1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ጥበቃ የሚሹት የዱር እንስሳት

ማክሰኞ፣ የካቲት 18 2006

በአንድ ወቅት ምድር ላይ ይኖሩ የነበሩ እንስሳት አሁን ዘራቸዉ በመጥፋቱ በምስል ብቻ ከበርካታ ሚሊዮን ዓመታት በፊት እንደነበሩ ከመግለጽ የዘለለ አሻራ አጥተዋል። ዛሬስ ቁጥራቸዉ እየተመናመነ የሄደዉ የዱር እንስሳት የወደፊት እጣ ምን ይሆን?

https://p.dw.com/p/1BFFH
ምስል ALEXANDER JOE/AFP/Getty Images

አፍሪቃ ዉስጥ የሚገኙ የዝሆኖች ቁጥት ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በየጊዜዉ እየቀነሰ መሄዱን የዘርፉ ባለሙያዎች በምሳሌነት የኬንያና ታንዛንያን ይዞታ እያሳዩ ይጠቅሳሉ። ከዓመታት በፊት በኬንያዉ ሳቮ ብሄራዊ ፓርክ 35,000 ዝሆኖች ነበሩ፤ ዛሬ ግን 12,000 ብቻ መቅረታቸዉ ነዉ የሚገለፀዉ። በታንዛኒያ ሴሉስ ብሄራዊ ፓርክም እንዲሁ ከዛሬ 40 ዓመታት በፊት 109 ሺህ ዝሆኖች እንደነበሩ ነዉ የሚታመነዉ። ባለፈዉ የጎርጎሪዮሳዊ ዓመት በጀርመን መንግስት ድጋፍ በተካሄደዉ ቆጠራ ግን 13 ሺህ 84 ብቻ ነዉ የተገኙት። ከፍራንክፈርቱ የዱር እንስሳት አጥኚ ቡድን ክሪስቶፍ ሼንክ ስለቆጠራዉ ሲያስረዱ፤

Symbolbild Wilderei in Simbabwe
ምስል Desmond Kwande/AFP/Getty Images

«በርካታ አዉሮፕላኖች በየቀኑ በርከት ያሉ በረራዎችን እንዲያደርጉ ተሰማርተዉ ነበር። በአንድ አካባቢ 80 ሺ ኪሎ ሜትር ያህል በረራ በማድረግም ዝሆኖቹን በመቁጠርና በተወሳሰበዉ ቴክኒክ አማካኝነት የተገኘዉን አጠቃላይ መረጃም በመተንተን በቀጣይ ለሚደረገዉ ቁጥጥርም ከአየር ፎቶግራፎች አንስተናል።»

እንስሳቱን የሚገኙበትን የአሁኑን ይዞታ አጥኚዎቹ ይመልከቱ እንጂ ምን ያህሉ በሕገ ወጥ አዳኞች እንደተገደሉ አልተገለጸም። ዝሆኖቹ የሚታደኑት በሕገ ወጡ ገበያ ከወርቅ በላይ ዋጋ ለሚያወጣዉ ጥርሳቸዉ ሲባል ነዉ። ባለፈዉ ዓመት ብቻ በሕገወጥ መንገድ ከታደኑ ዝሆኖች የተሰበሰበ 40 ቶን የዝሆን ጥርስ መያዙ ተሰምቷል። ዩናይትድ ስቴትስ በዚህ መንገድ ከገባዉ የዝሆን ጥርስ 6 ቶን ያህሉን ዴንቨር ላይ እንዳልነበረ ስታደቅቅ፤ የቻይና ፖሊስም እንዲሁ 6 ቶን ያህል ባለፈዉ ወር መባቻ መያዙን እና እንዲወድም ማድረጉ ተዘግቧል። እንዲህ ያለዉን በሕገወጥ መንገድ የሚካሄድ ንግድና የዱር እንስሳቱንም በሕገወጥ የማደኑን ተግባር የማስቆሙ እንቅስቃሴ ዓለም ዓቀፍ ትኩረት አግኝቷል። ከሳምንታት በፊት ሎንደን ላይ በተካሄደዉ ሕገወጥ አደንን ለማስቆም ያለመ ጉባኤ ከ40 ሃገራት በላይ ተወካዮች ተሳትፈዋል። ተወያዮቹ የዱር እንስሳትን በሕገወጥ ማደኑ አደንዛዥ እፅን እንደማዘዋወር መታየት አለበት ባይ ናቸዉ።

Bildergalerie Wilderei
ምስል STRINGER/AFP/Getty Images

በጉባኤዉ ላይ እንደተገለፀዉም አፍሪቃ እና እስያ ዉስጥ በተለይ ዝሆኖች፤ እንዲሁም አዉራሪሶችና ነብሮች ለአደጋ ተጋልጠዋል። ባለሙያዎች እንደጠቆሙትምበየዓመቱ 25 ሺ ዝሆኖች ይገደላሉ። እስያ ዉስጥ ባለፉት አስር ዓመታት ዉስጥ የነብሮች ቁጥር ከመቶ ሺህ ወደ3 ሺ የወረደበት ሁኔታም ተገልጿል። ደቡብ አፍሪቃ ዉስጥ ብቻ ባለፈዉ ዓመት አንድ ሺህ አዉራሪሶች ተገድለዋል። በሕገወጥ መንገድ ከሚታደኑት ከዝሆን ጥርስ፤ ከአዉራሪስ ቀንድ እንዲሁም ከነብር አካላት ሽያጭ በየዓመቱ 19 ቢሊዮን ዶላር በላይ እንደሚገኝም ተጠቁሟል። ይህን ዘገባ ያደመጡት የጀርመን የአካባቢ ጥበቃ ሚኒስትር ባርብራ ሄንድሪክስ የዱር እንስሳቱን መታደግ ካልተቻለ ወደፊት ዘራቸዉ ጠፍቶ ስለእነሱ ሲነገር ለትዉልድ በስዕል ብቻ የምናሳይበት ወቅት እንዳይመጣ በማለት ለጉባኤዉ ስጋታቸዉን ገልጸዋል።

ደህንነታቸዉን ለማረጋገጥም እንስሳቱ በሕገ ወጥ መንገድ የሚታደኑባቸዉም ሃገራትም ሆኑ የእንስሳቱ አካል የሚነገድባቸዉ ሃገራት በጋራ መሥራት እንደሚኖርባቸዉ ነዉ የታመነዉ።

ኢትዮጵያ ዉስጥ የዱር እንስሳትንና የመኖሪያ አካባቢያቸዉን በሚመለከቱ ጉዳዮች ኃላፊነት ወስዶ የሚንቀሳቀሰዉ መሥሪያ ቤት በፌደራል ደረጃ የሚተዳደረዉ በኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ልማት እና ጥበቃ ባለስልጣን ነዉ። የባለስልጣን መሥሪያ ቤቱ የሕዝብ ግንኙነት ጊዜያዊ አስተባባሪ አቶ ታደሰ ማሞ ለዶቼ ቬለ እንደገለፁት፤ ይህ መሥሪያ ቤቱ 13 ፓርኮችን ማለትም 11 ብሔራዊ ፓርኮችና ሁለት የመጠለያ ቦታዎችን በኃላፊነት ያስተዳድራል። በክልሎች የሚተዳደሩ የተለያዩ ፓርኮችም በመኖራቸዉ ከእነሱጋ በትብብርም ጥናትም ሆነ ለኅብረተሰቡ ግንዛቤን የማስጨበጥን ሥራ ሁሉ ጨምሮ ለእንስሳቱ የሚደረጉ ጥንቃቄዎችን እንደሚያከናዉንም አብራርተዋል። በተለያዩ አካባቢዎች የሚከናወነዉ ሕገ ወጥ አደን በተለይ ትላልቅ የሚባሉትን የዱር እንስሳት ቁጥር እያመናመነ ለመጥፋት አደጋ እያጋለጠ መሆኑ ይታመናልና ኢትዮጵያ ዉስጥ ሁኔታዉ እንዴት እንደሆነ ጠይቀናቸዉ እንደሚከተለዉ አብራርተዋል።

Flashgalerie Tiger (Indien)
ምስል AP

በሎንደኑ ጉባኤ የተሳተፉት ቻድ፣ ጋቦን፤ ታንዛኒያ ኢትዮጵያ እና ቦትስዋና ዝሆንን ከሕገወጥ አደን ለመከላከል የተለየ ተግባራዊ እቅድ እንዳላቸዉ በጉባኤዉ ላይ ገልጸዋል። የዱር እንስሳትን ከሕገ ወጥ አደንና ንግድ ለመታደግ ሃገራት የገቡት ቃል እና የነደፉት እቅድ ምን ያህል ዉጤታማ እንደሆነ ከአንድ ዓመት በኋላ ቦትስዋና በምታዘጋጀዉ ተመሳሳይ ጉባኤ ይመዘናል።

ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ