1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ፉከራ እና ዛቻ

ነጋሽ መሐመድ
ሐሙስ፣ ነሐሴ 4 2009

 ሰሜን ኮሪያ ትንሽ ሐገር ናት።ከብዙዉ ዓለም የተነጠለች-ዝግ፤ በማዕቀብ የደከመች፤ በሐብታም ጠላቶችዋ የተከበበች-ደኃ ናት።ግን ግሪናዳ፤ ኢራቅ ወይም ሊቢያ አይደለችም።የድሮዋ ጃፓንም አይደለችም። እሷም ጋ ገመገም ዞሮ-የሚያነድ፤ ተመዘግዝጎ የሚያነፍር እሳት አለ።ፕሮፓጋንዳዉ ደግሞ ሞልቶ ይፈሳል።

https://p.dw.com/p/2i23p
Nordkorea | U-Boot-gestützte ballistische Rakete
ምስል picture-alliance/AP Photo

የኑክሌር ታጣቂዎቹ ዛቻና መዘዙ

ዩናይትድ ስቴትስ እና ሰሜን ኮሪያ አንዳቸዉ ሌላቸዉን ለመዉጋት የሚነዙትን ዛቻ እና ፉከራ እንደቀጠሉ ነዉ።ሁለቱ የኑክሌር ባለቤቶች አምርረዉ ዉጊያ ከገጠሙ የመጀመሪያ ዒላማ የሚሆኑት ደቡብ ኮሪያና ጃፓን  የሚፈራዉ እንዳይደርስ ይማፀናሉ።የሰሜን ኮሪያ የቅርብ ወዳጅ የምትባለዉ ቻይና የፕዮግዮንግ እና የዋሽግተን ገዢዎች ጠባቸዉን ከሚያቀጣጥል ንግግር እንዲታቀቡ አደራ ብላለች።ከዩናይትድ ስቴትስ ጎን የቆሙት የምዕራብ አዉሮጳ መንግሥታትም ሁለቱ ወገኖች ዲፕሎማሲያዊ መፍትሔ እንዲፈልጉ ይመክራሉ። 

በሚያስፈራ ግን ማራኪ ቃላት በተቀመረዉ ዛቻ ፉከራ ለወትሮዉ የተካኑት ፒዮንግዮንጎች ነበሩ።አሁን ዋሽግተኖች ሳይበልጧቸዉ አልቀሩም-እንድሜ ለትራምፕ።ዶላር ከመቁጠር-መደመር-መቀነስ ባንዴ የዓለምን ከፍተኛ የኑክሌር ቦምብ «ክምር» ወደ ታጠቀዉ ጦር ጠቅላይ አዛዥነት የተቀየሩት ዶናልድ ትራምፕ የጦር አዉዱንም እንደ ቴሌቪዢኑ ትርዒት ሊፈነጩበት ሳይዳዳቸዉ አልቀረም።
እርግጥ ነዉ ትራምፕ አልጀመሩትም።በመጀመሪያዉ የዓለም ጦርነት እንደወታደር የተዋጉ-ወታደሮችን ያሰለጠኑት፤ ሁለተኛዉን የዓለም ጦርነት እንደ ምክትልም እንደ ፕሬዝደትም የመሩት ሐሪ ኤስ ትሩማን በተመሳሳይ ቃላት ጃፓኖችን አስጠንቅቀዉ ነበር።«ዓለም አይቶት የማያዉቀዉ የጥፋት ዝናብ ይወርድባችኋል» ብለዉ።ዛቱ አደረጉት።ነሐሴ 6 እና 9-1945 እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር።
ዘንድሮ «የዓለም» የሚባል ጦርነት የለም።አሜሪካንን ያጠቃ መንግስትም የለም። ያለዉ በአሜሪካ አዉቶሚክ ቦምቦች ያለቁ ጃፓኖችን 72ኛ ዓመት መዘከር ነዉ።የ71 ዓመቱ ፕሬዝደንት የዛሬ 72 ዓመቱን ደገሙት።
                         
«ሰሜን ኮሪያ በዩናይትድ ስቴትስ ላይ መዛትዋን ማቆም አለባት።ዓለም ከዚሕ ቀደም አይቶት የማያዉቀዉ እሳትና እቶን ይወርድባቸዋል።»
 ሰሜን ኮሪያ ትንሽ ሐገር ናት።ከብዙዉ ዓለም የተነጠለች-ዝግ፤ በማዕቀብ የደከመች፤ በሐብታም ጠላቶችዋ የተከበበች-ደኃ ናት።ግን ግሪናዳ፤ ኢራቅ ወይም ሊቢያ አይደለችም።የድሮዋ ጃፓንም አይደለችም። እሷም ጋ ገመገም ዞሮ-የሚያነድ፤ ተመዘግዝጎ የሚያነፍር እሳት አለ።ፕሮፓጋንዳዉ ደግሞ ሞልቶ ይፈሳል።
                                 
«ከዚሕ በፊት እንደተገለጠዉ የኮሪያ ሕዝባዊ  ሥልታዊ ጦር ጉአምን በአንድ ጊዜ በተለያዩ  አቅጣጫዉዎች ለመምታት የሚያስችለዉን ሥልት  እየከለሰ ነዉ።የጠላትን ጦር የማጥቃት አቅም በመስበር ለዩናይትድ ስቴትስ ጥብቅ ማስጠንቀቂያ ለመስጠት፤ጉአም የሚገኘዉን ዋና ዋና የጦር ሠፈር  በአራት ሕዋሶንግ 12 የመካከለኛ ርቀት ተምዘግዛጊ ሚሳዬል ለመምታት ታቅዷል።»
ጉአም የዩናይትድ ስቴትስ ያየርና የባሕር ጦር ሠፈር የሚገኝባት ሰላማዊ ዉቅያኖስ ላይ የምትገኝ ደሴት ነች።ከሰሜን ኮሪያ 3000 ኪሎ ሜትር ትርቃለች።ሰሜን ኮሪያ ደቡብ ኮሪያን፤ ጃፓንን ወይም ዩናይትድ ስቴትስን ለመምታት ስትዝት ያሁኑ የመጀመሪያዋ አይደለም።የመጀመሪያ የሆነዉ የአሜሪካ የጦር ሠፈረን የሚመታዉ ሚሳዬል በጃፓን ባሕርና ከተሞች አናት ላይ እያፏጨ ጉአምን እንደሚያረባይ በዝርዝር ማስታወቅዋ ነዉ።ሥልቱን ገቢር ለማድረግ የዋና መሪዉ ትዕዛዝ ብቻ የሚጠበቅ መሆኑን መናገርዋ ነዉ።

Südkorea TV zeigt die Distanz von Nordkorea zu Guam bei einem möglichen Rakteneinsatz
ምስል Getty Images/AFP/J. Yeon-Je
Nordkorea - Angeblicher Test einer Interkontinentalrakete
ምስል Picture alliance/dpa/Uncredited/KRT/AP

የቃላት ጦርነቱ የኑክሌር-ሚሳዬሉን ዉጊያ እንዳያስከትል የሠጉት ጃፓንና ደቡብ ኮሪያ የሚፈሩት እንዳይደርስ እየተማፀኑ ነዉ።ቻይኖች፤ ሌሎቹ የእስያ ሐገራትና ምዕራብ አዉሮጶች ዛቻ ፉከራ፤የጦር ነጋሪት ጉሰማዉ በዲፕሎማሲ እንዲቀየር እየመከሩ ነዉ።የጀርመኑ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ሲግማር ጋብርኤል ግን የአሜሪካዊዉን መሪ ሥሕተት ከመጠቆም አልቦዘኑም።
                                          
«እንደሚመስለኝ ጀርመንም ሆነ መላዉ አዉሮጳዊ የሰሜን ኮሪያ የኑክሌር መርሐ-ግብር ያሰገዋል።ትናንት ከአሜሪካዊዉ ፕሬዝደንት የሰማነዉ በርግጥ እስደንጋጭ ነዉ።በዴሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጡ አሜሪካዊ ፕሬዝደንት፤ ከዚሕ ቀደም ከሰሜን ኮሪያ የምነሰማዉ አይነት ተመሳሳይ መልስ መስጠታቸዉ፤ እንዲሕ አይነት ዛቻ፤ ቃላት እና ለጥቃት የተዘጋጀ የሚያስመስል ቋንቋ መጠቀማቸዉ እኔን ራሴን በጣም አሳስቦኛል።»
ትራምፕ ከሐገራቸዉም ከዉጪም የሚሰነዘረዉን ትችት፤ ተቃዉሞና ምክር ያደመጡ አይመስሉም።የሰሜን ኮሪያ አፀፋ ከተሰማ በኋላ ትንናት ዛቻቸዉን የዩናይትድ ስቴትስ የኑክሌር ቦምቦች ከመቼዉም ጊዜ በላይ ለጥቃት ዝግጁ ናቸዉ ብለዉ ደገሙት።

Donald Trump
ምስል Picture-Alliance/AP Photo/E. Vucci

ነጋሽ መሐመድ

ኂሩት መለሰ