1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በቤኒሻንጉልና ኦሮሚያ ክልል አዋሳኝ የቀጠለዉ ግጭት

ረቡዕ፣ መስከረም 23 2011

በቤንሻንጉል ጉሙዝ እና ኦሮሚያ ክልል አዋሳኝ ቦታዎች ላይ በደረሱ ጥቃቶች 44 ሰዎች መሞታቸው መገደላቸውን የቤንንሻንጉል ጉሙዝ ክልል የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት አስታወቀ። የሟቾቹ ቁጥር ከዚህም በላይ ሊጨምር እንደሚችልም ገልጿል።

https://p.dw.com/p/35svH
Karte Äthiopien Südsudan Gambella Englisch

የቤንንሻንጉል ጉሙዝ ክልል የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት

በቤንሻንጉል ጉሙዝ እና ኦሮሚያ ክልል አዋሳኝ ቦታዎች ላይ በደረሱ ጥቃቶች 44 ሰዎች መሞታቸው መገደላቸውን የቤንንሻንጉል ጉሙዝ ክልል የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት አስታወቀ። የሟቾቹ ቁጥር ከዚህም በላይ ሊጨምር እንደሚችልም ገልጿል። በሁለቱ ክልል አዋሳኝ ቦታዎች ላይ የሚኖሩ ነዋሪዎች በአካባቢው አሁንም ጥቃት አለመቆሙን እና ቤቶች እየተቃጠሉ እንዳሉ ለDW እማኝነታቸውን ሰጥተዋል። የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ኃላፊ አቶ ዘላለም ጃለታ ለ«DW» እንደተናገሩት በሁለቱ ክልሎች አዋሳኝ ቦታዎች ላይ በደረሰ ጥቃት ከቤንሻንጉል ጉሙዝ 16 ሰዎች ከኦሮሚያ ደግሞ 28 ሰዎች መገደላቸውን ተናግረዋል። ባለፈው ረቡዕ መስከረም 16 አራት የካማሺ ዞን አመራሮች መገደላቸውን ተከትሎ በአካባቢው በተቀሰቀሰ ግጭት ምክንያት በክልላቸው ብቻ 20 ሺህ የሚሆኑ ሰዎች መፈናቀላቸውን ገልጸዋል። የኦሮሚያ ክልል ዛሬ ይፋ ባደረገው መረጃ መሰረት በሰሞኑ ግጭት 70 ሺህ ሰዎች ተፈናቅለዋል። ይህንን መረጃ መመልከታቸውን የተናገሩት አቶ ዘላለም ሰዎቹ የተፈናቀሉት ከቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ብቻ ሳይሆን በወሰን አካባቢ ካሉ የኦሮሚያ ክልል አካባቢዎች ጭምር ነው ብለዋል። 
በሰሞኑ ግጭት ቀያቸውን ለቅቀው “ወደ በረሃ መሸሻቸውን” የሚናገሩ አንድ ተፈናቃይ በአካባቢያቸው አሁንም ግጭቱ መቀጠሉን ለDW ተናግረዋል። ከነቀምት ከተማ 42 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ባለች አንገር በተሰኘች አነስተኛ መንደር ነዋሪ እንደሆኑ የተናገሩት አቶ ኤርሚያስ አበራ ከአምስት ቀን በፊት የተኩስ ድምጽ ሲሰሙ እና ቤቶች መቃጠል ሲጀምሩ ህይወታቸውን ለማትረፍ መሸሻቸውን ገልጸዋል። በአካባቢያቸው ከስምንት እስከ 10 ሰው እንደሞተ መስማታቸውን እና ደብዛቸው እስካሁን ያልታወቀ እንዳለም ጠቁመዋል።
በመኖሪያ መንደራቸው ያለው ሁኔታ መሻሻሉን ለማየት ዛሬ ወደ ስፍራው የሄዱት አቶ አበራ ቤቶች ሲቃጠሉ እንደተመለከቱ የዓይን እማኝነታቸውን ሰጥተዋል። ። በአካባቢው የመከላከያ ሰራዊት ቢሰማራም ጥቃቱ አለመቆሙንም አስረድተዋል። በአንገር እና አካባቢው ያለው ጥቃት አሁንም መቀጠሉን ያረጋገጡት አቶ ዘላለም ጉዳዩ ከክልሉ አቅም በላይ በመሆኑ ተጨማሪ የመከላከያ ኃይል ወደ ስፍራው እንዲገባ መጠየቁን ገልጸዋል። ከቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ኃላፊ እና በአንገር በተሰኘች አነስተኛ መንደር ነዋሪ ከሆኑት ዓይን እማኝ ጋር የተደረገዉን ቃለ-ምልልስ የድምጽ ማዕቀፉን በመጫን ይከታተሉ። 

 

ተስፋለም ወልደየስ

አዜብ ታደሰ 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ