«ፍሮንቴክስ» የቀረበበትን ወቀሳ ማመኑ
ዓርብ፣ ጥቅምት 8 2006ድርጅቱ ለአንድ የጀርመን ቴሌቬዥን በሰጠው ቃለ ምልልስ በአንዳንድ አጋጣሚዎች ስደተኞች ወደ ሶስተኛ ሃገራት በኃይል እንዲመለሱ መደረጉን አምኗል ። ለስደተኞች መብት የሚከራከሩ ድርጅቶች«ፍሮንቴክስ» የፈፀመው ተግባር ዓለም ዓቀፍ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎችን የሚፃረር ነው ሲሉ ይከሳሉ ። ሂሩት መለሰ ።
እጎአ በ2004 የተቋቋመው «ፍሮንቴክስ» ለአውሮፓ ህብረት አባል ሃገራት ድንበር ጥበቃ እገዛ የሚያደርግ ድርጅት ነው ። ይኽው ድርጅት በአውሮፓ ህብረት የሰብዓዊ መብቶች ህግጋት መሠረት የህብረቱ አባል ሃገራት የድንበር አስተዳደር መስራቱን የሚከታተልና የሚያስተባብር መስሪያ ቤት ነው ።
ይሁንና የስደተኞች መብት ተሟጋቾች እንደሚሉት ድርጅቱ ከተቋቋመበት ዓላማ ውጭ የስደተኞችን መብት ይጥሳል ፤ ስደተኞቹንም ለአደጋ ያጋልጣል ። ድርጅቱን በዚህ ከሚወቅሱት የስደተኞች መብት ተሟጋች ድርጅቶች ውስጥ አባሻ ኤጀንሲ የተባለው ለስደተኞች እርዳታ የሚሰጥ ግብረሰናይ ድርጅት ይገኝበታል ። የአባሻ ኤጀንሲ ሃላፊ አባ ሙሴ ዘርዓይ ድርጅታው ፍሪሮንቴክስን የሚወቅብስበትን ምክንያት ያብራራሉ ።
ከዚያ ይልቅ እንደ አባ ሙሴ ፍሮንቴክስ በሰብዓዊነት የስደተኞች ህይወት ለመታደግ ቅድሚያ መስጠት ነበረበት ።
ፍሮንቴክስ ከአንድ ዓመት በፊት ስደተኞች ወደ ሌላ ሶስተኛ አገር እንዲመለሱ በማድረግ ሂደት ኃይል በመጠቀሙ የአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት እርምጃው ኢሰብዓዊ ነው ሲል ብይን አሳልፎበት ነበር ። ይሁንና ምግባሩ አለመቆሙን ARD የተባለው የጀርመን ቴሌቪዥን ጣቢያ ባደረገው ምርመራ ደርሶበታል ። በዚሁ ጉዳይ ላይ ለቴሌቪዥን ጣቢያው ቃለ ምልልስ የሰጡት የድርጅቱ ሃላፊ ኢካ ላይቲነን ስደተኞችን በኃይል ወደ መጡበት እንዲመለሱ ማድረግ ተቀባይነት እንደሌለው ለመጀመሪያ ጊዜ ተናግረዋል ።
ሃላፊዋ የፍሮንቴክስ የሥራ ባልደረቦችም ስደተኞችን ጠርዞ ወደ ሶስተኛ ሃገራት በመላክ ተሳትፈውበታል የሚባለውንም በአንዳንድ ሁኔታዎች አልተደረገም ለማለት አይቻልም ሲሉ አምነዋል ። በቅርቡ በኢጣልያዋ የላምፔዱዛ ደሴት አቅራቢያ ወደ 364 የሚደርሱ ስደተኞች ህይወት ከጠፋበት የጀልባ መስጠም አደጋ በኋላ የአውሮፓ ህብረት አባል ሃገራት የሃገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሮች ባካሄዱት ስብሰባ ፍሮንቴክስን ለማጠናከር ተስማምተዋል ። አባ ሙሴ ፍሮንቴክስ የሚጠናከረው ስደተኞችን ወደ መጡበት ለመመለስ መሆን የለበትም ይላሉ
ሂሩት መለሰ
አርያም ተክሌ