1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ማሊ እና የመለያው ፕሬዚደንታዊው ምርጫ

ቅዳሜ፣ ነሐሴ 5 2010

የማሊ ዜጎች ነገ በሚያካሂዱት 2ኛ ዙር ፕሬዚደንታዊ ምርጫ ለሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ሀገሪቱን የሚመራው ይለያል። በመጀመሪያው ዙር ምርጫ የ73 ዓመቱ ፕሬዚደንት ኢብራሂም ቡበከር ኬይታ 41%፣ ለሬፓብሊኳ እና ለዴሞክራሲ አንድነት የተሰኘው የተቃዋሚ ፓርቲ ተፎካካሪያቸው ሱማይላ ሲሴ ደግሞ 17,8% የመራጭ ድምፅ በማግኘት ነው ያለፉት።

https://p.dw.com/p/32zN6
Mali Wahl Bildkombo | Ibrahim Boubacar Keita & Soumaila Cisse

ማሊ

ሕዝቡ ኢቤካ እያለ በአህጽሮት የሚጠራቸው ፕሬዚደንት ኢብራሂም ቡበከር ኬይታ ተፎካካሪያቸውን በከፍተኛ ድምፅ በመምራታቸው ቢኩራሩም፣ የነገውን ምርጫ  ህዝቡእንደ ዋዛ እንዳይመለከተው ጠይቀዋል።« ሁሉንም የማሊ ዜጎች እኛ ለሀገሪቱ ትክክለኛው አማራጭ መሆናችንን ማሳመን አለብን። ይህንን የሚጠራጠሩትን ወገኖች በተለይ  ማለመን ይኖርብናል።»

በፓሪስ የታሪክ እና የዓለም አቀፍ ግንኙነት ትምህርት ያጠኑት ኢብራሂም ቡባከር ኬይታ ከብዙ አሰርተ ዓመታታት ወዲህ በማሊ የፖለቲካ መድረክ ውስጥ ዋና ተዋናይ ሆነው ቆይተዋል። ገና በዘጠኛኛዎቹ ዓመታት ሀገሪቱን በመሩት ፕሬዚደንት አልፋ ኮናሬ ዘመን በጠቅላይ ሚንስትርነት ፣ በኋላም ላይ በምክር ቤት ፕሬዚደንትነት አገልግለዋል። በጎርጎሪዮሳዊው 2013 ዓምም የማሊ ፕሬዚደንት የሆኑት ቡባከር ኬይታ በምግባረ ብልሹነት የማይታሙ መሪ እንደሆኑ ሙሳ ተምቢነ የተባሉ ደጋፊያቸው ለዶይቸ ቬለ ተናግረዋል። « ከሳቸው ጋር የሚሰራ ሰው ጥሩ ምግባር ያለው መሆን አለበት። የሚዋሽ፣ የሚሰርቅ ሰው፣ ባጠቃላይ በሙስና የተተበተበ ሰው አይወዱም። »ፕሬዚደንት ኬይታ ነገ ከተቃዋሚው ህብረት መሪ እጩ ሱሜይላ ሲሴ ጋር በሚያደርጉት የመለያ ፕሬዚደንታዊ ምርጫ ላይ በመጀመሪያው ዙር ያልመረጧቸው መራጮች ድምፃቸውን እንዲሰጧቸው ለማግባባት በምርጫው ዘመጫ ከፍተኛ  ሙከራ አድርገዋል።  በመጀመሪያው ዙር 17,8 ከመቶ  ድምፅ  ያገኙት ሱሜይላ ሲሴ እና የምርጫ ዘመቻ ቡድናቸው ገዢው የማሊ መንግሥት ምርጫውን ለራሱ እንደሚመቸው ለመቀያየር ወደኋላ እንደማይል ያምናል።
« መንግሥት በ29/07/2018 በተደረገው ምርጫ ላይ ህዝቡ በነፃ እንዳይመርጥ ለማከላከል የሚቻለውን ሁሉ ማድረጉን እናውቃለን። የምርጫው ውጤት የማይታመን ነው። ውጤቱ የተጭበረበረ ነው።»

Mali Stichwahl Ibrahim Boubacar Keïta
ምስል DW/K. Gänsler

ሲሴ ከሌሎች 17 እጩ ተወዳዳሪዎች ጋር ባንድነት በመሆን ለምርጫው ዝግጅት እና ውጤቱ በይፋ ለወጣበት ድርጊት ኃላፊነቱን የያዘው የግዛት አስተዳዳሪ ሚንስቴር ኃላፊ  ስልጣናቸውን እንዲለቁ ጠይቀዋል። ሕገ መንግሥታዊው ፍርድ ቤት ምርጫው ተጭበርብሯል በሚል የተሰነዘረውን ወቀሳ እንዲያጣራ የተቃዋሚው ቡድንም አቅርቦት የነበረውን ጥያቄ ፍርድ ቤቱ አጣርቶ ውድቅ አድርጎታል፣ ውጤቱን ትክክለና መሆኑን ገልጿል። የመለያው ምርጫ የ2013 ዓም ን ምርጫ ያስታውሳል፣ ያኔ ኬይታ እና ሲሴ ተወዳድረው ኬይታ በ77 ከመቶ ድምፅ ባሸነፉበት ጊዜ ሲሴ ከ24 ሰዓታት በኋላ ነበር ሽንፈታቸው የተቀበሉት። በዳካር እና በሞንፐልየ የኢንፎርማቲክ ትምህርታቸውን የጨረሱት ሲሴ  በማሊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለመትከል በ1990 ኛዎቹ ከተጀመረ አንስቶ በሀገሪቱ ፖለቲካ መድረክ ላይ አሉ። ማሊን ከ1993 እስከ 1997 በመሩት በፕሬዚደንት ኮናሬ ዘመን ሲሴ የፊናንስ እና የኤኮኖሚ ሚንስትር  በኋላም የተፈጥሮ ጥበቃ ሚንስትር ሆነው አገልግለዋል። የከተማ አስተዳደር ሚንስትርም ነበሩ። በዚሁ ጊዜ ከአሁኑ ተፎካካሪያቸው ኢብራሂም ኬይታ ጋር አብረው ሰርተዋል። ኬይታ ጠቅላይ ሚንስትርም ነበሩ ። በ2002 ሁለቱም ለከፍተኛው ስልጣን በእጩነት ተወዳድረው፣ ነበር። ሲሴ ከኢቤካ በ4000 ድምፅ ብልጫ የተሻለ ውጤት አስመዝግበው ለሁለተኛ ዙር ምርጫ አልፈው ነበር። በዚሁ የመለያ ምርጫ ላይ ሲሴ በአማኒ ቱማኒ ቱሬ መሸነፋቸው ይታወሳል። 
ሲሴ በማሊ ለውጥ ለማምጣት የሚፈልጉ እጩ መሆናቸውን በምርጫ ዘመቻ ወቅት አጉልተዋል።  ይሁንና፣ ሲሴ ብዙዎች ሲሴ ከድሮ ጀምሮ ያሉ ፖለቲከኛ በመሆናቸው ይህን አነጋገራቸውን  አላመኑትም። የሲሴ  የመገናኛ ጉዳዮች አማካሪ ኑሁም ቶጎ ግን ይህን በሲሴ አኳያ የተሰነዘረውን የጥርጣሬ አስተያየት አይቀበሉትም። እንደ ቶጎ አስተሳሰብ ለመንግሥት ስልጣን ተሞክሮ  አስፈላጊ እንደሆነ እ ነው የተናገሩት። «ጀርመን ሀገር ውስጥ አንድ ምንም ሰርቶ የማያውቅ ወጣት ፕሬዚደንት መሆን ይችላል ወይ? የትኛው ሀገር ነው እንዲህ የሚደረገው ? ለውጥ እኮ በደረጃ እና በተጠየቅ፣ ማለትም፣ በሎጂክ  የሚገኝ ነው። »

Mali Stichwahl Soumaïla Cissé
ምስል DW/K. Gänsler

ስልጣን ለመያዝ ተሞክሮ እና እውቅቀት የግድ አስፈላጊ ነው ይላሉ። ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ ሲሴ ለዘመናዩ ቴክኒክ ቅርበት ካለው ወጣት ትውልድ ጋር በቅርብ የሚሰሩ መሆናቸው ለሀገሪቱ የተሻለ እድል ሊያስገኙ የሚችሉ እጩ እንዳደረጋቸው አማካሪያቸው ኑሁም ቶጎ አስረድተዋል። የሌሎች ተቃዋሚ ፓርቲዎችም የፕሬዚደንት ኬይታ አመራር አብቅቶ ለውጥ እንዲመጣ ተስፋ አድርገዋል።  ይሁንና፣ ተስፋው እውን መሆኑ ተንታኞች ተጠራጥረውታል። እንደ ተንታኞቹ  በመለያው ምርጫ የማይሳተፉት  የተቃዋሚ ቡድኖች እጩዎች በጠቅላላ ድጋፋቸውን በሱማይላ ሲሴ ዙርያ የሚያሰባስቡ አይመስልም ።
በመጀመሪያው ዙር ምርጫ ስምንት ከመቶ የመራጭ ድምፅ በማግኘት የሶስተኛነቱን ቦታ ያገኙት የዴሞክራሲያዊ ህብረት ለሰላም ፓርቲ እጩ አሊዩ ዲያሎ ከሲሴ ጎን በመቆም ፈንታ ለቀጣይ ምርጫዎች ማጠናከር አስፈላጊ መሆኑን ነው ከሁለት ቀን በፊት በይፋ የተናገሩት።

Mali Wahlen - Wahllokal
ምስል DW/K. Gänsler

« በመጪው ህዳር ለሚደረገው ምክር ቤታዊ ምርጫ ራሳችንን ማዘጋጀት መጀመር አለብን። ከአንድ ወር ገደማ በኋላ ማለትም፣ የፊታችን መስከረም አራት፣ 2018 ዓም  ፕሬዚደንቱን ለመቆጣጠር እንችል ዘንድ አብላጫውን የመራጭ ድምፅ ለማግኘት መስራት  ይኖርብናል። »
ዴሞክራሲን ለማዳበር የተጀመረው ጥረት በመጀመሪያው ዙር ፕሬዚደንታዊው ምርጫ ሂደት ክሽፈት እንደደረሰበት ገልጸው ይህን ለመቀየር መስራት አስፈላጊ መሆኑን አስረድተዋል። 
« ለውጥ ማምጣት እንደምንችል የሀገራችንን ህዝብ ወደፊት ማሳመን ይኖርብናል። ይህን ለሶስት ሚልዮኑ የማሊ መራጮች ማሳየት አለብን። ከዚህ፣ በተጫማሪም፣ ባለፈው ሀምሌ 29 ቀን፣ 2018 ዓም ከተካሄደው ፕሬዚደንታዊ ምርጫ የራቁትን ፣ አምስቱን ሚልዮን መራጮች ፣ ብሎም፣ ዝምታን የመረጡትን አብላጫ  ወገኖቻችንም መድረስ መቻል ይጠበቅብናል። »
በተቃዋሚዎች መካከል ጠንካራ ህብረት አለመኖሩ ለፕሬዚደንት ኬይታ ድጋሚ የመመረጡን አመቺ ሁኔታ እንደፈጠረላቸው ይታመናል።

አርያም ተክሌ/ካትሪን ጌንስለር

እሸቴ በቀለ