1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

መንግሥት የአሸባሪነት ስያሜ ያነሳላቸው ድርጅቶች

ዓርብ፣ ሰኔ 29 2010

የኢትዮጵያ መንግሥት የአሸባሪነት ስያሜ ያነሳላቸው የፖለቲካ ድርጅቶች ርምጃው አዎንታዊና አበረታች መሆኑን አስታወቅ። የኢትዮጵያ ምክር ቤት በትናንትናው ዕለት በኦሮሞ ነፃ አውጭ ግንባር (ኦነግ)፤ በኦጋዴን ብሔራዊ ነፃነት ግንባር (ኦብነግ) እንዲሁም በአርበኞች ግንቦት ሰባት ላይ ጥሎት የቆየውን የአሸባሪነት ስም በሙሉ ድምፅ በይፋ ሰርዟል።

https://p.dw.com/p/30y9j
Logo Patriot Ginbot 7

ምክር ቤቱ የወሰደው አዎንታዊ ርምጃ ነው

የአሸባሪነት ስያሜ ከተነሳላቸው ድርጅቶች አንዳንዶቹ ወደ ሀገር ቤት መግባት መጀመራቸው ተነግሯል። እንደአርደኞች ግንቦት ሰባት ያሉት ደግሞ ሀገር ውስጥ በሕቡዕ ሲያደርጉት የቆየውን እንቅስቃሴ ሕጋዊ እና ይፋ ለማድረግ እንደሚሠሩ አመልክተዋል። የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ኦነግ ኦብነግ እና ግንቦት ሰባትን በ2003ዓ,ም ነበር ሽብርተኛ ሲል የፈረጃቸው። ሆኖም ትናንት በይፋ አሸባሪ የሚለውን ፍረጃ ማንሳቱን ምክር ቤቱ አስታውቋል። የአርበኞች ግንቦት ሰባት የሥራ አስፈጻሚ አባል የሆኑት ዶክተር ታደሰ ብሩ የምክር ቤቱን ውሳኔ ድርጅታቸው ሲጠብቀው የነበረ ጉዳይ መሆኑን ይናገራሉ።

«ይኼ እንግዲህ መነሳቱ በጣም ጥሩ ነው፤ እዛም ስብሰባውም ላይ ተጠቅሶ እንደነበረው ከመጀመሪያውም መደረግ ያልነበረበት ነገር ነው። ግን መነሳቱ በጣም ደስ ብሎናል። ጥሩ ነገር ነው ስንጠብቀው የነበረ ጉዳይ ነው። እኛም ደግሞ በቀና ፖዘቲቪሊ ነው ያነው በጣም ጥሩ ነገር ነው።»

በተመሳሳይ ፍረጃው የተነሳለት የኦሮሞ ነፃ አውጭ ግንባር ኦነግ በበኩሉ ውሳኔውን በአዎንታዊ መልኩ ቢቀበለውም በድርጅቱ ላይ የተከፈተው ጦርነት የሚቆምበት መንገድ እንዲፈጠር አስቀድሞ ገለልተኛ ወገንን ያካተተ ድርድር ከመንግሥት ጋር እንደሚፈልግ የግንባሩ ሊቀመንበር አቶ ዳውድ ኢብሳ ገልጸዋል።

«መነሳቱን በበጎ ዓይን ነው የምናየው። ሆኖም በዚህ ግንባር ላይ ይኽ አዋጅ ብቻ አይደለም የታወጀው፤ በ1992 ከቻርተሩ ተገፍተን ስንወጣ በጊዜው የኢፒአርዲኤፍ ሊቀመንበር እና የኢትዮጵያ የሽግግር መንግሥት ፕሬዝደንት የነበሩት አቶ መለስ ዜናዊ ጦርነት ነው ያወጁብን፤ ይኼ ጦርነት እስካሁን አልተነሳም በእኛ ላይ ይሄ እንዲነሳ ሦስተኛ አካል ባለበት ቦታ ቁጭ ብለን ተነጋግረን ለዚህ መደምደሚያ እንድናደርግ አሁን መንግስት ላይ ላሉት ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ መንግሥት በተደጋጋሚ ጥሪ አድርገናል፤ እየጠበቅን ነው።»

እንዲያም ሆኖ ከዛሬ ሰባት ዓመት በፊት ድርጅቶቹን አሸባሪ ሲል የፈረጀው አዋጅ ሲታወጅ በኦሮሞ ሕዝብ እና በድርጅቱ ላይ አሳዛኝ ነገር መድረሱን፤ በዚህ አማካኝነትም በርካቶች የኦነግ አባል በመሆናቸው ብቻ ለእስራት፣ ለስቃይ እና እንግልት እንዲሁም ለአካል ጉዳት መዳረጋቸውን አቶ ዳውድ ኢብሳ አንስተዋል።

መንግሥት ፍረጃውን ለማንሳት በምክንያትነት ከጠቀሳቸው አንዱ ድርጅቶቹ በሰላማዊ መንገድ ለመንቀሳቀስ መወሰናቸው መሆኑን ትናንት በምክር ቤት የተነበበው ውሳኔ ያመለክታል። በቀጣይ በሀገሪቱ የፖለቲካ እንቅስቃሴ የሚኖረው ሚና ምን እንደሚመስል የጠየኳቸው የኦነግ ሊቀመንበር ድሮም ወደ ትጥቅ ትግል የገባነው ተገፍተን ነው ይላሉ። 

Äthiopien - Parlament
ምስል DW/Y. Gebregziabher

«ወደትጥቅ ትግል ተገፍተን ነው የገባነው፤ የኢትዮጵያ ሽግግር መንግሥት አባል ነበርን አብረን ነው የሽግግር መንግሥቱን ያቋቋምነው ከዚህ ነው ገፍተው ወደ ትጥቅ ትግል ያስገቡን በግዴታ። የትጥቅ ትግሉ የመከላከል ጦርነት ነው እስካሁን ድረስ እየተደረገ ያለው። ሌላው ደግሞ ትጥቅ ይዞ እንደ መንግሥት ሽብር ሲያፋፍም የነበረው ስልጣን ላይ ያለው ፓርቲ ነው። እግዜር ይስጣቸው ጠ/ሚኒስሩም ይህንን ተናግረዋል። እና አሁን መደምደሚያ እናድርግ እና ከፖለቲካ ሜዳ ኃይል መጠቀምን ለማውጣት ስምምነት ይጠይቃል።»

ለዚህም ዳግም ለመንግሥት ያቀረቡት ጉዳይ መደምደሚያ እንደሚያስፈልገው እና ያ ከተከናወነ በኋላም በድርጅታቸው በኩል ተነጋግረው የትጥቅ ትግሉን ለመተው ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል። ከዚህም ሌላ አቶ ዳውድል በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች ላለፉት 27 ዓመታት የሚንቀሳቀስ ሠራዊት ኦነግ እንዳላለው የገለፁ ሲሆን በኦሮሞ ሕዝብ ስም ከሚንቀሳቀሱ ድርጅቶች ጋር ይህ ነው የሚባል የጎላ ልዩነት እንደሌላቸውም አመልክተዋል። ወደ ሀገር ቤት መግባት የጀመሩትንም ውሳኔያቸውን እንደሚያከብሩ አስረድተዋል። የአርበኞች ግንቦት የሥራ አስፈጻሚ አባል የሆኑት ዶክተር ታደሰ፤ ድርጅታቸው ከድሮውም ቢሆን በሰላማዊ መንገድ መንቀሳቀስን ይፈልገው እንደነበር ነው ያመለከቱት። በቀጣይም በሀገሪቱ የሚታየው የለውጥ ንቅናቄ ወዴት በኩል ይሄዳል የሚለውንም በንቃት እየተከታተለ መሆኑንም በመጠቆም በሰላማዊ መንገድ በፖለቲካው ለመሳተፍ ግን ዝግጁ እንዳለ  ገልጸዋል። ወደሀገር ቤት እንደሌሎቹ የመግባት ሃሳብ እንዳለ ለቀረበላቸው ጥያቄ ግን እና እኮ ድሮም ሀገር ቤት ነበርን ነው ያሉት።

የመንግስትን ዉሳኔ አስመልክቶ አሰተያየታቸውን የሰጡን የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር የሥራ አስፈጻሚ አባል እና ቃል አቀባይ ዶክተር በያን አሶባ ርምጃው የፖለቲካ ምህዳሩን ያሰፋል የሚል ተስፋቸውን ገልጸዋል።

«ሽብረተኛ ተብለው ቀደም ብለው በፓርላማው እና አገዛዙ የተፈረጁ ድርጅቶችን አዋጅ ማንሳቱ በጣም ጥሩ እርምጃ እንደሆነ ነው እኛ የምንገነዘበው። በመጀመሪያም ደረጃ ስለ ሀገራችን ስለሕዝባችን ያገባናል የሚሉ ድርጅቶችን ከፖለቲካው ለማግለል ሆን ተብሎ የተሠራ ዴሞክራሲን የማፈን ሰብዓዊ መብትን የማፈን፤ ዜጎች በሀገራቸው ላይ ያላቸውን ተሳትፎ ለመገደብ የተደረገ አዋጅ እንጂ እነዚያ ድርጅቶች ሽብረተኛ ሆነው አልነበረም። ይህም በመሆኑ በአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አመራር ያን አዋጅ ማንሳቱ ትልቅ እና ትክክለኛ ርምጃ ነው የዴሞክራሲ ምህዳሩን ለማስፋት በጣም አጋዥነው።»  

በጉዳዩ ላይ የኦብነግን ምላሽ ለማካተት ያደረግነው ጥረት የሚመለከታቸው አካላት ስልኮቻቸው ስለማይሰሩ አልተሳካልንም።

ሸዋዬ ለገሠ

አርያም ተክሌ