ፊሊፒንስ ከሃያን በኃላ
የአደጋ ርዳታ ሰጪ ሰራተኞች ሃያን ባስከተለው ጥፋት የተጎዳውን ህዝብ ስቃይ ለመቀነስ ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛሉ።
ምስቅልቅሉ እና ግራ መጋባቱ ሁኔታ
ሃያን በፊሊፒንስ ከተሞች ላይ ግዙፍ ጥፋት አድርሶዋል። ከተሞችን ምድረ በዳ አስመስሏል። የስልክ እና የመብራት መስመሮች ተቋርጠዋል። የሟች እና የተጎጂው ቁጥር በየቀኑ ከፍ እያለ ነው። ሕዝቡን የመርዳቱ ግዙፍ ስራ ለመንግሥቱ የአደጋ ርዳታ ሰጪ መስሪያ ቤቶች ከአቅማቸው በላይ ሆኖባቸዋል። ስለዚህ ሕዝቡ ራሱን ለመርዳት እየሞከረ ነው።
የምግብ እጥረት
ከባዱ አውሎነፋስ ባለፈው አርብ የፊሊፒንስን የባህር ዳርቻ ዘልቆ ከገባ ወዲህ በተለይ በሌይቴ እና ሳማር አውራጃዎች ከፍተኛ የምግብ እጥረት ይታያል። በህይወት የተረፉ በያሉበት ምግብ ለማግኘት በመጣር ላይ ናቸው። በተለይ ሁኔታው እጅግ አዳጋች በሆነባት በታክሎባን ከተማ ግራ የተጋቡ ነዋሪዎች ከገበያ አዳራሾች ሩዝ እና ወተት ሲሰርቁ ተስተውለዋል።
የዝርፊያ ስጋት
ሰዎች፣ ኃይለኛው ዝናብ ሳይገታቸው፣ የተረፋቸውን ንብረት ይከላከላሉ። « ሰዎቹ አንድም በረሃብ ወይም ቤተሰቦቻቸውን ስለሞቱባቸው ራሳቸውን እየሳቱ ነው።» ይላሉ ኤንድሩው ፖሜዳ የተባሉ መምህር። ፍፁም ከጥቅም ውጪ በሆነችው ሌይቴ ሰዎች አንድ የምግብ ማመላለሻ ተሽከርካሪ አስቁመው መዝረፋቸው ተገልጿል። ተሽከርካሪው ለ 5000 ቤተሰብ የሚሆን የርዳታ እቃ ጭኖ ነበር።
ግፊያና ግርግር
ብዙ ሕዝብ የአንድ የምግብ አዳራሽን አጥር ዘለው ለመግባት ይጋፋሉ። «ታክሎባን ውስጥ ሁሉ ነገር ተመሰቃቅሏል።» ይላሉ የሌይቴ አውራጃ ከንቲካ-ሮዠር ማርካዶ። ሰዉ በተገኘው አጋጣሚ የሚያስፈልገውን ለማግኘት ይታገላል። በምግብ አዳራሽ ተጋፍቶ መግባት ብቻ ሳይሆን የገንዘብ ማውጪያ ማሽኖችን ሰብረው ገንዘብ ለመስረቅ የሞከሩም አልጠፉም።
ርዳታ በአየሩ መሥመር
የመጀመሪያ የርዳታ አቅርቦት የያዙ አይሮፕላኖች በስፍራው እየደረሱ ነው። የፊሊፒንስ የአየር ኃይል ሰራተኞች ከውጭው ጋ ግንኙነት የተቋረጠባቸውን የፓናይ ደሴት ነዋሪዎችን ለመርዳት ይሞክራሉ። ይሁንና፣ ርዳታውን ለተጎጂው የማድረሻ መንገድ የለም። መሠረተ ልማቱ በሙሉ ወድሟል። የቀይ መስቀል ሰውን ሁሉ በርዳታ አቀራረቡ ተግባር ላይ እንዲሠማራ እያበረታታ ይገኛል።
ብርድልብስ ከጀርመን
በፊሊፒንስ የደረሰው አደጋ ዓለም አቀፉን ማህበረሰብ አሳዝኗል። የተመድ ፣ የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን እና ሌሎች ሀገራት በጠቅላላው አፋጣኝ ድጋፍ ለመስጠት ተስማምተዋል። የአለም የምግብ ድርጅት 40 ቶን ምግብ ወደ ፊሊፒንስ ለመላክ አቅዷል። « ወርልጅ ቪዥን» እና «አክሲዮን ዶይችላንድ» የተሰኙት ድርጅቶችም ብርድልብስ እና ድንኳን በአይሮፕላን ልከዋል።
ስደት
ብዙዎች ፍፁም የወደመ መንደራቸውን ጥለው ወደ ሌላ ቦታ ተሰደዋል። 800 000 የሚሆን ሕዝብ ሁሉንም ነገር ትቶ አዲስ ወደሚሰናዱ ጊዜያዊ ማቆያ ሠፈሮች አምርቶዋል። በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች አስቀድመው ወደዚሁ ሥፍራ ደርሰዋል። በደረሰው አደጋ ወደ አራት ሚሊዮን የሚጠጋ ህዝብ ተጎጂ ሆኗል።
በቤተ ክርስትያን ውስጥ መጠለል
ቤተ መቅደስ ውስጥ የታጠበ ልብስ ተሰጥቶዋል። በሕይወት የተረፉ ብዙ ሰዎች ባለፈራረሱት አብያተ ክርስትያን ውስጥ መጠለያ አግኝተዋል። 80 ከመቶ የሚሆነው የፊሊፒንስ ሕዝብ የካቶሊክ እምነት ተከታይ ነው። በአደጋው በጣም የተጎዳው የሌይቴ አውራጃ፣ አደጋው ከመድረሱም በፊት ቢሆን፣ በፊሊፒንስ እጅግ ድሆች ከሚባሉት አካባቢዎች አንዱ ነው።
የድረሱልን ጥሪ
በአንድ ቤተ ክርስትያን አጥር ላይ ያካባቢው ነዋሪዎች በሕይወት ለተረፉ ሰዎች ርዳታ እንዲቀርብ የሰቀሉት የድረሱልን የርዳታ ጥሪ ይነበባል። ከጀርመን ጎን ዮናይትድ እስቴትስ፣ ኒውዚላንድ፣ አውስትሬሊያ፣ ጃፓን እና ሌሎችም ሀገራት ርዳታ ለምስጠት ቃል ገብተዋል። ሀገራቱ የቁሳቁስ ድጋፋ ብቻ ሳይሆን የሰው ኃይልም ወደ አካባቢው እየላኩ ነው።