1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ሳይንስ

ማበረታቻ የሚሻዉ የወጣቶች የፈጠራ ስራ

ረቡዕ፣ ኅዳር 19 2011

በኢትዮጵያ በተለይም በትምርት ቤቶች የተለያዩ የፈጠራ ስራዎችን የሚሰሩ ታዳጊ ወጣቶች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱ ይነገራል።የእነዚህን ወጣቶች የፈጠራ ስራዎች ወደ ምርትና አገልግሎት መቀየር ግን ብዙ እየተሰራበት አይደለም በሚል ይተቻል።

https://p.dw.com/p/393R5
Äthiopien Solomon Bahiru, junger Erfinder
ምስል Solomon Bahiru

«ትኩረት ያላገኜዉ የወጣቶች የፈጠራ ስራ»



የኢትዮጵያ ኢኖቬሽንና የቴክኖሎጅ ሚኒስቴር ከትምህርት ሚኒስቴርና ስቴም ሲነርጅ ከተባለ ድርጅት ጋር በመተባበር ዓለም ዓቀፍ የሳይንስ ቀንን ምክንያት በማድረግ በቅርቡ የ5 ቀናት የተማሪዎች ፈጠራ ስራዎች ትዕይንት አዘጋጅቶ ነበር።በኢትዮጵያ የቴክኖሎጂና የኢኖቬሽን ሚኒስቴር የሚዲያና የፕሬስ  ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ አለምነዉ እንደሚሉት አዉደ ርዕዩ 3 መሰረታዊ ዓላማዎች ነበሩት።የማበረታታት፤የልምድ ልዉዉጥ እንዲያገኙ ማድረግና ወደ ስራ ሊገቡ የሚችሉ የፈጠራ ስራዎችን ከገበያ ጋር ማስተሳሰር።

ከዚህ የፈጠራ ስራ ትዕይንት ከየትምህርት ቤቱ ተወዳድረዉ አሸናፊ የሆኑ  ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች  ከ160 በላይ ተማሪዎች የፈጠራ ስራዎቻቸዉን አቅርበዋል። ከደቡብ ክልል ወላይታ ሶዶ ከተማ ቦጋለ ዋለልኝ ሁለተኛ ደረጃና መሰናዶ ትምህርት ቤትን ወክሎ የመጣዉ ወጣት ሶሎሞን ባህሩ ከእነዚህ ወጣቶች አንዱ ነዉ።ሶሎሞን፤ የ19 ዓመት ወጣትና የ12ኛ ክፍል ተማሪ ሲሆን  የግብርና ስራን በቀላሉ ለማከናወን የሚያስችሉ 5 የፈጠራ ስራዎችን ይዞ ነበር በዓዉደ ርዕዩ የቀረበዉ።

Äthiopien Solomon Bahiru, junger Erfinder
ምስል Solomon Bahiru

« ይዠ የቀረብኩት አምስት በግብርና ላይ ያተኮሩ ስራዎችን ነዉ።እነሱም አንደኛ ዘመናዊ የበቆሎ መፈልፈያ ነዉ።ሁለተኛዉ ደግሞ የጤፍ፣ የስንዴ ፣የገብስ የበቆሎ በመስመር መዝሪያ ማሽን ነዉ።ሶስተኛዉ ዘመናዊ የጤፍ ፣የስንዴና የገብስ ማጨጃ ነዉ።አራተኛዉ ደግሞ የማሳ መኮትኮቻ ነዉ።አምስተኛዉ የጤፍ የስንዴ ማበጠሪያ ነዉ።»

ከ5 ቱ የፈጠራ ስራዎቹ አንዱ ብቻ በኤለክትሪክ የሚሰራ ሲሆን የተቀሩት አራት ስራዎቹ በቀላሉ በእጅ በማንቀሳቀስ ብቻ የሚሰሩ በመሆናቸዉ ማንም ሰዉ በቀላሉ ሊጠቀምባቸዉ የሚችሉ ናቸዉ።በተለይ ብስክሌት መሰል የበቆሎ መፈልፈያዉ በአንድ ጊዜ 5 እና 6 ኩንታል በቆሎ መፈልፈል የሚያስችል በመሆኑ ጊዜና ገንዘብን ይቆጥባል።አሰራሩም ቢሆን ቀላል ነዉ ይላል። 
እንደ ጋሪ የሚገፋዉ የማጨጃ ማሽንም በኤለክትሪክ ወይም በባትሪ የሚሰራ ቢሆንም በአጭር ጊዜ ብዙ ስራዎችን ለማከናወን የሚያስችል መሆኑን ነዉ ያብራራዉ።
ለቤተሰቡ የመጀመሪያና ብቸኛ ወንድ ልጅ መሆኑን የሚናገረዉ ሰሎሞን  ከትምህርቱ ጎን ለጎን ወላጆቹን በግብርና ስራ የማገዝ ሀላፊነት ነበረበት። የወላጆቹን  አድካሚና ዉጣ ዉረድ የበዛበት የግብርና ስራ በቅርብ መመልከቱም ለአሁኑ የፈጠራ ስራዉ መነሻ ሆኖታል።
የፈጠራ ስራዎቹ ላለፉት 7 ዓመታት በትምህርት ቤቱ የፈጠራ ማዕከል ባገኜዉ የተወሰነ ድጋፍና እዉቀት የተሰሩ ናቸዉ።አገልግሎታቸዉም ቢሆን ከዚያዉ ከትምህርት ቤቱ የአትክልት ቦታዎች አላለፈም።ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በተለያዩ አጋጣሚዎች የተሳተፈባቸዉ የሰርተፌኬት ሽልማት ያገኘባቸዉ የፈጠራ ስራ አዉደ ርዕዮች በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ዕድል ፈጥረዉለታል። 
ያም ሆኖ ግን የፈጠራ ስራዎቹን በማስፋፋት ወደ ምርትና አገልግሎት ቀይሮ ገንዘብ እንዲያመጡ ለማድረግ የፈጠራ ዕዉቅናና ባለቤትነት ፈቃድ እንዲሁም የገንዘብ ድጋፍ አለመኖር  ማነቆ ሆኖበታል።
ኢትዮጵያ በቴክኖሎጅዉ መስክ የተፋጠነ እድገት እንዲኖራት ከተፈለገ ያላትን ወጣት ኃይል መጠቀምን፣ እንዲሁም  የእዉቀትና የፈጠራ ስራ ላይ ትኩረት ሰጥቶ መስራትን ፤ባለሙያዎች ይመክራሉ።ያም ሆኖ ግን የቴክኖሎጅ ፈጠራዎችን የሚያሳዩ አዉደ ርዕዮችን ከማዘጋጀትና ሰርተፌኬት ሰጥቶ አዉደ ርዕዩን ከማጠናቀቅ በዘለለ ችግር ፈቺና ማህበረሰቡ ሊጠቀምባቸዉ የሚችሉ የፈጠራ ስራዎች ዳብረዉ ወደ ስራ እንዲገቡ ማድረግ ግን እስካሁን ትኩረት የተሰጠዉ ስራ እንዳልሆነ ብዙዎች ይናገራሉ።እንዲህ መሰሉ አዉደ ርዕይ በተማሪዎቹ መካከል የልምድ ልዉዉጥ ለማግኘትና ስራዎቻቸዉን ለማስተዋወቅ የሚጠቅም ቢሆንም ወጣቶቹን ተከታትሎ በመደገፍ ረገድ እጥረት አለበት።

Äthiopien Solomon Bahiru, junger Erfinder
ምስል Solomon Bahiru

በኢትዮጵያ የቴክኖሎጅና የኢኖቬሽን ሚኒስቴር የሚዲያና የፕሬስ  ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር  አቶ ተስፋዬ አለምነዉ ከአሁን ቀደም በተደራጀ መልኩ  ወጣቶችን የመደገፉ ስራ አናሳ እንደነበር ገልፀዉ፤ ለወደፊቱ ግን የወጣቶቹን የፈጠራ ስራዎች በመለየት ወደ ምርት ሊገቡ የሚችሉ ስራዎችን ለመደገፍ ዕቅድ ይዘናል ነዉ ያሉት። 
በዉጭ ምንዛሬ ተገዝተዉ ከሚመጡ የቴክኖሎጅ ዉጤቶች ይልቅ ሀገር በቀል ቴክኖሎጅዎችን መጠቀም የተሻለ ችግር ፈቺ መሆኑን የሌሎች ሀገራት ልምዶች ያሳያሉ።በተለይም  85 በመቶ የሚሆነዉ ህዝብ በግብርና ለሚተደደርባት ኢትዮጵያ ፤ ሀገር በቀል የግብርና ቴክኖሎጅዎች አዋጭ መሆናቸዉን በዘርፉ ባለሙያዎች ይነገራል። 

ሙሉ ቅንብሩን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነዉ ያድምጡ።

ፀሐይ ጫኔ

ሂሩት መለሰ