1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ቱኒዚያ እና ሞሮኮ

ማክሰኞ፣ ነሐሴ 23 2009

ቱኒዚያ ራሱን እስላማዊ መንግሥት ብሎ የሚጠራውን እና ሌሎች አክራሪ ቡድኖችን የሚቀላቀሉ ዜጎችዋ ቁጥር ብዙ ነው። ሞሮኮም ከጥቂት ሳምንታት በፊት በባርሴሎና፣የደረሰውን የሽብር ጥቃት እንደምሳሌ ብንወስድ ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር ከዋሉት መካከል አብዛኞቹ ዝርያቸው ከሞሮኮ ነው። በማግሬብ ሀገራት ከእምነት ጋር የተያያዘ ፅንፈኝነት ለምን ተስፋፋ? 

https://p.dw.com/p/2j1JL
Tunesien Prozess von Angriff in Sousse
ምስል picture-alliance/AP Photo/H. Dridi

ቱኒዚያ ዴሞክራሲያዊውን ስርዓት በመትከሉ ሂደት ላይ ትገኛለች። ያም ሆኖም ግን ከህዝቧ ብዛት ጋር ሲነፃጸር ራሱን እስላማዊ መንግሥት ብሎ የሚጠራውን እና ሌሎች አክራሪ ቡድኖችን የሚቀላቀሉ ዜጎችዋ ቁጥር ብዙ ነው። ካለፉት ስድስት ዓመታት ወዲህ አንዳችም የሽብር ጥቃት ባልተካሄደባት ሞሮኮም ሰላም ሰፍኗል፣ ግን፣ ከጥቂት ሳምንታት በፊት በባርሴሎና፣ ስጳኝ የደረሰውን የሽብር ጥቃት እንደምሳሌ ብንወስድ ጥቃቱን ፈጽመዋል በሚል ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር ከዋሉት መካከል አብዛኞቹ ዝርያቸው ከሞሮኮ ነው። 
ሪድሀ ራዳዊ ጠበቃ ናቸው። በቱኒዝያ በሽብርተኝነት የተጠረጠሩ የ1000 ገደማ ሰዎችን ክሶች መርምረዋል። ጠበቃው በምርምራቸው መጨረሻ የተረዱት አንድ ነገር አለ። ይኸውም፤« ከተከሳሾቹ መካከል ከሶስት አራተኛ የሚበልጡት ከ 34 ዓመት በታች ናቸው።  የአምባገነናዊው ስርዓት ጠንካራ ግፊት ያላረፈበት፣ በንፅፅርም ጥሩ የትምህርት እድል ያገኘ ትውልድ ነው። 40 ከመቶ የሚሆኑት የዩኒቨርሲቲ ትምህርት ተከታትለዋል። »
ራዳዊ ከመረመሯቸው በሽብርተኝነት የተጠረጠሩት ተከሳሾች ሰነድ መካከል ወደ 70 ከመቶ የሚሆኑት  በውጭ ሀገራት የሽብርተኞች ማሰልጠኛ ጣቢያዎች የሰለጠኑ ጥሩ የትምህርት ደረጃ ያላቸው ወጣቶች ናቸው። ግማሾቹም የፅንፈኝነትን መስመር የያዙት ሀይማኖት ነክ ጽሁፎችን አንብበው ሲሆን፣ ሌሎቹ የተሰማሩበትን ትናንሽ የወንጀል ተግባር ትተው አክራሪ ቡድኖችን የተቀላቀሉ ናቸው። ሁሉም ሽብርተኝነትን የሚረዱበት መንገድ ግን ይለያያል። ለዚህም የተለያየ ምክንያት እና መነሻ አላቸው። እንደ ጠበቃ ራዳዊ እና ባልደረቦቻቸው ጥናት ውጤት እንዳሳየው፣ የቱኒዝያ ወህኒ ቤቶች አክራሪነት በይበልጥ የሚስፋፋበት ስፍራ ነው። ጠበቃ ራዳዊ በቱኒዚያ አብዮት ከተካሄደ ስድስት አመታት በኋላም የሀገሪቱ መንግሥት አክራሪነትን መታገል የሚቻልበትን መንገድ ባለማግኘታቸው አብዝተው ይተቻሉ።
ሞሮኮ ውስጥ በሰባኪነት ይታወቁ የነበሩት አቦ ሀፍስን የመሳሰሉ የቀድሞ ፅንፈኛ ወጣት ለዚህ ችግር መፍትሔ በማፈላለጉ ተግባር ላይ ሊረዱ እንደሚችሉ ይገመታል። አቦ ሀፍስ ዘጠኝ አመታት በወህኒ ቤት ካሳለፈ በኋላ፣ አሁን በቀድሞ ትክክለኛ ስሙ፣ መሀመድ ራፊቅ መጠራት ጀምሯል። በወቅቱ የፅንፈኝነትን መንገድ መከተል የመረጠው አባቱ እና ጓደኞቹ ሁሉ አክራሪ አማኞች ስለነበሩ ነው ይላል። ወጣቱ መሀመድ ስልጠናውን እና የቁራን ትምህርቱን የተከታተለው በሳውዲ አረቢያ ነው። « እስልምና አንድ ትርጓሜ ብቻ እንዳለው ነው የተማርኩት።  የተለያዩ ትርጓሜዎች እንዳሉት አስተማሪያ አልነገረኝም። ይህን ቆየት ብሎ ነው የተማርኩት እና ይህ ለኔ በጣም አስደንጋጭ ነበር።»
ይህንን እስኪገነዘብ ድረስም መሀመድ በሳውዲ የተማረውን ነበር ሞሮኮም ውስጥ ይሰብክ የነበረው። መስከረም አንድ፣2001 ዓም በዩናይትድ ስቴትስ ላይ የተጣለውን የሽብር ጥቃትም አማኖች ባልሆኑ ላይ የተፈፀመ ትክክለኛ ቅጣት ነበር ሲሊ በወቅቱ ካወደሱት ተርታም ተሰልፏል። 
እኢአ በ 2015 ዓም ሞሮኮ ውስጥ ጠበቆች  በምህፃሩ BCIJ  የተባለው ፀረ ሽብር ማዕከል አቋቁመዋል።  የማዕከሉ ኃላፊ አብደልሀቅ ቃሂም እንደሚሉት ማዕከሉ ከተቋቋመ አንስቶ 46 የሽብር ህዋሳትን ሞሮኮ ውስጥ ማጥፋት ችሏል። ኃላፊው ሌላም ቁጥር ተናግረዋል። 1664። ይህን ያህል ሞሮኳውን የተለያዩ የፅንፈኛ ቡድኖችን ተቀላቅለዋል። አብዛኞቹም ራሱን እስላማዊ መንግሥት ሲል የሚጠራውን ቡድን ነው የተቀላቀሉት። « የአክራሪነት መንስኤዎችን መታገል ያስፈልጋል። ለዚህ ደግሞ ቤተሰብ፣ ትምህርት ቤት እና የሲቪክ ማህበረሰብ ፣ማንኛቸውም ቢሆኑ ትልቅ ሚና መጫወት ይገባቸዋል። ምክንያቱም ኃላፊነቱ የጋራ ነው።»
ይላሉ የጠበቆቹ ማዕከል ኃላፊ ቃሂም። ለምን ግን ሰዎች አክራሪ ይሆናሉ? የቱኒዚያው ጥናት እንደሚያመለክተው የተለያዩ ምክንያቶች አሉ። እነዚህ ምክንያቶች በሞሮኮም እንደሚታዩ መገመቱ አያዳግትም። ዘጠኝ ዓመት ወህኒ ቤት የቆየው የቀድሞ ፅንፈኛ ሰባኪ መሀመድ ሌሎች አክራሪ የሚሆኑበትን ምክንያት ሊረዳው ይችል ይሆናል፣ ያለፈበት ስለሆነ። የሚጓዙትንም መንገድ ያውቃል። ስለሆነም አሁን ወጣቶቹን ከፅንፈኝነትና አክራሪነት ለማራቅ እንደቻለ ይናገራል።  

Jugendliche bei der Demonstration der Ennahdha Partei in Tunis
ቱኒዚያ እና ሞሮኮ የሽንር ቡድናትን የሚቀላቀሉ ጨምረዋልምስል DW/T. Guizani
Symbolbild Marokkanische Polizei
የሞሮኮ ፖሊስምስል picture-alliance/dpa/dpaweb/P. G. Guerrero
Tunesien Polizei am Strand
በሽብር ጥቃት ስጋት አገር ጎብኚዎች ቀንሰዋል።ምስል picture-alliance/dpa/M. Messara


የንስ ቦርቸርስ /ልደት አበበ 
አርያም ተክሌ