ፔተር ሊምቡርግ የወደፊቱ የዶይቸቬለ አስተዳዳሪ
እሑድ፣ መጋቢት 8 2005
የጀርመን ቴሌቪዥን ጣቢያ ፣ የፕሮዚብን ዛት አይንስ የኢንፎርሜሽን ክፍል ሃላፊ ሊምቡርግ ፣ በመጀመሪያው ዙር ምርጫ በአብላጫ ድምፅ ነው የተመረጡት ። ከ17ቱ የቦርዱ አባላት 14 ቱ የድጋፍ ድምፅ ሲሰጧቸው አንድ የተቃውሞ ና 2 ድምፀ ተዐቅቦም ነበር ።
ፔተር ሊምቡርግ ፣ እ ጎ አ መስከረም 30 2013 የሥልጣን ዘመናቸው የሚያከትመውን የ68 አመቱን ኤሪክ ቤተርማንን ተክተው ያገለግላሉ ። ቤተርማን፤ እ ጎ አ ከ 2001 ዓ ም አንስቶ ዶይቸ ቬለን ያስተዳደሩና ፤ ድርጅቱ አዳዲስ አገልግሎቶችን እንዲያቀርብ በመቀየስ ጭምር የሚታወሱ ስራ አስኪያጅ ናቸው ።
« ዶይቸ ቬለ የጀመረውን አዳዲስ አገልግሎቶች የበለጠ አጠናክሮ የጀርመንን የአለም አቀፍ የሚዲያ ትኩረት እንዲያሻሽል ፔተር ሊምቡርግ የሚጠበቅባቸውን በሙሉ የሚያሟሉ ጋዜጠኛ ናቸው» ሲሉ፤ ሽሚት ተናግረዋል።
በተለያዩ ቋንቋዎች የዶቼቬለን የመገናና ብዙሃን አገልግሎት ማስፋፋት
የ 52 አመቱ ሊምቡርግ የዶቹቬለ የመገናኛ ብዙሃን ስርጭት ቦርድ በርሳቸው ላይ ፅኑ እምነት በመጣሉ አመስግነዋል ። « በሚመጡት አመታት አገራችን በአለም ውስጥ ያላትን ተቀባይነት ለማጎልበት ካለው ተግዳሮት አንፃር ባለኝ አቅም ሁሉ የሚቻለኝን አደርጋለሁ ። ከወጣትነቴ አንስቶ ከጀርመን ውጭ ባሳለፍኳቸው ጊዜያት የዶይቸ ቬለ ዝግጅቶች ጠቃሚ የህይወት ተሞክሮዮ አካል ነበሩ ። ከባልደረቦቼ ጋር የዶቼቬለን የጋዜጠኝነት በጎ ስም በመጠበቅ ፣ የራድዮ ጣቢያውን የተለያዩ ቋንቋዎችና የተለያዩ የመገናና ብዙሃን አገልግሎቶች ይበልጥ ማዳበር እፈልጋለሁ። ሌላው ግቤ ዶቼቬለ እንደ ARD እና ZDF ካሉ ለህብረተሰቡ አገልግሎት ከሚሰጡ ከሌሎች የጀርመን ጣቢያዎች ጋ ትብብሩን ይበልጥ ማጠናከር ነው ። »
ፔተር ሊምቡርግ የብሔራዊ ወታደራዊ አገልግሎት ካጠናቀቁ በኋላ በቦን ከተማ የህግ ትምህርት አጥንተዋል ። እ ጎ አ 1987 ዓ ም የመጀመሪያውን የህግ ብሔራዊ ፈተና ወሰዱ። ከዚያም እጎአ ከ1988 እስከ 1989 በጀርመን የቴሌቪዥን ጣቢያ (DFA) በቦን እና በለንደን ከተማ የጋዜጠኝነት ስልጠና ወስደዋል ። በቀድሞዋ የምስራቅ ጀርመን ከተማ ላይፕዚግ በዘጋቢነት የሰሩት ሊምቡርግ እጎአ ከ1990 ጀምሮ የአውሮፓ እና የኔቶ ቃል አቀባይ በመሆን ለጀርመን ዲ-ኤፍ-ኤ እና ዛት-አይንስ ጣቢያዎች ከብራስልስ ይዘግቡም ነበር ። እጎአ በ1996 የፕሮዚብን ጣቢያን ሃላፊነት ተረከቡ ። በ 1999 የ N24 ቴሌቪዥን ጣቢያ ዋና አዘጋጅነት እና በፕሮዚብን ጣቢያ የፖለቲካ ክፍል ኃላፊነት ማገልገል ጀመሩ። እጎአ 2004/05 እና 2008/09 ከበርሊን በሚሰራጨው ፑል-በተባለው የግል ቴሌቬዥን ጣቢያ ዋና ስራ አስኪያጅነት ፣ ከ2008-2010 ደግሞ ተመልሰው በ N24 ጣቢያ በዋና አዘጋጅነት አገልግለዋል ። ከ 2008 አም አንስቶ የዛት አይንስ ቴሌቪዥን ዜና አቅራቢ፣ ከ2010 ዓም አንስቶ ደግሞ የፕሮ ዚብን ዛት አይንስ ነባር ምክትል ፕሬዝዳንትም ነበሩ ። ሊምቡርግ የጀርመን ፌደራላዊ ምክር ቤት የመገናኛ ብዙኃን ሽልማት ዳኞች ሊቀመንበር፣ አክስል ሽፕሪንገር አሳታሚ ድርጅት -ለወጣት ጋዜጠኞች የሚሰጠው ሽልማት ዳኞች ቡድን አባል፣ የጀርመን የጳጳሳት ጉባዔ አሳታሚ ኮሚሽን አማካሪ እና የካቶሊካዊያን የግብረ ሰናይ ድርጅት የ« ማልቴዘር »አባልም በመሆን አገልግለዋል። ቦን ከተማ የተወለዱት ሊምቡርግ ፣ ያደጉት ሮም ፣ፓሪስ አቴንስና ብራስልስ ነው ። ሊምቡርግ ባለትዳር እና የ ሶስት ልጆች አባት ናቸው።
ዮሀንስ ሆፍማን
ልደት አበበ
ሒሩት መለሰ