1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ማክሮ እና አዲስ ያሉት የአፍሪቃ ፖሊሲያቸው

ማክሰኞ፣ ኅዳር 19 2010

የፈረንሳይ ፕሬዚደንት ኤማኑዌል ማክሮ አሁን በአፍሪቃ የጀመሩት ጉዞ  የሀገራቸውን አዲስ የአፍሪቃ ፖሊሲ ማሳያ ይሆናል ተብሏል። ፕሬዚደንት ማክሮ በቡርኪና ፋሶ ዛሬ ለተማሪዎች ያደረጉት ዲስኩር እና ወደ እንግሊዝኛ ተናጋሪዋ ጋና የሚያደርጉት ጉብኝታቸው የእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ መዋቅር ማክተሙን እንደሚያጎላ የፖለቲካ ተንታኞች ለዶይቸ ቬለ ገልጸዋል።

https://p.dw.com/p/2oOvM
Burkina Faso Emmauel Macron Besuch bei Roch Marc Kaboré in Ouagadougou
ምስል Getty Images/AFP/L. Marin

«አፍሪቃውያን ምን ማድረግ እንዳለባቸው ከማይናገር ትውልድ ነው የመጣሁት።»

የፈረንሳይ ፕሬዚደንት ኤማኑዌል ማክሮ የቀድሞው አቻቸው ፍራንስዋ ኦሎንድ ከተከተሉት የተለየ የአፍሪቃ ፖሊስ ለመጀመር እቅድ አላቸው። ለዚሁ እቅድ ማሳካት ይረዳቸውም ዘንድ ማክሮ አፍሪቃን በተመለከተ ሀሳብ የሚያጋሩዋቸው፣  በተለይ ከኤኮኖሚው ዘርፍ የተውጣጡ በበጎ ፈቃድ የሚሰሩ 11 አማካሪዎች ያሉት በምህፃሩ ሲፒኤ የተባለ አንድ ቡድን አቋቁመዋል። ይኸው ቡድን ፈረንሳዊው ፕሬዚደንት የምዕራብ አፍሪቃ ጉዟቸውን ከመጀመራቸው በፊት በነበሩት ሳምንታት ስለ አህጉሩ አስፈላጊ የተባሉ መረጃዎችን ሲያቀርብ ሰንብቷል። 
ማክሮ ዛሬ በቡርኪና ፋሶ መዲና ዋጋዱጉ ዩኒቨርሲቲ ለ800 ተማሪዎች ያሰሙት ዲስኩራቸው ከቀድሞው አቻቸው የተለየ አዲስ ሀሳብ ያቀረቡበት እንደነበር የፖለቲካ ተንታኞች ጠቁመዋል። አፍሪቃውያን ምን ማድረግ እንዳለባቸው ከማይናገር ትውልድ መምጣታቸውን ያጎሉት ማክሮ አዲስ ያሉትን የሀገራቸውን የአፍሪቃ ፖሊሲ በዋጋዱጉ ዩኒቨርሲቲ ይፋ ማድረጋቸው ትልቅ መልዕክት የሚያስተላለፈ መሆኑን በፓሪስ የሶርቦን ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ መምህር የሆኑት የኮንጎው ተወላጅ ቱምባ ሻንጎ ሎኮሆ አስታውቀዋል። 
« የአፍሪቃ  ወጣት የወደፊቱ ተስፋ ነው ከተባለ፣  ትምህርት፣ የሙያ ስልጠና እና የአፍሪቃን ተሀድሶ ማነቃቃት ይችል ዘንድ በዚያው በአህጉሩ ስራ መስራት የሚያስችለው  ሁኔታ ሊፈጠርለት ይገባል። »  
ፈረንሳዊው ፕሬዚደንት  የአፍሪቃን ወጣት ትውልድ ከጎናቸው እንዲቆም መገፈለጋቸውን ቢያሳዩም፣ ይህ ቀላል እንደማይሆን ፈረንሳዊው ጋዜጠኛ እና ደራሲ ኦንቷን ግላሴ ገምተዋል።
«  የፈረንሳይ እና የማክሮ ችግር ሀገሪቱ ለብዙ ጊዜ ተፃራሪ የሆነ የአፍሪቃ ፖለቲካ ስትከተል መቆየቷ ነው። ፈረንሳይ ራሷን በተለይ በፈረንሳይኛ ተናጋሪ ሃገራት ርዕሳነ ብሔር ላይ ጥገኛ አድርጋለች። እና ማክሮ አሁን ለአህጉሩን ወጣቶች እና በፈረንሳይ ለሚኖሩ አፍሪቃውያንን ፍላጎት ትኩረት ለመስጠት ዝግጁነታቸውን በማሳየት ይህንን ጥገኝነት ለማብቃት ይፈልጋሉ። »

Burkina Faso Emmauel Macron Besuch bei Roch Marc Kaboré in Ouagadougou
ምስል Reuters/L. Marin

እንደ ፖለቲካ ምሁሩ ቱምባ ሻንጎ ሎኮሆ አመለካከት፣ ማክሮ በስልጣን በቆዩባቸው ባለፉት ስድስት ወራት በዚህ ረገድ አንዳንድ ለውጦች ታይተዋል።
« ማክሮ ከአፍሪቃውያን አቻዎቻቸው ጋር በመተማመን፣ በመከባበር እና በግልጽነት ላይ የተመሰረተ አካሄድ ተከትለዋል ብዬ አምናለሁ። አሁን በወጣቶችም አኳያ ፣ «እጣ ፈንታችሁን ራሳችሁ መወሰን አለባችሁ ባሉበት አነጋገራቸውም»፣ ይህንኑ ግልጽነትን መሰረት ያደረገውን አቀራረባቸውን አንጸባርቀዋል። » 
ኤማኑዌል ማክሮ አዲስ የአፍሪቃ ፖሊሲ  እንደሚከተሉ ቢያስታውቁም ግን፣ እስካሁን ሀገራቸው የተከተለችውን ፖሊሲ ሁሉ ይቀይራሉ ማለት አለመሆኑን ጋዜጠኛው ኦንቷን ግላሴ ጠቁመዋል። ግላሴ እንደሚሉት፣ የፀጥታ ጥበቃ ፖሊሲን በተመለከተ ማክሮ ፍራንስዋ ኦሎንድ ካቆሙበት  ቀጥለው «ቡድን 5» በሚል የሚታወቀውን በሳህል አካባቢ አዲስ የጦር ተልዕኮ ከመጀመራቸው ጎን፣ በሽብርተንነት አንፃር ከምዕራብ አፍሪቃ ሃገራት ጋር የተፈጠረውን ጉድኝት አጠናክረዋል። ይሁንና፣ እንደ ፖለቲካ ሳይንስ መምህር ቱምባ ሻንጎ ሎ ኮሆ አስተሳሰብ፣ ማክሮ ሽብርተኝነትን ለመታገል ከወታደራዊ  ጎን ኤኮኒሚያዊ ርምጃዎችም በተጨማሪ መታከል እንዳለባቸው መረዳታቸውን አዎንታዊ ነው።
« በአፍሪቃ ሃገራት የሚታዩት ማኅበራዊ እና ኤኮኖሚያዊ ሁኔታዎች ችላ እስከተባሉ ድረስ፣  ሽብርተኝነትን በሚገባ መታገል አይቻልም።  ስለዚህ በነዚህ ሃገራት ውስጥ ፍትሓዊ እና የሃገራቱን ሁኔታ ያገናዘበ የኤኮኖሚ ፖሊሲ ማራመድ አስፈላጊ ይሆናል። » 

Infografik Kampf gegen Terror in der Sahel-Region

 አርያም ተክሌ/ፊሊፕ ዛንድነር

ሸዋዬ ለገሠ