1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በትግራይ ክልል ምክር ቤት የተደረገዉ ሹም ሽር

Merga Yonas Bula
ረቡዕ፣ ጥር 2 2010

ዛሬ የትግራይ ክልል ምክር ቤት ባካሄደዉ አምስተኛ መደበኛ ሶስተኛ አስቸኳይ ስብሰባ ሹም ሽሮችን አካሒዷል። በክልሉ ያሉት ችግሮች በዚህ ሹም ሽር እንደማይፈቱና ከአምስት ዓመት በፊት ጀምሮ መተካካት በሚል ሲቀርብ የነበረዉ ሀሳብ እዉን እንዳልሆነ ባለሙያዎች ይናገራሉ። 

https://p.dw.com/p/2qeBO
Äthiopien 40. Jahrestag TPLF
ምስል DW/T. Weldeyes

Tigray Reg. Council Reshuffles - MP3-Stereo

ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ/ ህወሓት/ ከአንድ ወር በላይ ግምገማ ማድረጉ ይታወሳል። «የሰማዕታትን አላማ ለማሳካት» ተደረገ የተባለዉን ከጥቂት ጊዜ በፊት የተደረገውን ግምገማ ተከትሎ በሃላፊነት ላይ የነበሩ በሌሎች እንዲተኩ እንደተወሰነ፣ በዛም መሰረት ዛሬ የክልሉ ምክር-ቤት በአምስተኛ መደበኛ ሶስተኛ አስቸኳይ ስብሰባዉ ሹም ሽሮችን እንዳካሄ የምክር ቤቱ የኮምዩንኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ አቶ ሙሉጌታ ታረቀ ለዶይቼ ቬሌ ተናግረዋል።

የቀድሞ የክልሉ ርዕሰ-መስተዳድር የነበሩት አቶ አባይ ወልዱና የኤፈርት ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ በየነ ምክሩን ከሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልነታቸዉ ተነስተዉ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል እንዲሆኑ መደረጋቸዉን የአገር ዉስጥ ዘገባዎች አመላክተዋል። የኤፈርት ሥራ አስከያጅና የቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ ባለቤት ወ/ሮ አዜብ መስፍን ከመዕከላዊ ኮሚቴ እንደታገዱም ዘገባዉ አክሎበታል።

በክልሉ ያለዉ ችግር በዚህ ሹም ሽር ይፈታል ብዬ አላስብም የሚሉት በመቐለ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስና የስትራቴጅክ ጥናቶች መምህር የሆኑት አቶ መሃሪ ዮሃንስ ናቸዉ።

የሹም ሽሩ መነሻ በህወሓት ዉስጥ ያለዉ «የስልጣን ሽኩቻ» ነዉ የሚሉት የዓረና ትግራይ ለዴሞክራሲና ለሉዓላዊነት ሊቀ-መንበር የሆኑት አቶ አብራሃ ደስታ ሹም ሽሩ «መሰረታዊ ለዉጥ አላመጣም» ይላሉ።

ህወሓት በፓርቲዉም ሆነ በመንግስት እርከኖች በወጣት እንደሚተካ ከአምስት ዓመት በፊት ጀምሮ ሲናገር ቆይቷል። የክልሉ ምክር-ቤት የኮምዩንኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ አቶ ሙሉጌታ መተካካቱ እየተፈጸመ እንደሚገኝ ቢናገሩም ሌሎች መተካካት የተባለዉ እስካሁን እምብዛም አልታየም ስሉ ይከራከራሉ።

እስካሁን ለፓርቲዉም ሆነ ለክልሉ ሊቀ-መንበርነት ትግል ዉስጥ የነበሩት ታጋዮች ሲቀባበሉ ቢቆዩም መተካካቱ ወደ ላይኛው እርከን እንዳልደረሰ መምህር መሃሪ አክሎበታል።

መርጋ ዮናስ

አርያም ተክሌ