1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሀበሻ የአረጋዉያንና ምስኪኖች መርጃ ማዕከል

ሐሙስ፣ ሐምሌ 26 2010

የወገኖቻችን ስቃይ በተለይ በክፍለ ሃገሩ ላይ እጅግ እጅግ የመረረ ነዉ። ማኅበረሰቡ በማዕከሉ ተረጅዎች ቢaneስ መጥቶ ቢጎበኘን ጥሩ ነበር። ሥራችን ምን ያህል ጊዜ፤ እድሜ፤ ጉልበት፤ እንደሚጠይቅ አይቶ ባለዉ አቅም ቢረዳን እንላለን። ይህን ችግራችንን ከኛ ማኅበረሰብ ዉጭ ለማንም መንገር አንችልም።

https://p.dw.com/p/32VmX
Altenheim in Äthiopien, Debere Brehan
ምስል Mulugeta Mamo

ኢትዮጵያዉያን የመረዳዳት ባህላችንን ልናድስ ይገባል

የወገኖቻችን ስቃይ በተለይ በክፍለ ሃገራት ጎልቶ የሚታይ መሆኑ እሙን ነዉ። የወገኖቻችን ስቃይ በተለይ በክፍለ ሃገሩ ላይ እጅግ እጅግ የመረረ ነዉ። ማኅበረሰቡ በዚህ መርጃ ድርጅት ያሉትን ተረጅዎች ቢያንስ መጥቶ ቢጎበኘን ጥሩ ነበር። ሥራችን ምን ያህል ጊዜ፤ ጤና፤ እድሜ፤ ጉልበት፤ እንደሚጠይቅ አይቶ ባለዉ አቅም ቢረዳን እንላለን። ይህን ችግራችንን ከኛ ማኅበረሰብ ዉጭ ለማንም መንገር አንችልም ። ምክንያቱም ችግሩ እኛዉ ጋር ያለ የኛዉ ነዉና ነዉ። ስለዚህ በሃገር ዉስጥም ሆነ ከሃገር ዉጭ ለሚገኙ ወገኖቻችን የድረሱልን ጥሪ ማስተላለፍ እንፈልጋለን።  ሰዉ እንኳ መቅረበርያ መጓጓዣ የለንም። ድርጅቱ ተረጅዎችን ወደ ሃኪም ቤት የሚያመላልስበት  አልያም  ለቀብር የሚያጓጉዝበት መኪና እንኩዋ የለዉም።»

«ሀበሻ የአረጋዉያን እና ምስኪኖች መርጃ ማዕከል ይባላል፤  ደብረ ብርሃን ላይ ነዉ እየሰራን ያለዉ። ሥራችንን የጀመርነዉ እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር 2008 ዓም ነዉ። ማዕከሉ በአሁኑ ሰዓት ከ 80 በላይ ወገኖች ከወደቁበት አንስቶ እየረዳ ይገኛል።    

Altenheim in Äthiopien  /Debere Brehan
ምስል DW/M. Mamo

ዮርዳኖስ ፍቃዱ ተክለ ማርያም፤ ይባላል ማክሰኞ ምሽት ከዚህ ዓለም በሞት የተለየዉ የአርቲስት ፍቃዱ ተክለማርያም ልጅ ነዉ። በርግጥ ከኛ የተለየዉን የእዉቁን የአርቲስት ፍቃዱ ተክለ ማርያምን ልጅ ዮርዳኖስን በደብረ ብርሃን የዛሬ ሦስት ዓመት ግድም ስላቋቋመዉ ሀበሻ አረጋዉያን እና ምስኪኖች መርጃ ማዕከል ልንጠይቀዉ ነበር በሳምንቱ መጀመርያ በስልክ ደዉለን ያገኘነዉ። ዮርዳኖስን ስለ ማዕከሉ፤ ስለአባቱ ጤንነት ጠይቀን ተሰነባበትን ቃለ ምልልሱን ለዛሬ አየር ላይ ለማዋል እንዳሰብን በመንገር ተሰናባበትን። ማክሰኞ ምሽት ግን ከመድረክ እስከ ሲኒማ ስክሪን ወርቃማ ታሪክን ያተመው አርቲስት ፍቃዱ ተክለ ማርያም ላይመለስ ማሸለቡን ሰማን፤ አርቲስት ፈቃዱ ተክለ ማርያም በኪነ-ጥበቡ ዘርፍ ብቻ ሳይሆን፤ ሰብዓዊ ርዳታንም በመቸሩ በብዙዎች ልብ ዘንድ ሕያዉ ነዉ። በተለይ  ደብረ ብርሃን የሚገኘዉን ሀበሻ አረጋዉያን እና ምስኪኖች መርጃ ድርጅት በቦርድ አባልነት ሲያገለግል ቦታዉ ድረስ እየሄደ አረጋዉያንን፤ ወላጆቻቸዉን ላጡ ሕጻናት ድጋፍ ሲሰጥ ታይታን ስለማይፈልግ ብቻ የሚሰራዉን እንደማይናገር እንደሱ በማዕከሉ በፈቃደኝነት የሚያገለግሉ ይናገራሉ። የማዕከሉ መስራች የአርቲስ ፈቃዱ ተክለ ማርያም ልጅ ዮርዳኖስም አባቱ ሰዉን ሲረዳ ለራሱ ሲል እንጂ ለሰዉ መናገርን እንደማይፈልግ ነዉ የተናገረዉ።   

«አዎ አባቴ ፍቃዱ ሠዎችን በጣም ይረዳይ። እንደዉም እሱ ሰዉ እንዲawuq,ዉ ስለማይፈልግ ከሃይማኖት ጋር በማያያዝ ነዉ የሚያደርገዉ። ብዙ የእርዳታ ሥራዎችን ያደርግ ነበር። ሕዝብ እንዲህ መታመሙን ሳይሰማ በነበረበት ጊዜ ማዕከሉን በጣም ብዙ ደግፎአል ። ማዕከሉን ሁለት ሦስት ጊዜ መጥቶ ጎብኝቶአል። የአበሻ ማዕከል የቦርድ አባልም ነዉ። ሌላዉ ፀሐፊ ተዉኔት ዉድነህ ክፍሌም የሀበሻ መርጃ ማዕከል የቦርድ አባል ነዉ። አርቲስት መቅደስ ፀጋዬም የማዕከሉ አምባሳደር ናት። ሌሎችም ባለሞያዎች እንዲሁ ለማዕከሉ የተለያዮ ድጋፍን ያደርጋሉ። » 

ሀበሻ አረጋዉያን እና ምስኪኖች መርጃ ማዕከል ዉስጥ አረጋዉያን ወላጆቻቸዉን በሞትም ሆነ በሌላ የተለያዩ ምክንያቶች ያጡ ታዳጊ ሕጻናት እንዲሁም የአዕምሮ ሕሙማን ተጠልለዉ ርዳታን ያገኛሉ። ወጣት ዮርዳኖስ ይህን የመርጃ ማዕከል ለማቋቋም የወሰነዉ ከክፍለሃገር መጥተዉ አዲስ አበባ ጎዳና ላይ እየተሰቃዩ የሚገኙ አዛዉንቶችን ካየ በኋላ እንደሆን ተናግሮአል።

«አዲስ አበባ ላይ የሚታየዉ ነገር ትንሽ ልብን ይነካል ። ለዛም ነዉ ይህን ነገር ለመስራት የተነሳሳሁት። ምክንያቱም ከክፍለሃገር የአካል ጉዳተኞች አይነስዉራን አዛዉንቶች መጥተዉ አዲስ አበባ ጎዳና ላይ ተጥለዉ ለልመና ይዳረጋሉ። ስለዚህም ይህን ችግር መቅረፍ የምንችለዉ አዲስ አበባ ላይ በመስራት ሳይሆን እዝያዉ እነዚህ ሰዎች ከመጡበት ፤ አልያም ችግሩ በአለበት የወደቁትን በማንሳት፤ ማኅበረሰቡም ላይ የአስተሳሰብ ለዉጥ በማምጣት ነገ ሌሎች ወገኖቻችንን እንዲጠበቁ በማሰብ ነዉ። በማዕከሉ የሚረዱ አረጋዉያን፤ ወላጆቻቸዉን ያጡ ሕጻናት፤ መሄድ የማይችሉ ጎልማሶች፤ የአይምሮ ህመምቶኞች ይገኛሉ። »

Altenheim in Äthiopien  /Debere Brehan
ምስል DW/M. Mamo

ወጣት ዮርዳኖስ ሀበሻ የአረጋዉያንና ምስኪኖች መርጃ ማዕከል ማስተባብርያ ቢሮ አዲስ አበባ ላይ መክፈቱን ተናግሮአል። የርዳታ ማዕከሉ ከደብረ ብርሃን ከተማ ራቅ ብላ ከበምትገኘዉ አጣዬ ከተማ ላይ ሁለተና ቅርንጫፍን ከፍቶአል። 

በጀርመን ነዋሪ የሆትና የሀበሻ አረጋዉያንን እና ምስኪኖች መርጃ ማዕከል ዉስጥ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ኃላፊ አቶ ሙሉጌታ ማሞ ፤ የአረጋዉያኑን እና የምስኪኖች መርጃ ማዕከሉን ይደግፋሉ። በቅርቡ እዚያዉ ደብረብርሃን አንድ ወር ቆይተዉ እንደመጡም ነግረዉናል።

አቶ ሙሉጌታ የመረዳዳት ባህላችን ማጠናከር ይኖርብናል ያሉት አቶ ሙሉጌታ በተለይ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የሰሞኑ ዉጭ ለሚኖር ኢትዮጵያዊ ያስተላለፉትን ጥሪን ከልብ ልናጤን ይገባናል ሲሉ አስምረዉበታል።

የወገኖቻችን ስቃይ በተለይ በክፍለ ሃገራት ጎልቶ የሚታይ መሆኑ እሙን ነዉ፤ ሲሉ ጥሪ ዉን ያስተላለፈዉ የሀበሻ የአረጋዉያን እና የምስኪኖች መርጃ ማዕከል መስራች ዮርዳኖስ ፍቃዱ ተክለማርያም በበኩሉ ፤ «ወገን ስለወገኑ ትንሽ ወጣ ብሎ ቢያስብ ጥሩ ነዉ ብዬ አስባለሁ። የወገኖቻችን ስቃይ በተለይ በክፍለሃገሩ ላይ እጅግ እጅግ የመረረ ነዉ፤ እጅግ የሚያሳዝን  ነዉ። ማኅበረሰቡ በዚህ መርጃ ድርጅት ያሉትን ተረጅዎች ቢያንስ መጥቶ ቢጎበኘን ጥሩ ነበር። ሥራችን ምን ያህል ጊዜ፤ ጤና፤ እድሜ፤ ጉልበት፤ እንደሚጠይቅ አይቶ ባለዉ አቅም ቢረዳን እንላለን። ርዳታዉ ከተቻለ በገንዘብ ፤ አልያም ቁሳቁስ በመስጠት፤ አልያም ደግሞ በጉልበት ይሆናል። ተረጅዎችን ልብስ በማጠብ፤ ጥፍር በመቁረጥ፤ ገላ በማጠብ፤ በፀሎት ሊሆን ይችላል።  ይህን ችግራችንን ከኛ ማኅበረሰብ ዉጭ ለማንም መንገር አንችልም ። ምክንያቱም ችግሩ እኛዉ ጋር ያለ የኛዉ ነዉና ነዉ። ስለዚህ በሃገር ዉስጥም ሆነ ከሃገር ዉጭ ለሚገኙ ወገኖቻችን የድረሱልን ጥሪ ማስተላለፍ እንፈልጋለን።  ሰዉ እንኳ መቅረበርያ መጓጓዣ የለንም። ድርጅቱ ተረጅዎችን ወደ ሃኪም ቤት የሚያመላልስበት  መኪና እንኩዋ የለዉም።»

Altenheim in Äthiopien  /Debere Brehan
ምስል DW/M. Mamo

በሀበሻ የአረጋዉያን እና የምስኪኖች ማዕከል በቦርድ አባልነት በማገልገል ደካሞችን ሲረዳ የቆየዉ ታዋቂዉ አርቲስት ፍቃዱ ተክለማርያም ግብዓተ መሪቱ ቢፈፀምም ሥራዉ ሕያዉ ሆኖ ትዉልድ ሲያስታዉሰዉ እና ቅን ሥራዉን ሲከተል ይኖራል። ቃለ ምልልስ የሰጠን ልጁ ዮርዳኖስ ፍቃዱ ተክለማርያም  እና ቤተሰቡን ወዳጅ ዘመዶቹን መፅናናትን እየተመኘን፤ ማዕከሉ ደብረ ብርሃን የሚገኘዉን የአዛዉንቶችና ምስኪኖች መርጃ ማዕከል በተቻላችሁ ሁሉ እንድትረዱ እንድትጎበኙ ሲል የሰጠዉን ጥሪ በመድገም ሙሉ ጥንቅሩን እንዲያደምጡ እንጋብዛለን።

አዜብ ታደሰ

ሸዋዬ ለገሠ