1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

“ፌየር ትሬድ” በመስፋፋት ሂደት

ረቡዕ፣ ሚያዝያ 20 2002

የታዳጊ ሃገራት አምራቾች በገበያ ላይ የተሻለ ሁኔታና ቀጣይ ሕልውና እንዲኖራቸው ለማድረግ በተደራጀ መልክ የሚካሄደው ማሕበራዊ የገበያ እንቅስቃሴ ፌየር-ትሬድ፤ ፍትሃዊ ንግድ በመባል ይታወቃል።

https://p.dw.com/p/N8mF

ንግዱ በተለይም ከታዳጊው ዓለም ወደ በለጸጉት ሃገራት የሚገቡ ምርቶችን የሚመለከት ነው። የዕጅ ስራ ውጤቶች፣ ቡና፣ ኮኮ፣ ሻይ፣ ሙዝና ማር፤ እንዲሁም ጥጥ፣ ፍራፍሬና አበቦችን የመሳሰሉት በዚህ ንግድ ውስጥ የሚጠቃለሉት ናቸው። ንግዱ ከጠቅላላው የዓለም ንግድሲነጻጸር ገና ብዙ ቢቀረውም ከዓመት ወደ ዓመት ከፍተኛ ዕድገት እያሳየ ነው የመጣው። በዚህ በጀርመን የዚህ ፍትሃዊ ንግድ አራማጅ ድርጅት ትራንስፌየር በቅርቡ እንዳስታወቀው ባለፈው የኤኮኖሚ ቀውስ ዓመት 26 በመቶ ዕድገት ተደርጓል።

የፍትሃዊ ንግድ መለያ ማሕተም ሰፍሮባቸው በዓለምአቀፍ ደረጃ የሚሸጡት ምርቶች ዋጋ እጎ.አ. በ 2008 ዓ.ም. አራት ቢሊዮን ዶላር ወይም ሁለት ቢሊዮን ኤውሮ ገደማ ይጠጋ ነበር። ከዓመት ወደ ዓመት 21 በመቶ ዕድገት መሆኑ ነበር። መጠኑ እርግጥ ከዓለም ንግድ ስፋት ሲነጻጸር በጣሙን ጥቂት ነው። አንዳንዶቹ ምርቶች ከመሰላቸው ከሃያ እስከ ሃምሣ በመቶውን ድርሻ ቢይዙ ነው። ሆኖም የፍትሃዊው ንግድ አራማጅ ድርጅቶች በሰኔ ወር 2008 ባቀረቡት ግምት ከሰባት ሚሊዮን ተኩል የሚበልጡ አምራጮችና ቤተሰባቸው በፍትሃዊው ንግድ ገንዘብ የተካሄደው መዋቅራዊ ግንባታ፣ ቴክኒካዊ ድጋፍና የሕብረተሰብ ልማት ፕሮዤዎች ተጠቃሚዎች ነበሩ።

እርግጥ በፍትሃዊው ንግድ ላይ ያለው አመለካከት ቅይጥ ሆኖ ቆይቷል። በአንድ በኩል ተከታዩ እየጨመረና ዝነኛ እየሆነ ቢመጣም በሌላ በኩል ደግሞ ትችትን ማስከተሉም አልቀረም። በመጀመሪያ ደረጃ የንቅናቄው ዓላማ ለተገለሉ አምራቾች የገበያ ዕድል መክፈት፣ ከምርቱ ገዢዎች ማገናኘትና ከዓለም ገበያው የተሻለ ዋጋ እንዲያገኙ፣ ኑሯቸውን እንዲያሻሽሉ፤ እንዲሁም ዕውቀትና ብቃትን እንዲያዳብሩ ማድረግ ነው። ንቅናቄው የምርቱ አንሺዎች በሚገኙበት በበለጸገው ዓለምም ሕዝቡን ለዚሁ ለማንቃት ይጥራል።

የፍትሃዊው ንግድ ታሪክ ምናልባትም እስከ አርባኛዎቹ ዓመታት ድረስ መለስ የሚል ነው። በጊዜው የሃይማኖት ቡድኖችና ከመንግሥት ነጻ የሆኑ ድርጅቶች የፍትሃዊ ንግድ ምርቶችን በሰሜኑ ዓለም ገበዮች ለመሸጥ የመጀመሪያውን ሙከራ ያደርጋሉ። ዕቃዎቹም በአብዛኛው የዕጅ ስራ ውጤቶች ሲሆኑ እንደ መዋጮ ነበር የሚታዩት። የወቅቱ የፍትሃዊ ንግድ እንቅስቃሴ በአውሮፓ ቅርጽ መያዝ የጀመረው ግን በስልሣኛዎቹ ዓመታት ነው።

ወዲያው በ 1968 “ከዕርዳታ ይልቅ ንግድ” የሚለው ከበለጸጉ ሃገራት ጋር የሚደረግ ፍትሃዊ ንግድን የሚያስረግጥ መፈክር በተባበሩት መንግሥታት የንግድና የልማት ጉባዔ በዩንክታድ ተቀባይነት ያገኛል። በዓመቱም ኔዘርላንድ ውስጥ የፍትሃዊ ንግድን ዓላማ ሠሠረቱ ያደረገው የመጀመሪያው የዓለም መደብር ይከፈታል። ከ 60ኛዎቹ ዓመታት አጋማሽ ወዲህ አማራጩ የንግድ ድርጅቶች እየተበራከቱ ሲሄዱ ዛሬ መደብሮቹ በአብዛኛው የምዕራብ አውሮፓ አገሮች የተስፋፉ ናቸው።

ዕርምጃው ለግንዛቤ ያህል ከሞላ-ጎደል በአጭሩ ይህን የመሰለ ሲሆን የፍትሃዊው ንግድ ምርቶች ያለማቋረጥ ተወዳጅነት እያገኙ ከሄዱባቸው አገሮች አንዷም ጀርመን ናት። ጀርመናውያን ባለፈው ዓመት ለፍትሃዊው ንግድ ምርቶች 270 ሚሊዮን ኤውሮ ገደማ ሲያወጡ ይህም የ 26 ከመቶ ዕድገት በተለይ በኤኮኖሚ ቀውስ መሃል መገኘቱ የሚያስደንቅ ነው። የጀርመኑ የፍትሃዊ ንግድ ድርጅት የትራንስፌየር ስራ አስኪያጅ ዲተር ኦቨራት እንደሚሉት ለዕድገቱ ምክንያቱ እየተለወጠ የሚሄደው የፍጆተኛው ንቃተ-ህሊና ነው።

“የጀርመን ፍጆተኞች ስለ ችግር መስማቱ ብቻ የታከታቸው ይመስለኛል። እነርሱም መፍትሄ ማየት ይፈልጋሉ። እኛ በበኩላችን የፍትሃዊ ንግድ ምርቶችን በመፍጀት የተሻለች ዓለምን ለመፍጠር እንደሚቻል በግልጽ አሳይተናል። አሁን ደግሞ መደብሮች ሲበራከቱ የተሻለ አቅርቦትም አለ። ተቀባይነታችንም እየጨመረ በመሄድ ላይ ነው”

Transfair Flash-Galerie
ምስል Transfair

ይህም ሆኖ በዚህ በጀርመን በፍትሃዊ ንግድ የሚሸጡት ምርቶች ከጥቅሉ አንጻር ሲታዩ በጣሙን ጥቂቶች ናቸው። ከጠቅላላው ገበያ ያላቸው ድርሻ አንድ ከመቶ እንኳ የይሞላም። ቡናን ከወሰድን ለምሳሌ 0.5 ከመቶ ያህል ነው። ከሌሎች የአውሮፓ አገሮች ሲነጻጸር ገና ብዙ ቀዳዳ አለ ለማለት ይቻላል። ጀርመን ውስጥ እያንዳንዱ ተጠቃሚ ለፍትሃዊው ንግድ ምርት በያመቱ 3.20 ኤውሮ ብቻ የሚያወጣ ሲሆን ድርሻው ብሪታኒያ ውስጥ በነፍስ-ወከፍ 12 ኤውሮ፤ በስዊስ እንዲያውም 23 ኤውሮ ይደርሳል። ለዚህ ልዩነት ምክንያቱም እንደ ዲተር ኦቨራት አገላለጽ ከሆነ የጀርመናውያን በቅናሽ መደብሮች በተቻለ መጠን በርካሽ የመገብየት ብህርይ ነው።

“ጀርመን በዓለምአቀፍ ደረጃ የኑሮ ቁሳቁስ ገበያው የረከሰባት መሆኑን በቀላሉ መገንዘብ ያስፈልጋል። እዚህ በዓለምአቀፍ ንጽጽር ሰዉ ለኑሮ ቁሳቁስ ከገቢው የሚያወጣው ገንዘብ ከየትናውም ቦታ ዝቅ ያለ ነው። ርካሽ ምግብ የሚቀቀልባቸው በውድ መሣሪያዎች የተሞሉ ማዕድቤቶች አገር ነን ለማለት ይቻላል። በፍትሃዊው ንግድ ረገድ ሁኔታውን ለመለወጥና ፍላጎቱን ለማሳደግ ገና ብዙ ጥረት የሚያስፈልግ ነው”

አንዱ ጥረትም ኦቨራት እንደሚያስረዱት ታላላቆቹ ሱፐር-ማርኬቶችና ቅናሽ ዕቃ አቅራቢዎች በፍትሃዊ ንግድ የሚገኙ ምርቶችን ደርድረው እንዲሸጡ ማግባባት ይሆናል። ይህ ለምሳሌ አሁን ከኬንያና ከታንዛኒያ በሚገቡ አበቦች እየታየ ነው። በነገራችን ላይ አበባ ዛሬ ከቡና ቀጥሎ ሁለተኛው ትልቅ የፍትሃዊው ንግድ ዘርፍ ሆኖ ነው የሚገኘው። በሌላ በኩል ሙዝን በተመለከተ ሁኔታው ያን ያህል አርኪ አይደለም። በስዊስ ለምሳሌ ከጠቅላላው የሙዝ ንግድ ግማሹ የፍትሃዊ ንግድ ድርሻን ሲይዝ በዚህ በጀርመን ትልቅ የዋጋ ውጣ-ውረድ ፉክክር በመኖሩ ከመደብር መደርደሪያ እንኳ አይደርስም።

ይሁን እንጂ የፍትሃዊው ንግድ ጣራ ድርጅት ሃላፊ ሮን ካሜሮን ምርቶቹ የታዳጊ ሃገራት ዕቃዎችን በሚሸጡ በትናንሽ መደብሮች ብቻ ተወስነው ሊቀሩ አይገባም ባይ ናቸው። የካሜሮን ፍላጎት ታላላቆቹ ኩባንያዎችና የንግዱ ሰንሰለት ምርቶቹን እንዲቀበሉ መማረክ ነው።

“እርግጥ እኛ ከአማራጩ የንግድ እንቅስቃሴ፤ የአንድ ዓለም መደብር ከሚለው ወገን የመነጨን ነን። ይህ ደግሞ በጣም አስፈላጊ ነው። መሠረታችን ነው። ግን የገበያው ሃቅ ለየት ይላል። አብዛኛው ንግድ የሚካሄደው በዓለምአቀፍ ኩባንያዎች በኩል ነው። ቀደም ባለው ጊዜ ከኛ ጋር ምንም ነገር አይፈልጉም ነበር። አሁን ግን ፍትሃዊው ንግድ የተሻለ ምርት የሚፈልጉ ደንበኞችን ለማርካት መንገድ መሆኑ እየታያቸው ነው። እኛም በዚህ ረገድ በመተባበር ለተጨማሪ ሕዝብ የተሻለ የኑሮ ሁኔታን ለሚያስከትል ለውጥ አስተዋጽኦ ለማድረግ እንችላለን”

በእንግሊዝ ኔስትለንና ካርድበሪይን የመሳሰሉት ታላላቅ ኩባንያዎች ለምሳሌ ከአሁኑ የፍትሃዊ ንግድ ቾኮሌትን ለምርት ተግባራቸው ይገለገላሉ። በጀርመን ለጊዜው ይህ ሁኔታ ባይኖርም አንዱ ታዋቂ ኩባንያ ተመሳሳይ ዕርምጃ እንዲወስድ በተሥፋ ነው የሚጠበቀው። በሌሎች መስኮች ለምሳሌ በቡና ረገድ ስታርባክስ በአውሮፓም የፍትሃዊ ንግድ ምርትን ተጠቅሞ ኤስፕሬሶን ለጠጪዎች ያቀርባል። ቤን-ኤንድ-ጄሪይስ የተሰኘው አይስክሬም አምራች ደግሞ እስከ 2012 ማለት የሚቀጥሉትን ሁለት ዓመታት የፍትሃዊ ንግድ ምርቶችን ብቻ ነው የሚጠቀመው።

የፍትሃዊው ንግድ ዓላማ ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው በታዳጊ አገሮች ያሉ አምራቾች ከዓለም ገበያ ይልቅ ከፍ ያለ ዋጋ በማግኘት በተሻለ ሁኔታ እንዲጠቀሙ ማድረግ ነው። አምራቾቹ በዚሁ ንግድ ያገኙትን ተጨማሪ ገንዘብ በምን ተግባር ላይ ያውላሉ፤ ወሣኞቹ ራሳቸው ናቸው። ለምሳሌ በሕንድ የሩዝ ገበሬዎች እንዳደረጉት ምርትን ለማሳደግ የሚረዳ መሣሪያን መግዛቱ አንዱ አማራጭ ነው። ሮን ካሜሮን!

“ገበሬዎቹ የሩዝ ሜዳቸውን ብዙ ውሃ ሳያባክኑ ማጠጣት የሚችሉበት አንድ መሣሪያ እንዲኖራቸው ይፈልጋሉ። በዚህም የውሃ ፍጆታቸውን ከሃያ እስከ ሰላሣ በመቶ ይቀንሳሉ። የእርሻ ምርታቸውም በዚያው መጠን ይጨምራል። ይህ መዋዕለ-ነዋይ ደግሞ ኑሯቸውንና ከረጅም ጊዜ አንጻር ገቢያቸውንም እንዲሻሻል ነው ያደረገው። ይህ የተቻለው ታዲያ ፌየር-ትሬድ ምስጋና ይግባው በቀላል መሣሪያና በቀላል አጠቃቀም ነው”

ፍትሃዊው ንግድ በዚህ በያዝነው ዓመት ሂደትም ተሥፋ ሰጭ ሆኖ ነው የሚታየው። ስራ አስኪያጁ ዲተር ኦቨራት ዘንድሮም ባለሁለት አሃዝ ዕድገት እንደሚቻል ያምናሉ። ሕልማቸው በፊታችን 2012 ገቢያቸውን እጥፍ ገደማ ወደ 500 ሚሊዮን ኤውሮ አድጎ ማየት ነው። ይህ ለነገሩ በዚህ አገር ትልቅ ገንዘብ አይደለም። ንጽጽር ከተፈለገ ጀርመናውያን በያመቱ ለአንቅልፍ መድሃኒቶች ከሚያወጡት አይበልጥም።

MM/DW