1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ስፖርት፤ ሚያዝያ 1 ቀን፣ 2010 ዓ.ም

ሰኞ፣ ሚያዝያ 1 2010

በተለያዩ የአውሮጳ ከተሞች ውስጥ በተደረጉ የማራቶን ሩጫ ፉክክሮች ኢትዮጵያውያንና ኬንያውያን አሸናፊ ኾነዋል። በአፍሪቃ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ቅዱስ ጊዮርጊስ ድል ቀንቶታል። ወደ ታንዛኒያ ያቀናው ወላይታ ዲቻ ግን ተሸንፏል። ሊቨርፑል ባለፈው ሣምንት በዜሮ የሸኘው ማንቸስተር ሲቲን ነገ በሜዳው ለመግጠም ያቀናል።

https://p.dw.com/p/2vjbO
Fußball Euro 2008 Finale Deutschland Spanien Torres Tor
ምስል picture-alliance/ dpa

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

በሣምንቱ መጨረሻ ላይ በተለያዩ የአውሮጳ ከተሞች ውስጥ በተደረጉ የማራቶን ሩጫ ፉክክሮች ኢትዮጵያውያን እና ኬንያውያን አትሌቶች አሸናፊ ኾነዋል። በአፍሪቃ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ቅዱስ ጊዮርጊስ ድል ቀንቶታል። ወደ ታንዛኒያ ያቀናው ወላይታ ዲቻ ግን ተሸንፏል። በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ እና በአውሮጳ ሻምፒዮንስ ሊግ ሰሞኑን ተደጋጋሚ ሽንፈት የደረሰበት ማንቸስተር ሲቲ፤ ባለፈው ሣምንት በዜሮ የሸኘው ሊቨርፑልን ነገ በሜዳው ቀጥሯል። ነገ እና ከነገ በስተያ የሻምፒዮንስ ሊግ የሩብ ፍጻሜ አራት ግጥሚያዎች ይኖራሉ። 

አትሌቲክስ

በሣምንቱ ማሣረጊያ በተለያዩ የአውሮጳ ሃገራት በተከናወኑ የማራቶን ሩጫ ሽቅድምድሞች ኢትዮጵያውያን በወንድ እና በሴት ውጤት ቀንቷቸዋል። ትናንት ቱርክ ኢስታንቡል ከተማ ውስጥ በተከናወነው የግማሽ ማራቶን የጎዳና ላይ ሩጫ ፉክክር  ኢትዮጵያዊው አምደወርቅ ዋለልኝ በድንቅ ኹኔታ 59 ደቂቃ ከ50 ሰከንድ በመሮጥ በአንደኛነት አጠናቋል። 17 ሰከንዶች ዘግይቶ የሁለተኛነት ደረጃውን ያገኘውም ሌላኛው ኢትዮጵያዊ አሠፋ ተፈራ ነው።ቱርካዊው ካን ኪጌን ከአሰፋ ለጥቂት በ1 ሰከንድ ተበልጦ  የሦስተኛ ደረጃ ለአዘጋጇ ሀገር እንዲሆን አድርጓል።

Symbolbild Leichtathletik Laufen
ምስል picture-alliance/dpa/B. Thissen

በዚሁ ውድድር በሴቶች ዘርፍ ኢትዮጵያውያቱ አባበል የሻኔ እና ሮዛ ደረጄ አንደኛ እና ሁለተኛ ተከታትለው በመግባት ድል ተቀዳጅተዋል። አባበል ርቀቱን ለማጠናቀቅ የፈጀባት ጊዜ 1 ሰአት ከ6 ደቂቃ ከ22 ሰከንድ ነው። ከዚያም ከ45 ሰከንድ በኋላ ሮዛ ስትገባ፤ ኬኒያዊቷ ዲያና ኪፕዮኬ ሦስተኛ የወጣችው ሮዛ ከገባችበት ሰአት 55 ሰከንድ በኋላ ነው።  በዚህ ውድድር ሌላኛዋ ኬንያዊትን ተከትላ የአምስተኛ ደረጃን ያገኘችው ኢትዮጵያዊቷ እታገኝ ወልዱ ናት።

ጣሊያን ሮም ከተማ ውስጥ በተከናወነው የማራቶን ሩጫ ደግሞ በሴቶች ምድብ ኢትዮጵያዊቷ ራህማ ቱሳ በሦስት ተከታታይ ዓመታት ለሦስተኛ ጊዜ አሸናፊ መኾን ችላለች። ራህማ ውድድሩን በአንደኛነት ለማጠናቀቅ የፈጀባት ጊዜ ሁለት ሰዓት ከ23 ደቂቃ ከ46 ሰከንድ ነው።

Deutschland, Brandenburger-Tor, 36. Berliner Halbmarathon
ምስል picture-alliance

በዚህ ውድድር ትውልደ-ኢትዮጵያዊት የባሕሬን ሯጭ ደሊላ አብዱልቃድር ከሦስት ሰከንድ በኋላ ተከትላ በመግባት የሁለተኛ ደረጃ አግኝታለች። የሦስተኛ ደረጃውን ኬንያዊቷ አትሌት አሊስ ኪቦር ወስዳለች። እዛው ጣሊያን ሚላኖ በተከናወነው ማራቶንም አሸናፊው ኢትዮጵያዊው አብዲዋቅ ቱፋ ሠይፉ ነው፤ የፈጀበት ጊዜደግሞ 2 ሰአት ከ9 ደቂቃ  4 ሰከንድ።  ኬንያውያን ጁሱስ ኪሙታይ እና ባርናባስ ኪፕቱም ሁለተኛ እና ሦስተኛ ወጥተዋል። በሴቶች ምድብ የሚላኖ ማራቶን አንደኛ ከወጣችው ከሉሲ ካቡ አንስቶ እስከ ሦስተኛ ደረጃ ሙሉ ለሙሉ የኬንያውያቱ ኾኗል።

ፈረንሳይ መዲና ውስጥ በተከናወነው የፓሪስ ማራቶን የሩጫ ፉክክር ኢትዮጵያዊቷ ጉሉሜ ጫላ ሦስተኛ ደረጃ ከማግኘቷ ውጪ ሙሉ ለሙሉ በወንድም በሴትም ፉክክር በኬንያውያን የበላይነት ተጠናቋል።

በበርሊኑ ማራቶን ተሳታፊ አትሌቶች እና ታዳሚዎች ላይ በስለት ጥቃት ሊደርስ ነው የሚል ዘገባ መውጣቱን ተከትሎ እሁድ በጥርጣሬ የተያዙት ስድስት ሰዎች ላይ ፖሊስ አዲስ ማስረጃ ማግኘት አለመቻሉን ዛሬ ዐስታወቀ።  በበርሊኑ ማራቶን ላይ ጥቃት ለማድረስ ሤራ መጠንሰሱን ፖሊስ ደርሼበታለሁ ብሏል ሲል የዘገበው ዕለታዊው ዲ ቬልት (Die  Welt) ጋዜጣ ነበር።

እግር ኳስ

በአፍሪቃ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ቅዱስ ጊዮርጊስ በሜዳው ድል ቀንቶታል። በአዳነ ግርማ ብቸኛ ግብ የኮንጎ ብራዛቪሉ ካራ ብራዛቪልን ድል አድርጓል። ወደ ታንዛኒያ ያቀናው ወላይታ ዲቻ ግን መዲናይቱ ዳርኤሠላም ውስጥ 2 ለ0 ተሸንፏል። የመለሱ ጨዋታ የረቡዕ ሣምንት አዋሳ ስታዲየም ውስጥ ይከናወናል። የቅዱስ ጊዮርጊስ ደግሞ በtm,ሳሳይ ቀን ብራዛቪል ውስጥ።

Champions League Liverpool vs Manchester City
ምስል Reuters/A. Yates

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ኮከብ ግብ አግቢ ኾኖ ለማጠናቀቅ የሚደረገው ግብግብ ተጠናክሯል። ሞሐመድ ሣላኅ በቀዳሚነት እየገሰገሰ ነው። የቶትንሀም ሆትስፐሩ አጥቂ ሐሪ ኬን ግን የሊቨርፑሉ ሞሐመድ ሣላኅን በግብ ክፍያ ልቆ ዘንድሮ ወርቃማውን ጫማ እንደሚያነሳ የሰነቀው ተስፋ አለመምከኑን ተናግሯል። በፕሬሚየር ሊጉ እስካሁን 24 ግቦችን ከመረብ ማሳረፍ የቻለው የ24 ዓመቱ የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን ተሰላፊ ሔሪ ኬን በግብፃዊው የሊቨርፑል አጥቂ በአምስት ግቦች ይበለጣል።

የሁለቱ አጥቂዎች ፉክክር ከመረብ ባረፉ ግቦች ብዛት ብቻ የተወሰነ አይደለም። በፕሬሚየር ሊጉ በሦስተኛነት አጠናቆ በቀጣዩ የሻምፒዮንስ ሊግ ውድድር ተሳታፊነትን ከወዲሁ ለማስረገጥ የሚደረግም ትንቅንቅ ነው። ታዲያ ሊጠናቀቅ ስድስት ጨዋታዎች በቀሩት ፕሬሚየር ሊግ ሊቨርፑል አምስት ጨዋታዎች ይጠብቁታል፤ 67 ነጥብ ሰብስቦ ለጊዜው ሦስተኛ ደረጃ ላይ ሠፍሯል። ባለበት መቆየት ይችላል? ቀሪ አንድ ተስተካካይ ጨዋታ የሚቀረው ቶትንሀም በሚያደርገው ግጥሚያ ይወስናል።

እንደ ሊቨርፑል 67 ነጥብ የያዘው ቶትንሀም በአጠቃላይ ስድስት ጨዋታዎች አሉት። ቀጣይ ተስተካካይ ግጥሚያውን የሚያከናውነውም ሰሞኑን ተደጋጋሚ ሽንፈት ከደረሰበት መሪው ማንቸስተር ሲቲ ጋር ነው። ያም በመኾኑ ታዲያ ለቶትንሀም ፈተና ሳይኾንበት አይቀርም።

71 ነጥብ ሰብስቦ በደረጃ ሠንጠረዡ በሁለተኛነት በሚገኘው ማንቸስተር ዩናይትድ ቅዳሜ እለት የ3 ለ2 ሽንፈት የገጠመው ማንቸስተር ሲቲ የፊታችን ቅዳሜ በሚያደርገው ግጥሚያ  ላለመሸነፍ አለያም ግቡን ላለማስደፈር ተጠንቅቆ መጫወቱ የማይቀር ነው።በአንጻሩ ማንቸስተር ሲቲን በሻምፒዮንስ ሊጉ ባለፈው ሣምንት ጉድ ያደረገው ሊቨርፑል በተመሳሳይ ቀን ቅዳሜ የሚገጥመው እስካሁን ለ13 ጊዜያት ሽንፈት ቀምሶ 11ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው በርመስን ነው። በፕሬሚየር ሊጉ እስካሁን 53 ግቦችን ያስተናገደው በርመስ በሊቨርፑሉ ሞሐመድ ሣላኅ ስንት እንደሚቆጠርበት ለማየት አምስት ቀናት ብቻ መጠበቅ ነው። ሐሪ ኬን መሪው ማንቸስተር ሲቲ ላይ በርካታ ግቦችን በቀላሉ ያስቆጥራል ማለት ግን ይከብዳል። በፕሬሚየር ሊጉ ትናንት አርሰናል ሳውዝሀምፕተንን 3 ለ2 ሲያሸንፍ፤ ቸልሲ ከዌስትሀም ጋር እንድ እኩል ተለያይቷል።

Champions League Liverpool vs Manchester City |
ምስል Reuters/A. Yates

ሻምፒዮንስ ሊግ

በሻምፒዮንስ ሊግ ግጥሚያ ባለፈው ሳምንት በሊቨርፑል የተቀጣው የፕሪሚየር ሊጉ መሪ ማንቸስተር ሲቲ የመልስ ጨዋታውን  ነገ በሜዳው ያስተናግዳል። የፕሬሚየር ሊጉን ዋንጫ ዘንድሮ በአስተማማኛ ኹኔታ ለማንሳት ጫፍ ላይ የደረሰው ማንቸስተር ሲቲ በሻምፒዮስን ሊጉ ግማሽ ፍጻሜ ለመድረስ ግን ነገ ሊቨርፑል ላይ ከሦስት ግብ በላይ ማግባት ይጠበቅበታል። ያን ማድረግ ግን ለማንቸስተር ሲቲ የሚከብደው ይመስላል፤ በሁለት ምክንያቶች። ማንቸስተር ሲቲ በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ዘንድሮ በመሪነት ለብቻው እየገሰገሰ ስለሚገኝ በሚቀጥለው የሻምፒዮንስ ሊግ ውድድር ላይ ተሳታፊ መኾኑን ከወዲሁ አረጋግጧል። በአንጻሩ በፕሬሚየር ሊጉ ሦስተኛ ኾኖ በመጨረስ በቀጣዩ ሻምፒዮንስ ሊግ ተሳታፊ ለመኾን አጣብቂኝ ውስጥ የገባው ሊቨርፑል በነገው ጨዋታ  ወደ ሜዳ የሚያቀናው በ3 ግብ ልዩነት ልቆ ነው። በዚያ ላይ ከማንቸስተር ሲቲ ይልቅ የነገው ጨዋታ ለሊቨርፑል የሞት ሽረት ነው።

የስፔኑ ባርሴሎና በመጀመሪያው የሻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታ 4 ለ1 ካንኮታኮተው የጣሊያኑ ሮማ ጋር ነገ በተመሳሳይ ሰአት ለመግጠም ወደ ጥንታዊቷ ሮም ከተማ ኦሎምፒኮ ስታዲየም አቅንቷል።

FC Barcelona - AS Rom
ምስል picture-alliance/dpa/M. Fernandez

ረቡዕ የጀርመኑ ኃያል ባየርን ሙይንሽን ከሌላኛው የስፔን ቡድን ሴቪላ ጋር ሙይንሽን ከተማ በሚገኘው አሊያንስ አሬና  ስታዲየም ይጋጠማል። ባየር ሙይንሽን የመለስ ጨዋታውን የሚያኪያሂደው በሜዳው በመኾኑ እና በመጀመሪያው ጨዋታ 2 ለ1 በማሸነፉ የተሻለ ዕድል አለው። በሻምፒዮንስ ሊጉ ሩብ ፍጻሜ የመልስ ጨዋታቸውን ከሚያደርጉ ሦስት የስፔን ቡድኖች አንዱ የኾነው ሪያል ማድሪድ በበኩሉ የጣሊያኑ ጁቬንትስን በሜዳው ሣንትያጎ በርናቤው ያስተናግዳል። ጁቬንቱስ ረቡዕ ዕለት ሪያል ማድሪድን በሜዳው ለመጣል ከ3 ግብ በላይ ማስቆጠሮ ይጠበቅበታል። 

ላሊጋ

ቀደም ሲል ለቸልሲ እና ሊቨርፑል ተሰልፎ የተጫወተው ፈርናንዶ ቶሬዝ በዚህ የውድድር ዘመን ማብቂያ አትሌቲኮ ማድሪድን እንደሚለቅ አስታውቋል። የ34 ዓመቱ አጥቂ ፈርናንዶ ቶሬዝ በቡድኑ ለሌሎች ተጨዋቾች መንገድ ለማመቻቸት ገለል ማለቱ ጊዜው አሁን እንደሆነ ተናግሯል። ስለ ወደፊት እጣ ፈንታው ግን ምንም ያለው ነገር የለም።  ሊጠናቀቅ ሰባት ዙር ጨዋታዎች በሚቀሩት የስፔን ላሊጋ አትሌቲኮ ማድሪድ በ68 ነጥብ በሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። መሪው ባርሴሎና 79 ነጥቦች አሉት።  ዛሬ ማታ አትሌቲኮ ቢልባዎ እና ቪላሪያል ይጋጠማሉ።

Bahrain Formel 1 | Vettel siegt
ምስል Getty Images/L. Baron

የመኪና ሽቅድምድም

ዘንድሮ በፎርሙላ አንድ የሚኪና ሽቅድምድም እንደባለፈው ዓመት የዙር ውድድር አጠቃላይ አሸናፊ ይኾናል ተብሎ የተገመተለት የብሪታንያ አሽከርካሪ ሌዊስ ሐሚልተን አጀማመሩ አልተሳካለትም። የመርሴዲስ ተወዳዳሪው ሌዊስ ሐሚልተን በዘንድሮ ሁለት ውድድሮች በጀርመናዊው ሠባስቲያን ፌትል ተሸንፏል። የፌራሪ አሽከርካሪው ሠባስቲያን ፌትል የትናንቱ የባሕሬን ውድድር ድልን ጨምሮ ሌዊስ ሐሚልተንን በ17 ነጥብ ልዩነት እየመራ ነው።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ኂሩት መለሰ