1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በቴፒ ከተማ የቀጠለው ተቃውሞ እና አለመረጋጋት

ረቡዕ፣ ኅዳር 19 2011

በደቡብ ክልል በሸካ ዞን በምትገኘው የቴፒ ከተማ ከወራት ወዲህ በቀጠለው ውዝግብ ነዋሪዎች ባለመረጋጋትና በግጭት ሥጋት ውስጥ ይገኛሉ። የከተማይቱ ነዋሪዎች እንደገለጹት፣ በከተማዋ ያለመረጋጋቱና የግጭት ሥጋቱ የተፈጠረው የሸካ ብሄረ ሰብ በዞን መዋቅር ለመደራጀት ያቀረበውን ጥያቄ ተከትሎ ነው።

https://p.dw.com/p/394fS
Demo in Teppi Äthiopien
ምስል DW/S. Wegayehu

ውጥረት በቴፒ

በደቡብ ክልል ሸካ ዞን የምትገኘው የቴፒ ከተማ ከባለፉው የመስከረም ወር አንስቶ  ባለመረጋጋትና በግጭት ሥጋት ውስጥ እንደምትገኝ ከአካባቢው የሚወጡ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
የከተማዋ ነዋሪዎች እንደሚሉት በተከሰተው አለመረጋጋትና የግጭት ሥጋት የተነሳም፤  ከመንግሥት መሥሪያ ቤቶች እስከ ንግድ ድርጅቶች ያሉ ተቋማት አገልግሎታቸውን አቋርጠው ከተዘጉ ሶስተኛ ወራቸውን አስቆጥረዋል፡፡
በሚዛን ቴፒ ዩኒቨርስቲ ሥር የሚገኘው የቴፒ ካምባሳም ፤ እስከአሁን በግቢው የተመደቡ ተማሪዎችን መቀበል እንዳልቻለ ነው የዲ ደብሊው ታማኝ ምንጮች ያረጋገጡት ፡፡
የቴፒ ከተማ ነዋሪዎችንና የሸኮ ብሄረሰብን በመወከል ለክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቤቱታ ለማቅረብ አዚህ ሀዋሳ ከተማ  የተገኙት ተወካዮች እንደገለፁት ፤ በከተማዋ አለመረጋጋቱ የተከሰተው የሸኮ ማህበረሰብ አራሱን በዞን አስተዳደር ለማዋቀር ያቀረበውን ጥያቄ ተከትሎ ነው፡፡
ከብሄረሰቡ የተነሳው ጥያቄ ሕገ መንግሥታዊ መሠረት ያለውና በሰላማዊ መንገድ የቀረበ የመዋቅር ጥያቄ ብቻ እንደሆነና ለተፈጠረው አለመረጋጋት ምክንያት ሊሆን እንደማይችል  የማህበረሰቡ ተወካይ አቶ ሸዋ ቱቻ ለዲ ደብሊው ገልጸዋል፡፡
በአሁኑወቅት በቴፒ ከተማ ዙሪያ የተደራጁ ቡድኖች የመዋቅር ጥያቄውን ለማዳፈን በሚደርጉት የቡድን እንቅስቃሴ የተነሳ ፤ ከተማዋ ዛሬም ድረስ ባለመረጋጋትና በሥጋት  ውስጥ እንደምትገኝ ተወካዮቹ ይናገራሉ፡፡
በተለይም የክልሉ መንግሥት ለከተማው ነዋሪዎች ተገቢውን የጸጥታ ጥበቃ ባለማድረጉ ፤ ባለፉት አምስት ቀናት ብቻ በተደራጁ ቡድኖች በተፈጸሙ ጥቃቶች አሥራ ሁለት መኖሪያ ቤቶች  ሲቃጠሉ ፤ በበርካታ ወጣቶች ላይ የድብደባና  የአካል ጉዳት መድረሱን ፤ ሌላው የማህበረሰቡ ተወካይ አቶ አሸናፊ በላይ ተናግረዋል፡፡
በጉዳዩ ላይ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጽህፈት የሥራ ሃላፊዎች ምላሽ እንዲሰጡበት  በስልክም ሆነ በአካል ለማነጋገር ያደረኩት ተደጋጋሚ ሙከራ አልተሳካልኝም፡፡
ይሁንእንጂ ክልሉን በገዢ ፓርቲነት በማስተዳደር ላይ የሚገኘው ፤ የደቡብ ኢትዮጲያ ሕዝቦች ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ የማዕከላዊ ኮሚቴ ፅህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ሞገስ ባልቻ ለክልሉ መንግሥት ቴሌቪዥን በሰጡት መግለጫ ፤ ችግሩን ከከተማው ነዋሪዎች ጋር ተወያይቶ ለመፍታት የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች ቡድን ወደ አካባቢው መንቀሳቀሱን ገልጸዋል፡፡
በደቡብ ክልል ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የአደረጃጀት ጥያቄዎችን ተከትለው  የሚፈጠሩ ግጭቶች ለሰው ሕይወት መጥፋት እና ለንብረት መውደም ምክንያት እየሆኑ ይገኛሉ፡፡
የክልሉ ምክር ቤት ባለፈው ወር በካሄደው መደበኛ ጉባዔ የሦስት ዞኖችና የአርባ አራት ወረዳዎች  መዋቅርን ቢያጸድቅም ፤ ከአየካባቢው የሚነሳው የተጨማሪ መዋቅር ጥያቄ ግን  ዛሬም  አላባራም፡፡

ሸዋንግዛው ወጋየሁ

አርያም ተክሌ

ሂሩት መለሰ