነበረ ሻቦ የተበላ ቋንቋ በተመሳሳይ ሁኔታ የጠፉ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ በአሁኑወቅት በኢትዮጲያ ከሚኙት ቋንቋዎች መካከል ግማሽ ያህሉ በደቡብ ክልል ውስጥ የሚነገሩ ናቸው፡፡ ከእነኝሁ ቋንቋዎች መካከል ታዲያ ሙሩሌ ፤ ናኦ ፤ ጫራና ብራይሌ የመሳሰሉ ቋንቋዎች ለመጥፋት ከተቃረቡ መካከል እንደሚጠቀሱ በክልሉ የብሄረሰቦች ምክር ቤት የጋራ እሴቶች ማጎልበትና ፤ አለመግባባቶችን መፍታት የሥራ ሂደት ዳይሬክተር አቶ ዘለቀ በላይነህ ይናገራሉ፡፡
ለቋንቋዎች መዳከምና መጥፋት በርካታ ምክንያቶች መኖራቸውን የሚናገሩት የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ልሳንና የሥነ ተግባቢት መምህር ዶክተር መሰረታዊ ናቸው የሚሏቸውን ይጠቅሳሉ፡፡  የደቡብ ክልል የብሄረሰቦች ምክር ቤት በክልሉለመጥፋት የተቃረቡ ቋንቋዎችን ለመታደግ የተለያዩ ተግባራትን በማከናወን ላይ እንደሚገኝ የሥራ ሂደቱ ዳይሬክተር አቶ ዘለቀ በላይነህ ይናገራሉ ፡፡ ከተግባራቱ መካከል ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመተባበር ቋንቋዎቹ በስረዓተ ትምህርት ውስጥ የሚካተቱበትን ጥናት የማካሄድ ሥራ እንደሚጠቀስ ዳይሬክተሩ ይገልጻሉ፡፡
ሸዋንግዛው ወጋየሁ
ማንጋፍቶት ስለሺ

gefährdete Sprachen in Süd-Äthiopien
ምስል DW/S. Wegayehu