1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሂዩማን ራይትስ ዎች የኢትዮጵያ መንግስትን ወቀሰ

ቅዳሜ፣ ጥቅምት 10 2011

ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋም ሂዩማን ራይትስ ዎች በኢትዮጵያ በቅርቡ የተካሄዱት የጅምላ እስሮች እና "አመለካከትን የመቀየር ስልጠናዎች" ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የጀመሯቸውን ፖለቲካዊ ማሻሻያዎች አደጋ ላይ የሚጥሉ ናቸው አለ።

https://p.dw.com/p/36svK
Human Rights Watch Logo

ሂዩማን ራይትስ ዎች ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የአፈና ስልቶችን እንዲያስቆሙ ጠየቀ። በኢትዮጵያ በቅርቡ የተካሄዱት የጅምላ እስሮች እና "አመለካከትን የመቀየር ስልጠናዎች" ጠቅላይ ሚኒስትሩ የጀመሯቸውን ፖለቲካዊ ማሻሻያዎች አደጋ ላይ የሚጥሉ ናቸው ብሏል። 

ተቋሙ ዛሬ ባወጣው መግለጫ  በሺህዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች ከአዲስ አበባ ታፍሰው በወታደራዊ ካምፖች በግዴታ ስልጠና እንዲወስዱ መደረጉን ተችቷል። ሰዎችን በወታደራዊ ካምፖች አቆይቶ ስለ መንግስት ፖሊሲዎች እና አመለካከቶች የማጥመቅ ስልጠና መስጠት ቀደም ባሉት ጊዜያት የተለመደ እንደነበር ተቋሙ አስታውሷል። በካምፖቹ የሚቆዩ ታሳሪዎች ከባባድ የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎች እንዲሰሩ እንደሚገደዱም ጠቁሟል።

እንደዚህ አይነት ማቆያዎች “ምንም ዓይነት የህግ መሠረት” የላቸውም ያለው መግለጫው በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ መንግስት እንደገና ለአገልግሎት መዋላቸው “አሳሳቢ” መሆኑን ጠቅሷል። ሁኔታውን “የጸጥታ ኃይሎች የዘፈቀደ እስር ይፈጽሙበት ወደነበረበት ጊዜ የመመለስ ምልክትም ነው” ብሎታል። ወደ ጅምላ እስሮች እና "አመለካከትን የመቀየር ስልጠናዎች" በመመለስ  “ኢትዮጵያ በቀላሉ ወደኋላ ልትንሸራተት ትችላለች” ሲልም በመግለጫው አስጠንቅቋል። ይህንን ለማስቀረት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የተሃድሶ ስልጠና የሚሰጥባቸውን ካምፖች እንዲዘጉ እና የዘፈቀደ እስርንም በማስቆም ቁርጠኝነታቸውን እንዲያሳዩ ሂዩማን ራይትስ ዎች ጠይቋል። 

ተስፋለም ወልደየስ

ልደት አበበ