1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ለኢትዮጵያ መንግስት ከኦነግ የተሰጠ ማስጠንቀቅያ 

Merga Yonas Bula
ማክሰኞ፣ ሐምሌ 10 2010

የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ አሕመድ ኤርትራን ሲጎበኙ ጎን ለጎን በአቶ ዳዉድ ኢብሳ የሚመራዉ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ፣ የኦነግ፣  ልዑካን ቡድን ጋር ሐምሌ 2 ቀን 2010 ዓ/ም ተገናኝቶ መወያየቱን ዘገባዎች ይጠቁማሉ።

https://p.dw.com/p/31ccK
 Logo Oromo Liberation Front

ይህን የተጀመረዉን «የሰለም ዉይይት» ባለፈዉ ሳምንት ሃሙስ ለማሳካት ግንባሩ ግዜያዊ የተኩስ አቁም አዉጆ ነበር። ይሁን እንጅ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር፣ ኦነግ፣ በትላንትናዉ እለት ባወጣዉ መግለጫ የኢትዮጵያ መንግስት በአንድ ጎን የሰላም ድርድር እያለ በሌላ በኩል ደግሞ በምዕራብ ኦሮሚያ የሚገኙ የግንባሩ ጦር ላይ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸዉን የመከላክያ ሰራዊት እያሰማራ እንደምገኝ ገልፀዋል።
ከግዜያዊ ጦርነት ማቆም ወደ ዳግም ጦርነት ማወጅ የተገባበትን ምክንያት የኦነግ ሥራ አስፈፃሚ አባልና ቃል አቀባይ አቶ ቶሌራ አዳባ እንደሚከተለዉ ያብራራሉ፤ «የእርቅ ዉይይቱን ወደ ፊት ለመዉሰድ ግንባሩ ግዜያዊ ቱክስ አቁም አዉጀዋል። ግን ከአዋጁ ወዲህ የኦነግ ሠራዊት ከተለያዩ ርምጃዎች ራሱን ቆጥበዋል። ይህን እድል በመጠቀም የኢትዮጵያ መንግስት በሦስተ አቅጣጫዎች፣ ማለትም በከጋምቤላ ወደ ደቢዶሎ፤ ከነቀምት ወደ ግጊምቢና ማንድ አከባቢ እንዲሁም ከአሶሳ ወደ ቤጊ ትልቅ ሠራዊት በማሰማራት ስልታዊ የሆኑት ቦታዎችን መቆጣጠር ቀጥሎአል። የኦነግ ሠራዊት ይህን እንቅስቃሴ ያይ ነበር። ይሁን እንጅ ለእርቁ ሲባል ምንም ርምጃ አለወሰደም። ይህ ደግሞ ሕዝብም ሆነ ሠራዊቱን አሳስበዋል።»

ይህ የመንግስት ርምጃ ከሠላም ዉይይቱ ጋር የሚጻረር ስለሆነ ከፍተኛ ቁጥር ያለዉን ሠራዊት ወደ ቦታ ማሰማራት አስፈላጊ አልነበረም የሚሉት አቶ ቶሌራ ከዚህ በኋላ ለሚፈፀመዉ ነገር መንግስት ሃላፊነቱ የመንግስት መሆኑን ለማሳወቅ መግለጫ ማዉጣታቸዉንም አክለዉ ገልፀዋል። በዚህ ጉዳይ ላይ በኢትዮጵያ መንግስት በኩል ማብራርያ ለማግኘት በተደጋጋም ያደረግነዉ የስልክ ሙከራ አልተሳካም።

በምዕራብ ኦሮሚያ፣ በተለይም በምዕራብ ወለጋና በቀለም ወለጋ አካባቢ የፀጥታ ሁኔታው ምን ይመስላል ብለን የአከባቢዉን ነዋሪዎች ጠይቀን ነበር። የደምቢ ዶሎ ነዋሪ የሆኑ ግን ስማቸዉ እንዳይጠቅስ የፈለጉ ግለሰብ በአከብያቸዉ የአጋር መከላክያ ሠራዊቱ እያደረሰ ይገኛል ያሉት ጫና ከበፊቱም ያልተናነሰ መሆኑን ይናገራል።

ስማቸዉ እንዳይጠቅስ የፈለጉ ግለሰብ: «ባለፉት ሳምንታት ዉስጥ እንኳን ብዙ ወጣቶች ላይ የተለያዩ አደጋዎች እየደረሰ ይገኛል። ለምሳሌ ጎማ አንገት ላይ በማጥላቅ፣ ቁጭ ብድግ እንድሰሩ ማሰደረግ፣ የተሰቀለዉን ባንዲራ አዉርዶ ሽናበት እያሉ የሚያስገድዱበት ሁኔታ አለ። ሕዝቡ  ታገዶ  ኦነግ ለመሆን የተፈለገበት ምክንያትም እየደረሰበት ያለዉን ጫና ጠልቶ እንጂ በአገሪቱ እየተደረጉ ያሉት ጥቃቅን ለዉጦችን በመጥላት አይደለም።»

ወደ ተጠቀሱት ቦታዎች ተሰማርተዋል የተባሉት የአገሪቱ የመከላክያ ኃይል የኦነግ ሠራዊት ያለበትን ቦታ መፈተሽ መጀመራቸዉን የዓይን እማኞች ጠቅሰዋል።

የዓይን እማኙ: «የኦነግ ሠራዊትም ከዚህ ድርጊት ራሱን ለመከላከል ለምሳሌ ትላንት ከሰዓት በዋላ ዋቾ የተባለች ቦታ ላይ የመከላክያ ሰራዊቱ ላይ ርምጃ ወሰደዋል። ትላንት ማታ ከአምስት ሰዓት ጀምሮ  በደምቢ ዶሎ ከተማ በ03/05 ና 07 ቀበሌዎች ዉስጥ ተኩስ ስሰማም ነበር።»

ማቻራ የተባለች ቦታም ሁለቱ ሠራዊቶች መጋጨታቸዉን ያረጋገጡት የግንባሩ ቃል አቀባይ አቶ ቶሌራ አዳባ፤ የተጀመረዉ  ዉይይት በሰላም እንዲጠናቀቅ እንደሚፈልጉ አክለዉ ገልፀዋል። አቶ ቶሌራ አዳባ: «መንግስት ሠላማዊ መፍትሔን ወደ ጎን በመተዉ፣ ወደ ጦርነት የሚገባ ከሆነ ያለን ምርጫ እንደ በፊቱ ከሕዝቡ ጋር በመሆን የኛን ትግል መቀጠል ነዉ።»

መቀመጫዉን ኤርትራ ያደረገዉ ኦነግ ኢ/ኤ/አ ከ1991 ዓ/ም ጀምሮ ሠራዊቱን በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በማሰማራት ከኢሕአዴግ መንግስት ጋር እየታገለ ይገኛል።


መርጋ ዮናስ
አዜብ ታደሰ