1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሜርክል ፋታ የሚያገኙ አይመስልም

ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 25 2011

እስካሁን ባለው ሂደት የጀርመን መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል ከፖለቲካው ዓለም ቀስ በቀስ የመውጣት ሃሳብ በዕቅዱ መሠረት እየተከናወነ ይመስላል። ሆኖም እስከ ምርጫው ድረስ የሚኖራቸው የመራኂተ መንግሥትነት ሚና ቀላል እንደማይሆን ነው የDWዋ ማኑዌላ ላይንሆስ በዘገባዋ የምታመለክተው። በየቦታው የተጠመዱ መሰናክሎች ስጋት እንደሚሆኑም ገልጻለች።

https://p.dw.com/p/3B0oj

ሜርክል በ2019

Deutschland | Neujahrsansprache Angela Merkel
ምስል picture-alliance/dpa/AP Photo/Pool/J. MacDougall

መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል የፓርቲያቸው የክርስቲያን ዴሞክራትን ፕሬዝደንትነት እንደተመኙት አነግሬት ክራም ክራንባወር ተረክበዋል። AKK በሚለው የስማቸው ምህጻር የሚታወቁት በአነግሬት ክራም ክራንባወር የሜርክልን ወግ አጥባቂ ፖለቲካ ላይ የሚነሳውን ትችት በጥንቃቄ የሚይዙ ጥብቅ ተጓዳኛቸው ናቸው። ሜርክል ጎርጎሪዮሳዊው 2018 ሲጠናቀቅ አዲሱን ዓመት አስመልክተው ለሕዝባቸው ባስተላለፉት መልእክት አንዴ ሌላውን እየተካ እና እየለወጠ መዝለቁ የዴሞክራሲ ሂደት መሆኑን ጠቋሚ ንግግር አድርገዋል።

«ዴሞክራሲ በለውጥ ውስጥ ይኖራል፣ እናም ሁላችንም በጊዜው እንቆማለን። ከእኛ ቀድመው ሠርተው ባለፉት ላይ የበኩላችንን በመገንባት የአሁኑን በመቅረፅ ከእኛ ለሚረከቡትም እናበጃለን። የእኔ መመሪያ በዘመናችን የሚገጥሙንን ተግዳሮቶች መወጣት የምንችለው አብረን ስንቆም እና ከድንበር አልፈንም ከሌች ጋር በጋራ መሥራት ስንችል ነው። »

ሆኖም ሜርክል ይህን ቢሉም በፓርቲያቸው ውስጥ ተቀናቃኛቸው የነበሩት ፍሬድሪክ ሜርስ ተጠናክረው መምጣታቸው ለእሳቸውም ሆነ ለተኳቸው የፓርቲያቸው አዲስ ፕሬዝደንት ስጋት መሆኑ ነው የሚነገረው። ሜርስ የምክር ቤቱ ምልዓተ ጉባኤ በተገኘበት በአንዱ የመንግሥት መሥሪያ ቤት በሚኒስትርነት ለማገልገል የመፈለጋቸው ጥያቄ በAKK ተቀባይነት አላገኘም። እንዲያም ሆኖ ፍሬዴሩክ ሜርስ መራሂተ መንግሥቷ ላይ የሚያሳርፉትን ጫና መቀጠላቸው እንደማይቀር አያጠራጥርም። 
በመጪው መጋቢት ወር በአውሮጳ ሕብረት የሚካሄደው ምርጫ ውጤት ለጀርመን መንግሥት ወሳኝ ሊሆን እንደሚችል ይገመታል። ከአንጌላ ሜርክል ፓርቲ ጋር በመጣመር የመንግሥት አስተዳደር የመሠረተው ሶሻል ዴሞክራት ፓርቲም ቢሆን መዘዝ ይኖረዋል። በዚህ ምክንያትም ከመንግሥት ኃላፊነቱ ሊለቅ፤ ይህ ደግሞ የሜርክልን የመራሂተ መንግሥትነት ዘመን እንዲያከትም ሊያደርገው እንደሚችልም ይገመታል። በሕብረቱ የሚካሄደው ምርጫ ቀኝ ሕዝበኛ ፖለቲከኞችን ወደ አውሮጳ ከፍ አድርጎ ሊያመጣቸው ይችላል፤ አንጌላ ሜርክልም እዚህ ጀርመን ውስጥ ሳይቀር ተፅዕኖውን ይመለከቱት ይሆናል። ጀርመን ውስጥ ባለፈው የሰሜኑ ንፍቀ ክበብ የበጋ ወራት ቀኝ ሕዝበኛ ፖለቲከኞች ከቀኝ አክራሪዎች ጋር ትከሻ ለትከሻ ገጥመው ኬሜትዝ ላይ ታይተዋል። የሜርክል አስተዳደር ዘመን ለማክተም ፈቅደው ሕብረት የፈጠሩት ሕዝበኛ ፖለቲከኞች ጀርመን ውስጥ አዲስ ኃይል ሊያገኙም ይችላሉ። 
በጎርጎሪዮሳዊው 2019 በቅርቡ ሦስት የፌደራል ጀርመን የምሥራቅ ፌደራል ግዛቶች የአካባቢ ምክር ቤት ምርጫ ያካሂዳሉ። አማራጭ ለጀርመን የተሰኘው ሕዝበኛ ፓርቲ ጠንክሮ በመውጣት በእነዚህ ፌደራል ግዛቶች የሜርክልን ፓርቲ መተካት ይፈልጋል። 
የቀኝ ክንፉ ሕዝበኛ ፓርቲ አማራጭ ለጀርመን በጎርጎሪዮሳዊው 2017 ዓ.ም አጠቃላይ ምርጫ ወቅት ያገኘውን ውጤት መድገም ከተሳካለት በዛክሰን ውስጥ ጠንካራው የፖለቲካ ኃይል ሆኖ ሊወጣ ይችላል። የሜርክል ክርስቲያን ዴሞክራት ፓርቲ በምርጫ የሚገጥመው ተጨማሪ ሽንፈትም በፌደራል መንግሥቱ ላይ የተሰነዘረ ተቃውሞ ተደርጎ ይወሰዳል። 
ይህ ሁሉ ደግሞ የትልቁን የፖለቲካ ፓርቲዎች ጥምረት ዕድሜ ጥያቄ ላይ የሚጥል ነው፤ ባለፈው ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት ማለቂያ ላይ ከሜርክል ፓርቲ ጋር ተጣምሮ መንግሥት የመሠረተዉ ሶሻል ዴሞክራት ፓርቲ በጥምረቱ ለመዝለቅ ያስችለኛል ያለውን መደራደሪያ አቅርቧል። ፓርቲው ባማራጭነት ከጥምር መንግሥቱ መዉጣትን አስቀምጧል። ይህን እውን ካደረገ ደግሞ የሜርክል ዘመነ መራሂተ መንግሥትነት ካለ ጊዜው ሊያከትም ይችላል። 

Deutschland CDU-Regionalkonferenz Düsseldorf l Ex-Fraktionschef Friedrich Merz
ፍሬድሪክ ሜርስምስል picture alliance/dpa/F. Gambarini
Deutschland CDU-Regionalkonferenz Düsseldorf l CDU Gerneralsekretärin Annegret Kramp-Karrenbauer
አነግሬት ክራም ክራንባወርምስል Imago/J. Schüler

ሸዋዬ ለገሠ/ማኑዌላ ላይንሆስ

ማንተጋፍቶት ስለሺ