1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ጥርጣሬ ያጀበዉ የላይቤሪያ ምርጫ ዉጤት

ረቡዕ፣ ኅዳር 7 1998

ባለፈዉ ሳምንት በላይቤሪያ በተካሄደዉ ፕሬዝደንታዊ ምርጫ አሸንፈዉ የአገሪቱ መሪ ሊሆኑ ነዉ በሚል የቀድሞዋ የገንዘብ ሚኒስትር ኤለን ጆንሰን ሲርሊፍ ስማቸዉ መነሳት በጀመረበት ወቅት ጥርጣሬ ተቀስቅሷል። ተፎካካሪያቸዉ ሆኖ የቀረበዉ ኮከብ የእግርኳስ ተጫዋች የነበረዉ ጆርጅ ዌህ ዉጤቱ የተጭበረበረ ተዓማኒነት የሌለዉ ነዉ ብሎታል። ደጋፊዎቹም የጎዳና ላይ ተቃዉሟቸዉን ባለፈዉ ዓርብ ጀምረዉ በገለፁበት ወቅት ከተባበሩት መንግስታት ሰላም አስከባሪዉ ቡድን

https://p.dw.com/p/E0jM

ጋር በመጋጨት ሶስት ሰዎች ክፉኛ መጎዳታቸዉ ተዘግቧል።

ፍትህ ከሌለ ሰላም የለም በማለት ነበር የምርጫ ዉጤቱ ተጭበርብሯል በማለት ለተቃዉሞ የወጡት የዌህ ደጋፊዎች በዩናይትድ ስቴትስ ኤምባሲ በር ላይ ያሰሙት መፈክር።
ከሰልፈኞቹ መካከል ዉጤቱ የማይታመን እንደሆነ የምትናገረዉ የ37ዓመቷ ሳራ ማኩኒ ምርጫ ማለት በጥቅም የሚፈልጉትን ደግፎ አሸንፏል ማለት አይደለም፣ እዉነተኛ ዲሞክራሲ ማስመሰል አይደለም የሚሉ ፅሁፎችን ይዘዉ መዉጣታቸዉን ለዘጋቢዎች ገልፃለች።
ሞኖሮቪያ በሚገኘዉ ኤምባሲ ፊት ለፊት የተቃዉሞ ሰልፉን ሲያካሂዱም ለዲፕሎማቶች ተጭበርብሯል ያሉት ምርጫ በገለልተኛና በማያዳላ ወገን እንዲመረመር የሚያሳስብ የፊርማ ስብስብ ሰጥተዋል።
በላይቤሪያ የተረጋጋ አስተዳደር ያመጣል የምትለዉን ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር ለማየት ተስፋ ያደረገችዉ ዩናይትድ ስቴትስ ተቃዉሞ ቢኖርም መንግስት ለጥርጣሬዉ ወዲያዉ ምላሽ በመስጠቱ ግጭት ስላልተፈጠረ ባለስልጣናቱ ልባቸዉ ተረጋግቷል።
የዉጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አዳም ኤርሊ ዋሽንግተን ዉስጥ ለጋዜጠኞች እንደገለፁት በዉጤቱ ሳቢያ ተቃዉሞዎች ቢታዩም ወደብጥብጥ ያላመራ፤ ስርዓት የተከተለና ግልፅ አሰራር በመታየቱ የሚያበረታታ ነዉ ብለዋል።
ዓለም ዓቀፍ ታዛቢዎቹና የአፍሪካ መሪዎች ደግሞ ምርጫዉ ነፃና ግልፅ ምርጫ ነበር የሚሉ ወገኖች ናቸዉ።
በምርጫዉ ሂደት በምርጫ ሳጥኖችና በምርጫ ካርዱ ላይ የተፈጸመ ግድፈት አለ የሚሉት ተቃዋሚዎች አቤቱታ የምርጫ ቦርዱንም ሆነ የመንግስት ባለስልጣናትን ጆሮ አግኝቷል።
በአግባቡ ምርመራ ተካሂዶ የድምፅ ቆጠራዉ ሳይጠናቀቅ የሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ ምሩቋ ኤለን ጆንሰን ሲርሊፍ አሸናፊነት መወራቱንና ደጋፊዎቻቸዉም ባልተራገጠ ዉጤት ፈንጠዝያ መጀመራቸዉን አስመልክተዉ የምርጫ ቦርዱ ሊቀመንበር ፍራንሲስ ጆንሰን ሞሪስ ማሳሰቢያ ሰጥተዋል።
ወይዘሮ ሲርሊፍ አሸንፌያለሁ በማለት የማወጅ መብት የላቸዉም ያሉት ሊቀመንበሯ ሞሪስ ይህን ማድረግ የሚችለዉ ብሄራዊ የምርጫ ኮሚሽን ብቻ መሆኑን በመግለጫቸዉ አረጋግጠዋል።
ሊቀመንበሯ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይም ጥርጣሬዉን ለማረጋገጥ ምርመራ እንደሚያካሂዱ በመግለፅ የዌህ ቡድን ተፈፅሟል ላላቸዉ መጭበርበሮች ተጨባጭ ማስረጃ ያቀርባል የሚል ተስፋ እንዳላቸዉ ነዉ የተናገሩት።
ይህንንም አገናዝበዉ የመጨረሻዉን የምርጫ ዉጤት በላይቤሪያ ህግ መሰረት የዛሬ ሳምንት እንደሚያሳዉቁ ይጠበቃል።
ለ14ዓመታት በእርስ በርስ ጦርነት በታመሰችዉ ላይቤሪያ የቀድሞዉ የኤሲ ሚላን ድንቅ ተጫዋች ጆርጅ ዌህ ለፕሬዝደንታዊ ምርጫዉ በእጩነት መቅረቡ በአገሪቱ አለን የሚሉትን ፖለቲከኞች ማስደነቅ ብቻ ሳይሆን አስደንግጧል።
ባለፈዉ ጥቅምት ወር በተካሄደዉ በመጀመሪያዉ ዙር ዉድድር 22 እጩ ተወዳዳሪዎችን መርቶ መከ1ሚሊዮን በላይ ከተገመተዉ ድምፅ ዉስጥ ዌህ 28.3በመቶ ሲያገኝ ሲርሊፍ 19.8በመቶ ነበር ያስመዘገቡት።
ይሄም ለደጋፊዎቹ የጥርጣሬና የተቃዉሟቸዉ መነሻ ሊሆን እንደቻለ ታዛቢዎች ገምተዋል ምንም እንኳን ምርጫዉ ነፃና ሚዛናዊ ነበር ቢሉም።
ከሶስት ዓመታት በፊት የተቋቋመዉ የአገሪቱ ጊዜያዊ አስተዳደር የበላይ የሆኑት ጊድ ብራያንት ለህዝቡ ባደረጉት ንግግር ከፍትህ ሚኒስቴር ፈቃድ ካልተሰጠዉ በቀር የጎዳና ላይ ተቃዉሞ መታገዱን አስታዉቀዋል።
ለዴሞክራሲያዉ ለዉጥ ኮንግረስ በምህፃሩ ሲዲሲ ፓርቲም የምርጫ ኮሚሽኑን እየከሰሰ ዉጤቱ ሳይጣራ የተቃዉሞ ሰልፍ መዉጣቱ በቋፍ የሚገኘዉን የአገሪቱን ሰላም የሚያናጋ በመሆኑ አግባብ አይደለም በማለት ኮንነዉታል።
ባንድ ወቅት የዓለም የእግርኳስ ፌዴሬሽን የዓመቱ ምርጥ ተጫዋች በማለት ያሞካሸዉ የጆርጅ ዌህ አድናቂና ደጋፊዎች በአብዛኛዉ ወጣቶችና በእርስ በርስ ጦርነቱ ጊዜ መሳሪያ አንግበዉ የተሰለፉ እንደነበሩ ይነገራል።
ፍትህ ከሌለ ሰላም የለም የሚሉት የምርጫ ዉጤቱ ተቃዋሚዎች ከብዙ መተላለቅና አስከፊ ጉዳት በኋላ በቅርብ ጊዜ ሰላም በተገኘባት ላይቤሪያ ሌላ ችግር እንዳይለኩሱ ተሰግቷል።
በተጨማሪም የፓርላማ መቀመጫ ያገኙት የሲዲሲ ፓርቲ አባላት ሲርሊፍ አሸንፈዋል የሚለዉ ዉጤት ሳይጣራ ወደምክር ቤት እንደማይገቡ እያስጠነቀቁ ነዉ።