1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ፅዱ ሥነ-ቴክኒክ እና በአዳጊ አገሮች የመሥፋፋት ዕድሉ

ረቡዕ፣ ጥቅምት 11 2002

ሳይንስና ሥነ ቴክኒክ ፣ ለኤኮኖሚ ዕድገት መሠረትነቱ እሙን ነው። ያም ሆኖ፣ በኢንዱስትሪ የገሠገሡት አገሮች በተራመዱባቸው እርከኞች ምን ላይ እንከኖችእንዳጋጠሙ ለመገንዘብና እርማት ለማድረግ

https://p.dw.com/p/KCIQ
ታዳሽ የኃይል ምንጭ(ከፀሐይ ብርሃንና ሙቀት የኤሌክትሪክ ኃይል ማጠራቀሚያ ልዩ መስታውቶች)ምስል AP
አዳጊ አገሮች ምቹ አማራጭ እንዳላቸው የታወቀ ነው። በዛ ያሉ አገሮች፣ በመገናኛው ዘርፍ በቀጥታ ወደ «ዲጂታል» ረድፍ በመዛወር ላይ ሲሆኑ፣ የ 21 ኛው ከፍለ-ዘመን ፣ አዲሱ የኃይል ምንጭ ነኩ ኤኮኖሚም ቢሆን ፣ ለብዙዎቹ አዳጊ አገሮች አዲስ ሥነ-ቴክኒክ አጠቃቀም የሚያበረታታ መሆኑ አልቀረም። የኃይል ምንጭ ለኤኮኖሚ ዕድገት ወሳኝ ድርሻ የሚያበረክት ቢሆንም፣ የተፈጥሮ አካባቢ በካዮች ከሆኑ የደንጋይ ከሰልና ነዳጅ ዘይት ውጭ በሌሎች አማራጭ የኃይል ምንጮች መጠቀም የሚለው ዘይቤ፣ ከኅዳር 28 -ታኅሳስ 9 ቀን 2002 ዓ ም በኮፐንሄገን በሚካሄደው ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ጉዳይ የአህጉር መሪዎች ጉባዔ ላይ ዐቢይ ትርጉም ሳይሰጠው እንደማይቀር ነው የሚታሰበው። በባንግኮክ ፣ ታይላንድ ተካሂዶ በነበረው የአየር ንብረት አያያዝ ቅድመ-ድርድር ነክ ስብሰባ ላይ ተገኝተው የነበሩት የ «ግሪን ፒስ » ልዑካን መሪ ማርቲን ካይዘር እንዲህ ብለው ነበር።

«የታዳሽ የኅይል ምንጮችን ቅድሚያ ለማስያዝ ዘመቻው ከተጀመረ ቆይቷል። ጀርመን፣ በዚህ ሥነ-ቴክኒክ ረገድ ግንባር ቀደም ሚና መያዝ የያዘች አገር ናት፣ ዩናይትድ እስቴትስ፣ ችላ ብላው የነበርውን ይህንኑ ዘርፍ በአፋጣኝ ተመልሳበታለች። ቻይናን የመሳሰሉ አገሮች ደግሞ አዲሱን የይል ምንጭ ሥነ ቴክኒክ ለመጀመርና ለማስፋፋት፣ በሰፊው ጓጉተው ነው የተነሣሱት። በንግድ ረገድም ዐቢይ ድርሻ ያለው ነው።»

ጠበብት እንደሚሉት ከሆነ፣ በመገናኛ ረገድ የታየው የሥነ-ቴክኒክ እመርታ፣ በታዳሽ የኃይል ምንጭ ረገድም ተመሳሳይ ውጤት በማስገኘት ፣ የወደፊቱን ዓለም አቀፍ የምጣኔ ሀብት ዕድገት፣ አረንጓዴ ኤኮኖሚ ይሆናል የሚያሰኘው። ለአስተማማኝ ታዳሽ የኃይል ምንጭ ሲታገሉ የኖሩት የዓለም አቀፉ ታዳሽ ኃይል ምንጭ ድርጅት ተባባሪ ቅሥቀሳ ጀማሪ ሄርማን ሺር፣ በበኩላቸው ሥነ ቴክኒክን፣ መገናኛንና የኢንዱስትሪ አያያዝን አስመልክተው ሲናገሪሩ--

«ቀጣዩ ዐቢይ ሥነ ቴክኒካዊ የኢንዱስትሪ አብዮት፣ ወደፊት፣ ከመገናኛ ሥነ-ቴክኒካዊ አብዮት የላቀ ትርጓሜ የሚያገኝ ነው የሚሆነው። ይህ ደግሞ፣ የኢንዱስትሪውን ማኅበረሰባዊ እርምጃ የሚያጠናክር ሊሆን ይችላል። በቆየውና በተለመደው የኃይል ምንጭ ወደፊት መራመድ አይቻልም። ምክንያቱም፣ የኃይሉ ምንጭ ስለሚሟጠጥ ብቻ ሳይሆን፣ የሚያስከትለው ጥፋት ፣ በኤኮኖሚም ረገድ፣ መጠን የለሽ ስለሚሆን ነው።»

በተንቀሳቃሽ የስልክ አገልግሎት እንደታየው ግሥጋሤ፣ የወደፊቱ ኤኮኖሚም በዚያው መሥመር ሊያድግ እንደሚችል የሚያስቡት ፣ ዋና ጽ/ቤቱ፣ በናይሮቢ ኬንያ የሚገኘው፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ፣ የአካባቢ ጥበቃ መርኀ-ግብር ሥራ አስኪያጅ፣ አኺም እሽታይነር፣ ለዚህ እንደ ምሳሌ ያቀረቧት አገር ኬንያ ሆናለች። በኬንያ ዘመናዊው መድበለ-መልእክት ማሠራጫው ከመስታውትና ፕላስቲክ የሚሠራው እጅግ ዘመናዊው ሽቦ ተዘርግቷል። በኅይል ምንጭ ረገድም፣ ብዙዎች አዳጊ አገሮች የወደፊቱን የዕደገት ጎዳና ተያይዘውታል። ኬንያ ባለፉት 2 ዓመታት ፣ በከርሠ-ምድር የሚገኘውን የተፈጥሮ የአንፋሎት ኃይል 3 እጥፍ ጠቀሜታ እንዲሰጥ አድርጋለች። የነፋስ ኃይልም ሥራ ላይ እንዲውል ይፈለጋል። አኺም እሽታይነር---

«ባለፈው ዓመት በጥር ወር ይፋ በሆነው የኤልክትሪክ ማመንጪያና አጠቃቀም ደንብ፣ አመንጪዎች የሚከፍሉት ቀረጥ መጠን የተገለጠ ሲሆን፣ በሚመጡት 3 እና 4 ዓመታት በኬንያ በነፋስ ኃይል የሚሠሩ እጅግ ትልልቅ ኤልክትሪክ አመንጪ አውታሮች በቱርካና መተከላቸው አይቀርም። በ 10 ዓመታት ውስጥ፣ ኬንያ አጠቃላዩ የኃይል ምንጭዋ፣ የተቃጠለ አየር የሌለበት ታዳሽ የኃይል ምንጭ ይሆናል፣ ይህም፣ ከፀሐይ ሙቀትና ብርሃን የሚገኘውን የኃይል ምንጭ ጨምሮ ማለት ነው። እርግጥ ነው፣ ይህን ሥነ-ቴክኒክ ለማስፋፋት ፣ ገንዘብን ፣ በሰፊው ሥራ ላይ ማዋል ያስፈልጋል።»

በዛሬው ዕለት ከህንድ ጋር ኒው ደልሂ ውስጥ፣ የአየር ንብረትን ለመጠበቅ ሰፊ ውል የፈረመችው ቻይና፣ በኮፐንሃግኑ ጉባዔም ከህንድ ጋር የጋራ አቋም ይዛ እንደምትቀርብ ነው ያስታወቀች ። በነፋስና በፀሐይ ኃይል በሚሠሩ ታዳሽ የኃይል ምንጮች ሥነ ቴክኒክ ረገድ ግሥጋሤ ያሳየችው ቻይና ፣ በዚህ ረገድ የምታቀርበውን ምርት በመለስተኛ ዋጋ ማሰራቸት ነው የምትሻው። የተፈጥሮ አካባቢ ተንከባካቢና የልማት ድርጅት ሥራ- መሪ ዩዑርገን ማየር፣ ---

«የፀሃይን ኃይል በመሳብ ኤልክትሪክ የሚያከማቹ ልዩ መስታውቶችን በመሥራትና በዓለም ገበያ ላይ በማዋል፣ ቀዳሚውን ቦታ የያዘችው ቻይና ፣ በህንጻዎች የፈላ ውሃ፣ ከፀሐይ ኅይል እንዲገኝ በማድረግ ቻይና ቀደሚውን ቦታ ይዛለች። በነፋስ ኃይል አጠቃቀም በዓለም ውስጥ ቀዳሚውን ቦታ ለመያዝም፣ ጠንከር ያለ ዓላማ ይዛ ተነሣስታለች። ቻይናውያን የራሳቸው አምራች ድርጅት ስላላቸው ከውጭ አያስገቡም። አንዳንድ አውሮፓውያን በነፋስ ኃይል ኤሌክትሪክ አመንጪ የሆኑ ኩባንያዎች፣ የቻይና በዘህ ረገድ በውጭ ገበያ የምታደርገው ተሳትፎ አስፈርቷቸዋል። ቻይና ድምጿን አጥፍታ ኤሌክትሪክ አመንጪ መስታውቶችን ለውጭ ገበያ ማቅረቡን ተያይዛዋለች። ይህን የምታደርገው፣ ለጊዜው በዚያው በቻይና በሰፊው ተፈላጊ ባለመሆኑ ነው፣ ነገር ግን እንደሚመስለኝ እዚያም ቢሆን ሁኔታዎች መለወጣቸው አይቀሬ ነው።»

የወደፊቱ ዓለም አቀፍ ገበያ ትኩረት ከታዳሽ የኃይል ምንጭ ጋር የተያያዘ በመሆኑ፣ የትኞቹ አዳጊ አገሮች፣ በአዲሱ ሥነ ቴክኒክ መጠቀም የሚቻልበትን ዕድል እንደሚያተኩሩበት፣ በኢንዱስትሪ ከበለጸጉት አገሮችም የትኞቹ ቶሎ ብለው የተፈጥሮ አካባቢን ከሚበክሉ የኃይል ምንጮች እንደሚገላገሉ ወደፊት የሚታይ ይሆናል።

ተክሌ የኋላ፣

ሸዋዬ ለገሠ፣