1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የ188 ሰዎች ክስ ተቋረጠ

ማክሰኞ፣ ሰኔ 26 2010

በደቡብ ክልል የኮንሶ ባህላዊ መሪ  ካላ ገዛህኝ ወልዱን ጨምሮ የ188 ተከሳሾች ክስ እንዲቋረጥ መወሰኑን የክልሉ ፍትህ ቢሮ አስታወቀ። ክሱ የተቋረጠላቸዉ ከ 2007 እስከ መስከረም 2009  በኮንሶ ወረዳ ተከስቶ በነበረዉ አመፅና ብጥብጥ ተጠርጥረው የታሰሩ ሰዎች መሆናቸዉን ቢሮዉ ገልጿል።

https://p.dw.com/p/30lZV
Äthiopien Das Hochland von Konso
ምስል picture-alliance/Mary Evans Picture Library/M. Watson

የታሳሪዎቹን ክስ መቋረጥ ተከትሎ ለአካባቢዉ ነዋሪዎች ደስታ ቢፈጥርም የታሰሩበት ጥያቄ በአግባቡ እንዲመለስ አንድ የአካባቢዉ የሀገር ሽማግሌ ገልፀዋል ።  
የክልሉ የፍትህ ቢሮ ሃለፊ ወይዘሪት ትዝታ ፈቃዱ ለሀገር ዉስጥ መገናኛ ብዙሃን እንደገለፁት፤ዛሬ ክሳቸዉ የተቋረጠዉ በክልሉ በሰገን አካባቢ ህዝቦች ዞን በኮንሶ ወረዳ ከ2007 እስከ መስከረም 2009 ዓ/ም በአካባቢዉ ተከስቶ ከነበረ አመፅ ጋር በተያያዘ የታሰሩ ሰዎች ናቸዉ።ክሱ እንዲቋረጥ የተደረገዉም ለተሻለ ሀገራዊ መግባባት፣ የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት እንዲሁም በሀገሪቱ የተጀመረዉን የለዉጥ ጉዞ ለማስቀጠል መሆኑን ሃላፊዋ አመልክተዋል።
በዛሬዉ ዕለት ክሳቸዉ የተቋረጠላቸዉ ሰዎች ቁጥራቸዉ  188 ሲሆን በ8 መዝገብ ተከሰዉ የነበሩ ናቸዉ።ነገር ግን ከዚህ መዝገብ ዉስጥ በነብስ ማጥፋትና በከባድ ወንጀል የተጠረጠሩ የሁለት ሰዎች ክስ አልተቋረጠም ነዉ የተባለዉ። በክልሉ ፍትህ ቢሮ ክሳቸዉ እንዲቋረጥ ከተደረገላቸዉ መካከልም የኮንሶ ባህላዊ የጎሳ መሪ አቶ ካላ ገዛኽን እንደሚገኙም ታዉቋል።
በኮንሶ ወረዳ የሀገር ሽማግሌ መሆናቸዉን የገለፁልን አቶ ኩርሴ ኤሌቴ እንደሚሉት የእስረኞቹ ክስ መቋረጥ አስደሳችና ከመንግስት ጎን እንድንቆም የሚያደርግ ነዉ ሲሉ ለዶቼ ቬለ ገልፀዋል።
ይሁን እንጅ «የኮንሶ ወረዳ በሰገን አካባቢ ህዝቦች ዞን ከመተዳደር ወጥታ እንደቀድሞዉ ልዩ ወረዳ ሆና እንድትተዳደር« ያነሳነዉ ጥያቄ በአግባቡ መልስ እንዲያገኝ ያስፈልጋል ብለዋል።

Äthiopien Das Hochland von Konso
ምስል picture-alliance/Mary Evans Picture Library/M. Watson

በዚህ ጥያቄ ሳቢያ የታሰሩ ሰዎችን ክስ ከማቋረጥ ባለፈ ከሀገር የተሰደዱና በደል የደረሰባቸዉ የአካባቢዉ ነዋሪዎች ካሳ እንዲያገኙና በደል ፈጻሚዎቹም ለህግ እንዲቀርቡ አሳስበዋል።በአካባቢዉ በተቀሰቀሰዉ አመፅ ሳቢያ ከስራ የተፈናቀሉም ወደስራ ገበታቸዉ እንዲመለሱ ጠይቀዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች እያደረገ ያለዉን እስረኞችን በይቅርታና በምህረት መፍታት ተከትሎ ከኮንሶ ተወላጆች አንድም ሰዉ አልተፈታም በሚል ነዋሪዎቹ ቅሬታ ማቅረባቸዉን መዘገባችን ይታወቃል።

ሙሉ ቅንብሩን የድምፅ ማዕቀፉን በመጫን ያድምጡ።


ፀሀይ ጫኔ
አርያም ተክሌ