1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በሻሸመኔ ቢያንስ አራት ሰዎች ተገደሉ

እሑድ፣ ነሐሴ 6 2010

በሻሸመኔ አቶ ጃዋር መሐመድን ለመቀበል በተሰናዳ መርኃ-ግብር ላይ በተፈጠረ ግፊያና በተሳታፊዎች ጥቃት ቢያንስ 4 ሰዎች ሞቱ። ቦምብ ይዞ ተገኝቷል በሚል ጥርጣሬ በተሳታፊዎች የተያዘ አንድ ግለሰብ በአሰቃቂ ሁኔታ ተሰቅሎ ተገድሏል። ጃዋር መሐመድን ጨምሮ የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትወርክ ልዑካን ቡድን በሌሎች አካባቢዎች ያቀዷቸውን ጉብኝቶች ሰርዘዋል

https://p.dw.com/p/332aw
Äthiopien Unruhen in Shashemene
ምስል Privat

በሻሸመኔ ከተማ የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትወርክ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጃዋር መሐመድን ለመቀበል በተሰናዳ መርኃ-ግብር ላይ በተፈጠረ ግፊያ እና በተሳታፊዎች ጥቃት ቢያንስ አራት ሰዎች ሞቱ። በበርካታ ሰዎች ላይ ቀላል እና ከባድ ጉዳት መድረሱንም የዓይን እማኞች እና የሆስፒታል ምንጮች ተናግረዋል። ቦምብ ይዞ ተገኝቷል በሚል ጥርጣሬ በተሳታፊዎቹ የተያዘ አንድ ግለሰብ በአሰቃቂ ሁኔታ ተሰቅሎ የተገደለ ሲሆን አንድ ተሽከርካሪ በእሳት ጋይቷል። አቶ ጃዋር መሐመድ እና የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትወርክ ልዑካን አባላት ከኩነቱ በኋላ በሌሎች የክልሉ አካባቢዎች ያቀዷቸውን ጉብኝቶች መሰረዛቸውን አስታውቀዋል። 

በመርኃ-ግብሩ ተሳትፈው ጉዳት የደረሰባቸው አንድ የአይን እማኝ ለሕክምና በተጓዙበት ማዕከል ሁለት ሰዎች ሞተው መመልከታቸውን ለዶይቼ ቬለ አረጋግጠዋል። የአይን እማኙ "አንዱ አራት ይላል አንዱ አምስት ይላል። እኔ ሁለት የሞተ ሰው አይቻለሁ። እኔ ራሴ አሞኝ ከዚያ ወደ ሐኪም ቤት ነው የወሰዱኝ። ሐኪም ቤት ገብተው የሞቱ ሁሉ አሉ። የሰው ብዛት አይታወቅም። በየሐኪም ቤቱ ስትሔድ በሽተኛ ነው የምታገኘው" ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

በሻሸመኔ ከተማ የሚገኘው የፈያ አጠቃላይ ሆስፒታል ባለቤት ዶክተር ቀለሙ ደስታ አንድ ሰው ሕይወቱ አልፎ ወደ ሕክምና ማዕከሉ መድረሱን ለዶይቼ ቬለ አረጋግጠዋል። "አንድ ሰው የሞተ አለ። የኮፈሌ ሰው ነው። አስክሬኑን ይዘው ሔደዋል" ያሉት ዶክተር ቀለሙ ቀላል ጉዳት የደረሰባቸው እና የደነገጡ 80 ሰዎች በፈያ አጠቃላይ ሆስፒታል እገዛ ተደርጎላቸው ወደየመጡበት መመለሳቸውን ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

በሻሸመኔ ከተማ በሚገኘው ስታዲየም በተዘጋጀው መርኃ-ግብር የክብር እንግዳው አቶ ጃዋር መሐመድ ብዙም አለመቆየታቸውን ዶይቼ ቬለ ያነጋገራቸው የአይን እማኞች አረጋግጠዋል። በቦታው የነበሩ የአይን እማኝ "ምን እንደታየ እንጃ በአምስት ደቂቃ ጃዋር ወጣ። ልክ እሱ ከመውጣቱ አንድ ግለሰብ ቦምብ ተያዘበት" ሲሉ ተናግረዋል።

አንድ ሌላ ግለሰብ ቦምብ ይዟል በሚል በወጣቶች ተሰቅሎ መገደሉን የአይን እማኙ ጨምረው ተናግረዋል። "አንዱ ሲያዝ የገመድ ቦርሳ ውስጥ ቦምብ ይዟል። እና ቄሮዎች ይዘው ፖል ላይ ሰቅለው ገድለውታል። እንደ ኢቢሳ አዱኛ መንገድ ላይ እየጎተቱት በመኪና ወደ ላይ ወሰዱት" ሲሉ አስረድተዋል። ኢቢሳ አዱኛ የትግል ሙዚቃዎች በማቀንቀን የሚታወቅ የኦሮሞ ተወላጅ ሲሆን ቄሮዎች በኢትዮጵያ መንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ተገድሏል ብለው ያምናሉ።

የኦሮሞ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦህዴድ) የድርጅት ጉዳዮች ኃላፊው አቶ አዲሱ አረጋ በግል የፌስቡክ ገፃቸው ላይ ባወጡት ጽሁፍ በመርኃ-ግብሩ ላይ ቦምብ ይዞ ተገኝቷል የተባለ ሰው መገደሉን አረጋግጠዋል። "የተወሰኑ ህገ-ወጥ ቡድኖች ከተማዋ ላይ ህገ-ወጥነት፣ ብጥብጥ እና ግጭት ለማስነሳት ተንቀሳቅሰዋል። በዚህ ሂደትም ቦንብ ይዞ ተገኝቷል በሚል ሀሰተኛ ወሬ በአንድ ግለሰብ ላይ በቡድን ጥቃት በማድረስ የግለሰቡ ህይወት ሊያልፍ ችሏል" ብለዋል። በመርኃ-ግብሩ ላይ "በተፈጠረ መገፋፋትና መረጋገጥ የሶስት ሰዎች ህይወት ሲያልፍ በርከት ያሉ ሰዎች ላይ ደግሞ የአካል ጉዳት ደርሷል" ሲሉ አክለዋል። 

በወቅቱ የኦሮሚያ ሰሌዳ የለጠፈ ተሽከርካሪ በተሳታፊዎች በእሳት የጋየ ሲሆን ተሽከርካሪው የመንግሥት ንብረት እንደነበር አንድ የክልሉ ከፍተኛ ባለሥልጣን ለዶይቼ ቬለ አረጋግጠዋል። ተሽከርካሪው የሻሸመኔ ከተማ የፀጥታና አስተዳደር ፅህፈት ቤት እንደነበር የገለጹት አቶ አዲሱ "ምንም አይነት ቦምብ እንዳልነበረ ከኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ማረጋገጥ ተችሏል" ብለዋል። አቶ አዲሱ ከሰዓት በኋላ ከተማዋ መረጋጋቷን እና "በተፈጠረዉ ችግር በመሳተፍ የተጠረጠሩ ግለሰቦች" በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ገልጸዋል።
የኦሮሚያ ሚዲያ ኔት ወርክ (ኦ. ኤም. ኤን)  ማምሻውን በፌስቡክ ገፁ ባወጣው መግለጫ "ይህን አጋጣሚ በመጠቀም ሁኔታዎችን ወደ ብጥብጥ ለመቀየር የተንቀሳቀሱ ሀይሎች ሰላማዊ ህዝቡን ተገን በማድረግ የፈፀሙትን ርካሽና ኢሰብአዊ ተግባር አጥብቀን እናወግዛለን" ብሏል። የሻሸመኔውን ሁነት ተከትሎ "አቶ ጃዋር እና ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት ባደረጉት አስቸኳይ ዉይይት" የኦ. ኤም. ኤን ልዑክ ያቀዳቸው የጉብኝት መርሃ ግብሮች ለጊዜው እንዲቋረጥ መወሰናቸውን መግለጫው አስታውቋል፡፡ ልዑኩ ከሻሸመኔ ቆይታው በኋላ በሀዋሳ ከከተማ ነዋሪዎች ጋር የአዳራሽ ስብሰባ አካሂዷል። በሌሎች ከተሞች ሊደረጉ የታሰቡ ጉብኝቶች የተሰረዙት የሻሸመኔው ዓይነት "ተመሳሳይ ችግሮች እንዳይከሰቱ ለማድረግ" በሚል እንደሆነ ኦ. ኤም. ኤን በመግለጫው ጠቁሟል።  

እሸቴ በቀለ

ተስፋለም ወልደየስ