1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሳላፊስቶች በጀርመን አገር

ሰኞ፣ ጥቅምት 12 2011

ሳላፊስቶች በጀርመን አገር ወጣቶችን ሥራዬ ብለው ተከታትለው እነሱን በየአለበት ማጥመድ የጀመሩበትም ጊዜ ነው፡፡የዛሬ ስምንት አመት 2010 ዓ.ም. እ.አ.አ ፡ይህን ትርዕይት እንደገና ማየት የሚፈልግ ሰው ዩ ቲዩብ ውስጥ ገብቶ ፊልሙን አዞ ዛሬም መከታተል ይችላል፡፡

https://p.dw.com/p/36xuo
Köln Salafisten Veranstaltung
ምስል picture-alliance/dpa

የድምጽ ማጉያ ማይክሮፎኑን ከግራ ወደ ቀኝ እጁ፣ከቀኝ ወደ ግራው እያቀባበለ፣«አሁን የምነግርሽን ጮክ ብለሽ ድገሚው» እያለ በኃይለ ቃል አንድ ሰው በአንዲት ልጅቱዋ ላይ ይካል። ይህን የሚለው ሰው በቅርቡ ሃይማኖቱን ቀይሮ እስላም የሆነው ዜግነቱም፣ትውልዱም ጀርመን  የሆነው ፒየር ፎግል የተባለው ግለ,ሰብ ነው። እዚህ ጀርመን አገር፣ሔስን በሚባለው ክፍለ-አገር፣ በኦፍን ባህክ ከተማ፣ አደባባዩ ላይ «እኔ እስላም ነኝ.» የሚለውን የሰባኪውን ቃል በአደባባይ ጮክ ብላ እንድትደግመው የተፈረደባት ወጣቱዋ ልጅ ገና ድምጽዋን ስታሰማ የተሰበሰበው ሰው ደስታውን ሲገልጽ ታይቷል። 
ይህ ሁሉ የሆነው የዛሬ ስምንት አመት 2010 ዓ.ም. እ.አ.አ ነው፡፡ይህን ትርዕይት እንደገና ማየት የሚፈልግ ሰው ዩ ቲዩብ ውስጥ ገብቶ ፊልሙን አዞ ዛሬም መከታተል ይችላል፡፡
ጊዜው በትክክል ሳላፊስቶች በጀርመን አገር ወጣቶችን ሥራዬ ብለው ተከታትለው እነሱን በየአለበት ማጥመድ የጀመሩበትም ጊዜ ነው፡፡ ስድስት አመት በተከታታይ እስከ 2016 ዓ.ም እ.አ.አ ድረስ ይህ የሳላፊስቶች እንቅስቃሴ እጅግ በሚያሳስብና ድፍረት በተሞላበት ቆራጥነት፣እነሱ አደባባይ ላይ ወጥተው ማንነታቸውን ያሳዩበት ጊዜም ነው፡፡
እንደ ጀርመኑ ተወላጅ እንደ ፒዬር ፎግልም፣ ነጭ ጀለባ ልብሳቸውን ያሸረጡ፣ ጢማቸውንም አለቅጥ ያሳደጉ ሰዎች፣ በትላልቅ የጀርመን አደባባዮችንና በየገበያው ቦታዎች ብቅ ብለው አላፊ አግዳሚውን ሰው«አንብብ» በሚለው ጥሪአቸው ቅዱስ ቁራንን በነጻ በትነዋል፡፡ አብረውም ስብከታቸውን በኃይለ-ቃልና ወኔ በሚቀሰቅሱ አነጋገሮች ወደ መቀባባትም ተሸጋግረዋል፡፡ በተለይ ወጣቱን ትውልድ አድነው መያዙን ቀጠሉበት፡፡
በኋላም እንደሚታወቀውና እንደተደረሰበትም «የእስላም ትምህርት መስጫ ሴሚናር» የሚለውን የሽፋን መሰባሰቢያ መድረክም ከፍተውም ወጣቱን ትውልድ መሳቡን ተያያዙት፡፡
አሁን ብልሃታቻውን ቀይረው ሌላ መንገድ መከተል ጀመሩ፡፡ ስፖርት በተለይ የእግር ኳስ ቡድን ማቋቋም አንደኛው የማጥመጃ ዘዴአቸው ሆነ፡፡ሽርሽር መውጣትና ምግብ አንድ ላይ ቀቅሎ መብላት፣አሳት አንድዶም ከሃይማኖት ጓደኞቻቸው ጋር ጥብስ አዘጋጅቶ፣ሜዳ ላይ መገባበዝ ሌላው የመተዋወቂያ ድብቅ ዘዴአቸው ሆነ፡፡
ዋና ዓላማቸው የኋላ ኋላ አንድ ቀን የእራሳቸውን „ዓለም“ በጀርመን አገር ፈጥረው፣በመንግሥት ላይ ሌላ „ሁለተኛ የእራሳቸውን መንግሥት«እዚሁ አገር ፈጥረው «በስውር» ጠንክሮ ለመውጣት ነበር፡፡ በዚህ አካሄዳቸው ላይ ጀርመኖች፣ ከዚያና ከዚህ አሁን እንደሚሰማው እርግጠኛ ናቸው፡፡
ድርጊታቸው ሕገ ወጥ ነው እዚህ ከተባለ ወዲህ አሁን እነሱ ተመልሰው ኅቡዕ ገብተዋል፡፡ እነዚያ ዱሮ አደባባይ ላይ ወጥተው ፣ጠረጴዛቸውን ዘርግተው ቅዱስ ቁራንን „አንብቡ“ እያሉ በነጻ መንገድ ላይ የሚንጎራደዱት አክራሪዎች ፣ዛሬ ጀርመን አገር የትም ቦታ አይታዩም፡፡ የጸጥታ ሰዎች ሲጠየቁ «ተሰውረዋል»ይላሉ፡፡
2016 ዓ.ም. ላይ አካሄዳቸው ፈጽሞ ያላማረው የአገር አስተዳደሩ ሚኒስትር „ዕውነተኛ“ ወይም«„ትክክለኛው ሃይማኖት» በሚለው ሽፋናቸው ሥር  ወጣቱን ተንቀሳቅሰው ያጠምዱ የነበሩትን ድርጅት በሕግ እንዲከለከል አድርጎአል፡፡« ይህ ድርጅት» የሕግ አስከባሪው አካል ያኔ እንደአለው «የሚያራምደው ርዕዮተ ዓለም፣ የጀርመንን ሕገ-መንግሥት ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ፣ሥርዓቱን የሚያናጋና ከዚያም አልፎ በሶሪያና በኢራክ ለጅሃድ ጦርነት ወጣቱን ትውልድ ቀስቅሶና ሰብስቦ እነሱን የሚጋብዝ አደገኛ የሆነ የሃይማኖት እንቅስቃሴ ነው»  ብሎ ፈርጆበታል፡፡
ከዚያን ጊዜ ወዲህ ይህ ማህበር አሁን የት እንደደረሰ ሳይታወቅ ተሠውሮ ከመድረኩ ላይ ጠፍቶአል፡፡ያም ሁኖ ተደብቆአል እንጂ ድርጅቱ ተኖ አልጠፋም፡፡  «ብዙዎቹ አክራሪዎች » ሚስተር ካን ኦርሆን ለዲ ደብሊዩ እንደአሉት»የሰው ዓይን ውስጥ እንዳይገቡ ሰዎቹ ትንሽ ዞር አሉ እንጂ ውስጥ ውስጡን የተንኮል ሥራቸውን ከማካሄድ አሁን አርፈው አልተኙም፡፡“
ሚስተር ካን ኦርሆን ፣ በቦን ከተማ የተከፈተው «ሓያት» የሚባለው ቢሮ ውስጥ ተቀጥረው የሚሠሩ ሰው ናቸው፡፡ ድርጅቱ ሓያት በነገር ተሳክረው፣በጥላቻ ፕሮፓጋንዳና ቅስቀሳ ናላቸው ዞሮ ፣ነፍሳቸውን የሸጡ ወጣት ሞሲሊሞችን መክሮ እና ገሥጾ ወደ ሰላማዊ ኑሮአቸው እንዲመለሱ ተንከባክቦ እነሱን የሚረዳ ማህበር ነው፡፡ ሓያት የሚለውም ሰሌዳም የቢሮው በር ላይ በትናንሽ ፊደል ከመጻፉ ሌላ ይህን ቢሮ ቦን ከተማ ውስጥ ፈልጎ ለማግኘት ቀላል አይደለም፡፡ አድራሻውን በቀላሉ የቴሌፎን ማህደርም ውስጥ ገብቶ  ማግኘት አይቻልም፡፡ወይም በአለመመዝገቡ ኢንተርኔት ውስጥም ቢፈለግ አይገኝም፡፡
ይህም የሆነበት ምክንያት አለው፡፡ ከቀድሞ ተዋጊ ጂሃዲስቶች ፣ወይም ሳላፊስቶች ሸሽተው ያመለጡትን ወይም ጥለው ሊወጡ የሚፈለጉትን ወጣቶች ደህንነታቸውን አደጋ ላይ እንዳይወድቅ ለመጠበቅ ነው፡፡እንደሚታወቀው ከዳታችኋል ተብለው መቀጣጫ እንዳይሆኑ ነው፡፡ ሊቀጡአቸውም የሚፈልጉ ኃይሎች እዚህ አሉ፡፡
«አንዳንዶቹ ነፍሳቸውን ለማዳን ድርጅቱን ለቀው ይውጡ እንጂ፣የሳላፊሲቶቹ ምልመላ „ ሚሲተር ካን ለጣቢያችን እንደ አሉት»አሁንም እንደ ዱሮ እንደ አለ ነው፡፡ በቤተሰብ ዝምድና እና በጓደኛት ትውውቅ፣በዘመናዊው መገናኛ መስመሮች እና በተለያዩ ዘዴዎች፣ በዋትስ አፕ እና በቴሌግራም ጭምር ወጣቱን ትውልድ አጥምዶ መያዙን ሳላፊስቶቹ ያውቁበታል፡፡ «ዱካቸውን ግን የት እነደአሉ ፈልጎ ለማግኘት  ለጸጥታ ፖሊሶች አስቸጋሪ ነው፡፡
„የሳላፊስቶቹ ዋና ዓላማ አሁንም ቢሆን እንደ አለፉት ጊዜያት“ የኖርድ ራይን ቬስት ፋለን የጸጥታ ፖሊስ በአለሥልጣን ሚስተር ቡርክሓርድ ፍራየር ለጣቢያችን እንደአሉት „ ትኩስ ኃይል ሰብስቦና አደራጅቶ ወደ ጦር ሜዳ መርቆ ለመሸኘት ነው፡፡ ያም ሁኖ ግን ቁጥራቸው እንደ አለፉት ጊዜያት ትልቅ አይደለም፡፡ትንሽ ነው፡፡“

በብዛት አሉ ተብሎ የሚነገርበት አካባቢ፣በጀርመን አገር ቢኖር በኖርድ ራይን ቬስት ፋለን ነው፡፡ በዚያውም መጠን አክራሪዎቹ ሳላፊስቶች የተሰባሰቡበት ዋና መነሓሪያ መንደሮቻቸው የሚገኙት በዚሁ ክፍለ-አገር ውስጥ ነው፡፡ አሉ ከሚባሉት አንድ ሺህ ሳላፊስቶች ውስጥ ወደ መካከለኛው ምሥራቅ ወደ „እስላማዊ ግዛት“ ተብሎ ወደ የሚጠራው አካባቢ ለውጊያ አቆራርጠው ከሄዱት ሦስት መቶ ሰዎች የተነሱት ከዚሁ ክፍለ አገር ነው፡፡
ቦንብ በማፈንዳትና ሽብር በመፍጠር ከተሰማሩት የእስላም እንቅስቃሴ  ውስጥ አብዛኛዎቹ፣ ፖሊስ እንደሚለው ተደራጅተው የወጡት ከሳላፊስቶቹ ጉያ እና ብብት ነው፡፡ በርሊን ከተማ ላይ በነጮች የገና በዓል አካባቢ ፣ በታህሣሥ ወር የዛሬ ሦስት አመት ገደማ አኒስ አሚር የሚባለው የቲኒዚያ ተወላጅ፣የአሥራ ሁለት ሰዎች ሕይወት በትልቅ ካሚዮን ደፍጥጦ ያጠፋው ልጅ፣ እዚያ በሳላፊስቶቹ ተመልምሎ ለዚሁ የወንጄል ሥራው ወደ ዋና ከተማ ወደ በርሊን የተላከው ከዚያ ነው፡፡
«በእርግጥ ሳላፊስት ነኝ ያለ ሰው ሁሉ ሽብር ፈጣሪ ቴሮሪስት አይደለም፡፡ ግን ደግሞ አክራሪ እስላሞች በሙሉ የበቀሉትበት ቦታና ተኮትኩተው የወጡበት ዋሻቸው ከሳላፊስቶቹ መንደር ነው፡፡» እዚህ እንደዚህ ዓይነቱን አመለካከት እና አነጋገር ስለሳላፊስቶች ሲነሳ የሚሠነዝሩ የሕብረተስቡ ክፍሎች እዚህ ብዙ ናቸው፡፡የጸጥታ ፖሊሶች ይህን ዓይነቱን አስተያየት ያራምዳሉ፡፡ አባባሉንም ከሚወረውሩት ክፍሎች መካከል እነሱ ቅርበት ስለአላቸው አንደኛው ናቸው፡፡ አስተማሪዎች እና ወላጆች ሌሎቹ የሕብረተሰብ ክፍሎች ናቸው፡፡ተንከራተውና ተመልሰው የመጡትን የሚንከባከቡ ድርጅቶችና ፣እንዲሁም የፖለቲካ አማካሪዎችም ይህንኑ ጉዳይ ያነሳሉ፡፡
ግን አንድ ማለት የሚቻል ነገር ቢኖር፣ብዙ ቦታዎች ከአሉትና ከሚታዩት የተለያዩ የእስላም እምነቶች ውስጥ እንደ ሳላፊስቶቹ „ወደኋላ የቀረና“ ቅዱስ ቁራን ላይ ከዛሬ  ሺህ አመታት በፊት የሠፈሩትን ሕግጋትና የነብዩ መሓመድን ትምህርቶች ፣ከእሳቸው በኋላም የተነሱት ተከታዮቻቸውን የአሥፋፉትና የደነገጉትን ደንቦች፣ ቃል በቃል- እዚህ እንደሚባለው- በዚህ በያዝነው ክፍለ-ዘመን በዚህች ምድር ላይ በሥራ ላይ ተተርጉመው ማየት የሚፈልጉ ኃይሎች ቢኖር እነሱ ናቸው፡፡ እንደዚህ ዓይነቱ የእስላም ርዕዮተ-ዓለም ደግሞ ከማንኛውም ዘመናዊ አመለካከት ጋር አብሮ የማይሄድና የማይጣጥም ፣እንዲያውም የተለያዩ እምነትን የሚከተሉ ሰዎችን የሚያቀራርብን ሳይሆን የሚያራርቅ እምነት ነው፡፡ አንዳንድ የሳላፊስት ሃይማኖት ተከታዮች እዚህ እንደሚባለው ሌሎቹ ላይ ሳይደርሱ የራሳቸውን የግል ሕይወት፣መንፈሳዊ ኑሮአቸውን እላይ እንደተባለው፣ለእራሳቸው ሲሉ እሱን ተቀብለውና ተከትለው መኖር ይፈልጋሉ፡፡ ችግሩ እነሱ አይደሉም፡፡ ችግሩ ያለው ሌላ ቦታ ላይ ነው፡፡ ቁጥራቸው ትንሽ ነው የማይባሉ የፖለቲካ ሳላፊስቶች ከዚያ ከግል ሕይወታቸው አልፈው ማንኛውንም ምድራዊ ሕግጋቶችን ሽረው እና ፍቀው፣የጀርመንንም ሕገ-መንግሥት ሰርዘው በመለኮታዊ ሕግ እነሱ እንደሚሉት በሻሪያን ሕግ መጽሓፉ እንደሚለው ተክተውት ለመኖር ይፈልጋሉ፡፡ ይህን ግን እንዲያደርጉ እዚህ ማንም ዝም ብሎ አያያቸውም፡፡
በሩና መንገዱ ለብዙ ነገሮች ክፍት ነው፡፡ዓላማቸውን ከግቡ ለማድረስ የጅሃድ ጦርነት ከማወጅ የማይመለሱ ሳላፊስቶች አሉ፡፡አብዛኛዎቹ „እስላማዊ መንግሥታቸውን“ ለመቋቋም ጦር ከመምዘዝ ፣ኃይል ከመጠቀም ወደኋላም አይሉም፡፡ቁጥራቸው አድጎ አሁን ወደ ሦስት ሺህ የሚጠጉ የሳላፊስት ተከታዮች በኖርድ ራይን ቬስት ፋለን እንደሚኖሩ ፖሊስ እዚያ ይገምታል፡፡ወደ ስምንት መቶ የሚሆኑት ደግሞ ከእነሱ መካከል መሣሪያ አንስተው ከመተናነቅ የማይመለሱ ናቸው ይላል፡፡
ወደ ሶሪያና ወደ ኢራክ የጂሃዲስቶቹን ጥሪ ተከትለው ከወረዱት ሰዎች መካከል አብዛኛዎቹ የተነሱት ከዚሁ ክፍለ አገር ነው፡፡ አሁን አንዳንድ እናቶች ተስፋ ቆርጠው ልጆቻቸውን ይዘው ወደ ጀርመን አገር ተመልሰው ገብተዋል፡፡
„ከኢራንና ከሶሪያ የካለፊት መንግሥት የሚባለው ነገር መውደቁን አይተው ተስፋ ቆርጠው የተመለሱትን እናትና ልጆቻቸውን ተቀብለን እነሱን እንደገና ሕይወታቸውን እንዲመሩ ዕድል መስጥት ይኖርብናል፡፡ሕክምና እና ዕርዳታ የሚያስፈልጋቸውን ወደ ሓኪም ቤት፣ሕጻናቱንም ወደ ሕጻናት ማሳደጊያና ሌሎቹን ደግሞ ወደ ትምህርት ቤቶች መላክ ይገባናል፡፡በሌላ በኩል ግን „ ወይዘሮ ኮሌታ ማነማን ለጣቢያችን እንደ አሉት „ እነዚህ ከጦር ሜዳ የተመለሱ ሴቶች ሕጻናቱንና ወጣቱን ትውልድ በጥላቻ ትምህርታቸው ቀስቅሰውና በክለው ወደማይሆን ነገር ውስጥ እንደገና መልሰው እንዳይከቱአቸው እነሱን ነቅተን መጠብቅም ይኖርብናል፡፡“
ማን በአሁኑ ሰዓት ምን እንደሚያስብና በምን ሁኔታ ላይ በትክክል እንደሚገኝ፣ለጀርመን ፖሊስ ይህን ለማወቅ አስቸጋሪ የሆነበት ይመስላል፡፡ በዚያ ላይ አለበቂ ማሥረጃ በጥርጣሬ ብቻ አንድን ሰው አደገኛ ነው ብሎ ይዞ እሱን እሥር ቤት መወርወር ሕገ-መንግሥቱ ይህን እርምጃ ይከለክላል፡፡

ሴቶቹን ሶሪያና ኢራክ ነበራችሁ ብሎ አለበቂ ማሥረጃ እነሱን ይዞ ማሠር ጀርመን አገር አይቻልም፡፡ተዋጊ ወንዶቹን ግን እራሳቸው በለቀቁት የፕሮፓጋንዳ ቪዲዎቻቸው ላይ ተመሥርቶ እነሱን መክሰስ ይቻላል፡፡አንዳንዶቹ እጅ ከፍንጅ በዚሁ ቪዶዎቻቸውና የቅስቀሳ መልዕክታቸው ላይ የማይያዙ መስሎአቸው „ ይህን አድርጌአለሁ፣ያንን ፈጥሬአለሁ „ እያሉ በመፎከራቸው ተይዘው እነሱ አሁን እሥር ቤት ገብተዋል፡፡ ቁጥራቸውም ሃያ አራት ደርሶአል፡፡ግን እዚያ እሥር ቤት ውስጥ ሁነው፣የሚሠሩትን ሥራ ለማወቅ አስቸጋሪ ሁኖአል፡፡ከውጭ የሚመጡ ብዙ ጠያቂዎች አሉአቸው፡፡ „ከእህቶችና ከወንድሞች“ ማለት ከሳላፊስት ተከታዮች ደብዳቤም ጭምር ይጻፍላቸዋል፡፡የዕርዳታ ገንዘብም ይሰበሰብላቸዋል፡፡እዚያ እሥር ቤት ተጠናክረው ይውጡ፣ወይም ሌሎች እሥረኞችን ይመልምሉ ምንም የሚታወቅ ነገር የለም፡፡ 

ዋና መሰባሰቢያ ቦታቸው እንደ ቩፐርታልና እንደ ሙንቺን ግላድባህ፣እንደ ዲንስላክና እንደ ዶርትሙንድ ያሉ ትላልቅ ከተማዎች ናቸው፡፡ከሁሉም ግን የቀድሞው ዋና ከተማ ቦን ያሉ ሳላፊስቶች  ሌሎቹን በቁጥር ይበልጣሉ፡፡ 
ከቦን ተነስተው ነው ሁለቱ ወንድማማቾች ያሲንና ሙኒር ቹካ በ2008 ዓ.ም. አፍጋኒስታንና ፓኪስታን ድንበር ላይ ቆመው ጀርመን በቦንብ ደብድቡ የሚለውን አዋጃቸውን በቀረጹት ቪዲዎቻቸው ላይ የለቀቁት፡፡እዚያው ቦን ከተማ ነው ሰባኪው አቡ ዱጃና „ቁራንን አንብቡ“ የሚለውን ጥሪውን ይዞ አደባባይ ላይ ከብጤዎቹ ጋር የወጣው፡፡ „ኮከብ ተናጋሪዎች „ የሚባሉት ሰዎቻቸው በብዛት ቅስቀሳ ሲያደርጉ የታዩበት ቦታ ቦን ከተማ ላይ ነው፡፡ በተለይ የዱሮ ቡጢ ስፖርት ተጫወቹ፣ሃይማኖቱን የቀየረው፣ በቀይ ቀለም ጸጉሩ የሚታወቀው፣የጀርመኑ ዜጋ ፒየር ፎግል ረጅም ሰበካውን ያካሄደው እዚያው ቦን ላይ ነው፡፡

Polizisten kontrollieren Salafisten in Köln
ምስል Getty Images/M. Wienand
Düsseldorf Mutlu Günal Verteidiger mit Salafistenprediger Sven Lau (L)
ምስል picture-alliance/dpa/F. Gambarini
Syrien IS Kämpfer in Raqqa
ምስል picture-alliance/AP Photo
Berlin Salafisten verteilen Koran Bücher
ምስል Getty Images/A. Berry

ፒየር ፎግል ሮጦ ሮጦ አሁን የደከመው ይመስላል፡፡እርግጥ አሁንም ቢሆን በዩቲዩብ ካናል ሰበካውን ዱሮ እንደሚያደርገው መስበኩን አላቆመም፡፡በፌስቡክም ላይ ስለ „ትክክለኛው እና ሐቀኛው ሃይማኖት“ እሱ እንደሚለው „ትምህርት“ መስጠቱን አሁንም ጨርሶ አላቆመም፡፡ግን እንደ ዱሮው በየትምህርት ቤቶች ደጃፍ ቆሞ ተማሪዎችን አቁሞ ማነጋገሩን አቁሞአል፡፡ በተለይ ከአንድ ትምህርት ቤት በራፍ ላይ፣ ታንንበሽ ከሚባለው መንደር -እዚያ ብዙ የውጭ አገር ልጆች ይማራሉ ፣አብዛኞቹም የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ናቸው- ሁልጊዜ እሱ፣ አስተማሪዎች እንደአሉት፣ ከዚያ አይጠፋም ነበር፡፡
ብዙዎቹን ልጆች አስተማሪዎች እንደአሉት፣«እኔ ማን ነኝ የሚለው፣ የማንነት ጥያቄ „ ከሁሉም ነገር እነሱን እጅግ አድርጎ  የሚያሳስባቸው ጥያቄ ነው፡፡ » ጀርመን ነኝ! ወይስ የውጭ አገር ሰው!...የእስላም ሃይማኖት ተከታይ ወይስ አውሮፓ ዜጋ!...“ ወዘተ የሚሉ ጥያቄዎች የሃይማኖት „…ወጣቱን ትውልድ እዚያ ግራ የሚያጋቡ እና የሚያስጨንቁ ጥያቄዎች ናቸው፡፡“
አንድ ዘመናዊ ሰው ፣ማንነቱ አንድ ነገር ብቻ ሳይሆን ብዙ መለያ ምልክቶች አሉት፡፡ ግን ለወጣቱ ትውልድ ፣ገና ብዙ ነገሮች ግልጽ ላልሆነላቸው ልጆች „…የሳላፊስቶቹ ቀስቃሾች መጥታው፣እኛ አለንልህ፣ዕውነተኛውና ትክክለኘው ሃይማኖት ያውልህ፣ይህ ክልክል ነው፣ያን አድርግ፣ ይን አትንካ፣እሱ ሓራም ነው ፣ያ ደግሞ ሃላል ነው….እያሉ፣ በቀላላ ይስቡታል፡፡“ ፌስቡክ ላይ እንደዚህ ዓይነቱ ነገርም በብዛት ተለጥፎም ይነበባል፡፡
በአንዴ እነዚህ ወጣት ልጆች፣አስተማሪዎች ተከታትለው እንደአዩት ፣ „ ሳላፊስቶቹን ከገጠሙ በኋላ ፍጹም ልዩ የሆነ የሊህቃኖች ቡድን ውስጥ የገቡ ይመስላቸዋል፡፡“
በርንድ ባውክኔችት „የእስልምናን ሃይማኖት“ በቦን ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የሚያስተምሩት አስተማሪ እንደ አሉት „…በማይሆን አስተሳሰብ አንዴ የተጠመደ ተማሪ፣ወይም የተጠመዱ ተማሪዎች፣እነሱን ከዚያ ከለከፋቸው በሽታ ጎትቶ ለማውጣት ቀላል አይደለም፣ እጅግ ከባድ ነው…“ ይላሉ፡፡
ስለዚህ ወጣቱን ትውልድ ከአክራሪነት እና ከሽብር ፈጣሪነት ለማራቅ መንግሥትና ፣ሕዝባዊ ድርጅቶች ወላጆችም አንድ ላይ ሁነው ተያይዘው ብዙ ሥራ መሥራት ይኖርባቸዋል፡፡ ሜዳውን ለአክራሪ ሳላፊስቶች እንዲጨፍሩበት መልቀቅ አያስፈልግም፡፡

Symbolbild Mädchen Frauen Salafismus
ምስል picture-alliance/dpa/B. Roessler

 
„ከ2003 ወይም ከ2004 ጀምሮ በአጠቃላይ በሳላፊስቶች ዘንድ ይታይ የነበረው ድፍረት ያለው እንቅስቃሴአቸው አሁን “ የጸጥታ ፖሊሱ በአልሥልጣን ሚስተር ቡርካሃርድ ፍራየር እንደአሉት፣“እየቀዘቀዘ መጥቶአል፡፡ ቀደም ሲል እነዚህ ሰዎች “  በአለሥልጣኑ እንደአሉት“ ያተኩሩት የዲሞክረሲ ሥርዓቱን እዚህ አፍርሶ የጀርመንን ሕብረተሰብ ለመቀየር ሳይሆን ወደ ሶሪያ ወርዶ እዚያ በመካከለኛው ምሥራቅ የካሊፋት መንግሥትን ለማቋቋም ነበር፡፡ „
ከዚያም በላይ ምንም እንኳን የአንዳንዶቹ ቤተሰቦች እስላም ቢሆኑም ይህኛው ትውልድ ልጆቹ ስለ ሃይማኖቱ ምንም የማያውቁ ጠበብቱ እንደአሉት „መሓይም ነበሩ፡፡“ 
በእስላም ሕግጋት ብቻ የሚተዳደር „የካሊፋት መንግሥት“ የማቋቋም ሕልም ግን በጦርነት እዚያ ድል ከተመታ ወዲህ  ያሕልም እንዳለ አሁን ተኖ ጠፍቶአል፡፡ 
„አሁን የተያዘው ዓላማ ግን“ የፖሊስ ተጠሪው ለጣቢያችን እንደ አሉት “ እዚሁ ጀርመን አገር ውስጥ ከቁጥጥር ውጭ የሆነ የአክራሪዎች ክንፍ በሥውር ለመመሥረት ነው፡፡“ 
የሥውር ድርጅት መሥርተው፣አረሳስተው „ቦንብ ያፈንዱ“ ፣ወይም ቤታቸው ውስጥ ተቀምጠው ለካሊፋት መንግሥት ምሥረታ የቆየ ሕልማቸውን ያልሙ፣ወይም ደግሞ ሕይወታቸውን አስተካክለው እዚህ እንደማንኛውም ወጣት ተምረው ጥረው ግረው ትዳር ይዘው ይኑሩ፣ወይም ደግሞ በቃን ብለው ጀርመንን ጥለው ወደ መካከለኛው ምሥራቅ ይመለሱ ምንም የሚታወቅ ነገር የለም፡፡  
ይህን  ተከታትሎ ደግሞ ማወቅ ወይም ማክሸፍ የጸጥታ ፖሊሶች ሥራ ነው፡፡ እንቅስቃሴዎች በአንዴ ቦግ ብለው ይነሳሉ፡፡የወጣት ትውልድ እንቅስቃሴ ደግሞ -ከታሪክ እንደሚታወቀው - በአንዴ ብድግ ብሎ የተነሳውን ያህል ትውልዱ ሲቀየር ኩምሽሽ ብሎ ይደርቃል፡፡ የግራና የቀኝ አክራሪዎች ታሪክ ጥሩ ምሳሌ ነው፡፡ሃይማኖትን እና ዘርን አስታከው የሚነሱ ወጣቶችም መጨረሻ እላይ እንደተተረከው ነው፡፡

ይልማ ኃይለ ሚካኤል
አርያም ተክሌ