1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

"ሳንገለው አመለጠን የሚሉ ኃይሎች ነበሩ" ጠቅላይ ምኒስትር ዐብይ አሕመድ 

ሐሙስ፣ ጥቅምት 8 2011

ጠቅላይ ምኒስትር አብይ አሕመድ ባለፈው መስከረም 30 ቀን ወደ ቤተ-መንግሥት ካቀኑ ወታደሮች ጋር ተወያይተው ከተለያዩ በኋላ "ወይኔ አመለጠን ሳንገለው የሚሉ ኃይሎች" እንደነበሩ ተናገሩ። ወታደሮቹ ወደ አራት ኪሎ ሲያቀኑ «ከቡራዩ፣ ከሰበታ፣ ከለገጣፎ አርሶ አደር ወጣት መንግሥታችን ተነካ ብሎ ሊዋጋ ተደራጅቶ እየመጣ» እንደነበር አስረድተዋል

https://p.dw.com/p/36kV9
Äthiopien Ministerpräsident Abiy Ahmed wandte sich an einige Mitglieder der äthiopischen Streitkräfte
ምስል Fitsum Arega/Chief of Staff/Prime Minister's Office of Ethiopia

ጠቅላይ ምኒስትር ዐብይ አሕመድ ባለፈው መስከረም 30 ቀን ከነ ትጥቃቸው ወደ ፅሕፈት ቤታቸው የተጓዙ ባለ ቀይ ቆብ ወታደሮች ጋር ተወያይተው ከተለያዩ በኋላ «ወይኔ አመለጠን ሳንገለው የሚሉ ኃይሎች» እንደነበሩ ተናገሩ። ጠቅላይ ምኒስትሩ ወታደሮቹ ወደ ፅሕፈት ቤታቸው የሔዱበት አላማ «ማሻሻያውን ለማስተጓጎል ነው» ሲሉ ተናግረዋል። ጠቅላይ ምኒስትሩ ይኸን ያሉት በዛሬው ዕለት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው በመንግሥታቸው ሥራዎች እና አንገብጋቢ ባሏቸው ጉዳዮች ላይ በሰጡት ማብራሪያ ነው። 

ጠቅላይ ምኒስትሩ ወታደሮቹ ወደ ቤተ-መንግሥት እንዲያቀኑ ትዕዛዝ ያስተላለፉ አሊያም የሸረቡ አካላት ስለመኖራቸው በግልፅ ባይናገሩም «ያን ያደረጉ በቁጥራቸው ያነሱ ሰዎች ቢሆኑም አብዛኛው ወጣት ስለሆነ ደሞዝ ጭማሪ የሚያገኝ መስሎት ተንጋግቶ የመጣ ነው» ሲሉም ተናግረዋል። ጄኔራል ሰዓረ መኮንን ባለፈው ቅዳሜ በጉዳዩ ላይ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ «ግለሰቦች የገፋፉት እና ያርገበገቡት ነው። እነዚህን ግለሰቦች ማን ነው የገፋቸው? የሚለውን አጣርተን እርምጃ እንወስዳለን።» ብለው ነበር። 
«የመጡት ሰዎች ሁሉም ክፉ ሐሳብ ነበራቸው ወይ የሚለው የተሟላ ማስረጃ የለም። ቀድሞ ይኸ ችግር እንደሚያጋጥም የሚያውቅ የለም» ሲሉ የተደመጡት ጠቅላይ ምኒስትሩ እርሳቸው «በሳል እና ጠንቃቃ» ያሉትን የአመራር ሥልት ባይከተሉ ኖሮ ጉዳዩ አደገኛ እንደነበር ገልጸዋል። 

ጉዳዩን ሰፋ አድርገው ሊያብራሩ እንደሚሹ የገለጹት ጠቅላይ ምኒስትሩ «ሁሉ እንኳን ችግር አለባቸው ብለን ብናስብ እና በአየር ወይም በተለየ ኃይል ብንመታ ብንታኮስ እና የተወሰነ ሰው ብንገድል ማሻሻያው ተስተጓጉሏል እንኳ ባንል በራሱ የመከላከያ ኃይል ተቃውሞ የሚገጥመው ማሻሻያ ተብሎ በዓለም ደረጃ ቅቡልነታችንን ገደል ይከተዋል» ብለዋል። 

ወታደሮቹ ወደ ቤተ-መንግሥት ለመሄድ የወሰኑት «በተበተነ አኳኋን» እንደሆነ የገለጹት ጄኔራል ሰዓረ የተፈጸመው ጥፋት ተራ የዲሲፕሊን ግድፈት እንዳልሆነ ጠቅሰዋል።

Äthiopien Abiy Ahmed Premierminister
ምስል picture-alliance/AP Photo/Saudi Press Agency

ጠቅላይ ምኒስትር ዐብይ በብዙ ቅሬታ እና በተሳሳተ መረጃ ወደ ቢሯቸው አምርተዋል ያሏቸውን ወታደሮች ማረጋጋት ቀዳሚው ሥራ እንደነበር ገልጸዋል። «ሰዎች ፑሽ አፕ ተሰራ ሲባል እንደ ዋዛ አይተውታል» ያሉት ዐብይ በስፖርት ወታደሮቹን ለማስከን መሞከራቸውን አስረድተዋል። በምትኩ ሌላ እርምጃ መንግሥታቸው ቢወስድ መዘዙ የከፋ ሊሆን ይችል እንደነበርም ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ተናግረዋል። በብሔራዊው የቴሌቭዥን ጣቢያ በቀጥታ በተላለፈው ንግግራቸው «ብዙዎች ውጭ ሆነው የሚተርቱትን ተረት ብናደርግ የሚፈጠረው አደገኛ ነው» ያሉት ጠቅላይ ምኒስትሩ «መጀመሪያ ስሜትን አርግበን ከቀዘቀዘ በኋላ ውይይት አካሔድን 'ራሱ እከሌ ቀሰቀሰኝ፤ እከሌ አደራጀኝ' ብሎ አውርቶ ለሕግ እያቀረበ ነው አሁን» ሲሉ የተከተሉትን ሥልት አብራርተዋል። ጄኔራል ሰዓረ መኮንንም ከወታደሮቹ ድርጊት በኋላ በቁጥጥር ሥር የዋሉ ሰዎች መኖራቸውን ባለፈው ቅዳሜ ገልጸው ነበር። ጄኔራል ሰዓረ «እስካሁን በቁጥጥር ስር ያስገባናቸው ከፍተኛ አመራሮች አሉ። በቀጣይ ደግሞ በየደረጃው የማጥራት ሥራውን እንቀጥልበታለን» ቢሉም በቁጥጥር ሥር የዋሉ ሰዎች ብዛትንም ሆነ ያላቸውን ወታደራዊ ሥልጣን ግን አልገለጹም። 

የልዩ ኃይል አባላቱ «ቤተ-መንግሥት ሲገቡ ትጥቃችሁን ከፈታችሁ በኋላ የሆነ ሰው ሊያነጋግራችሁ ይፈልጋል ሲባሉ ትጥቃችንን አንፈታም» ብለው እንደነበር ያስታወሱት ጄኔራል ሰዓረ ስናይፐር እና ብሬልን ጨምሮ የተለያዩ ዘመናዊ የጦር መሳሪያዎች ታጥቀው እንደነበር ዘርዝረዋል። «ቀስ አርገን ትጥቃቸውን እንዲፈቱ አደረግናቸው» ያሉት ጄኔራል ሰዓረ በምኒስትሮች ምክር ቤት ስብሰባ ላይ የነበሩት ጠቅላይ ምኒስትር ዐብይ አሕመድ እንዳገኟቸውም ገልጸዋል።  

ኩነቱ «ጥይት ሳይተኮስ፤ ሰው ሳይሞት» እልባት ማግኘቱን የገለጹት ጠቅላይ ምኒስትር ዐብይ አሕመድ ግን የከፋ ኹኔታ ሊፈጥር ይችል እንደነበር በዛሬው ዕለት በይፋ ተናግረዋል። በዕለቱ ጉዳዩን ለጋዜጠኞች ሲያብራሩ «በከፍተኛ መዝናናት እና መሳቅ» እንደነበር ያስታወሱት ዐብይ «ውስጤ እርር ድብን እያለ» ሲሉ ትክክለኛ ስሜታቸው የተለየ እንደነበር አመልክተዋል። ጠቅላይ ምኒስትሩ «ከቡራዩ፣ ከሰበታ፣ ከለገጣፎ አርሶ አደር ወጣት መንግሥታችን ተነካ ብሎ ሊዋጋ ተደራጅቶ እየመጣ ነው» ሲሉ ሕዝቡን ለማረጋጋት መሞከራቸውንም አስረድተዋል። 

የዕለቱን ኩነት «አቃለን አንመልከተው» ያሉት ዐብይ «በነገራችን ላይ ወይኔ አመለጠን ሳንገለው የሚሉ ኃይሎች ነበሩ» ሲሉ ተናግረዋል። ጠቅላይ ምኒስትሩ «ሳንገለው አመለጠን» ብለዋል ያሏቸው ኃይሎችን ማንነት ግን በግልፅ አልጠቀሱም። የተባሉት «ኃይሎች» በመከላከያ ሠራዊቱ ውስጥ የሚገኙ ስለመሆናቸውም ለጊዜው የታወቀ ነገር የለም።

እሸቴ በቀለ

ሸዋዬ ለገሠ