1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ጠፈርተኛው በኅዋ ቆይታው

ረቡዕ፣ ሰኔ 22 2008

ጠፈርተኞችን ከዓለም አቀፉ የኅዋ ምርምር ማዕከል አሳፍራ የተመለሰችው መንኲራኲር ወደ ምድር ንፍቀ-ክበብ ከመግባቷ አስቀድሞ ለሦስት ተከፋፈላለች። ከክፋዮቹ አንዱ የጎጆ ጉበን ቅርጽ ያለው፥ ባለ ሦስት ማዕዘኑ ኩብ ሲቀር፥ ሌሎቹ እዛው ኅዋ ላይ ፈንድተው ብትንትናቸው ወጥቶ እንዲከስሙ ተደርገዋል።

https://p.dw.com/p/1JFuQ
Kasachstan Baikonur Kosmodrom Start Trägerrakete
ምስል picture-alliance/dpa/Roscosmos

ጠፈርተኛው በኅዋ ቆይታው

ባለ ሦስት ማዕዘኑ ኩብ ግን ሦስት ጠፈርተኞችን እውስጡ እንደጫነ በከፍተኛ ፍጥነት ኅዋውን እየሰነጠቀ ወደ ምድር ተመዝግዝጓል። «እኛን ጭኖ ቁልቁል የተምዘገዘገው ባለሦስት ማዕዘን ኩብ ከፍጥነቱ የተነሳ የፈጠረው ግለት 1600 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ደርሶ ነበር» ሲል እንግሊዛዊው ጠፈርተኛ ተናግሯል።

ጠፈርተኞችን ጭኖ ወደ ምድር ሲከንፍ የወረደው ባለሦስት ማዕዘን ኩብ (capsule) ምድር ላይ ሰኔ 11 ቀን፣ 2008 ዓም ያለ አንዳች እንከን ማረፍ ችሏል። ከጠፈርተኞቹ አንዱ የኾነው እንግሊዛዊው ቲም ፒክ ከጠፈር በተመለሰ በሦስተኛ ቀኑ የጀርመን የጠፈር ሣይንቲስቶች፣ የመከላከያ አባላት እና ጋዜጠኞች በተገኙበት ኮሎኝ ከተማ ውስጥ በሚገኘው የአውሮጳ የኅዋ ምርምር ማዕከል(ESA)ውስጥ ደማቅ አቀባበል ተደርጎለታል። እንግሊዛዊው ጠፈርተኛን ለጥያቄ እና መልስ ወደ መድረክ የጋበዙት የማዕከሉ ኃላፊ ዴቪድ ፓርከር ናቸው።

«ሁላችሁም እዚህ በመገኘታችሁ እጅግ በጣም ደስ የሚል ነው። ግን ደግሞ ልዩ የኾነ ሰው እዚህ ከመሀከላችን መገኘቱ የበለጠ አስደሳች ነው። ለ186 ቀናት በጠፈር የምርምር ማዕከል ውስጥ የሠራ እና እዛ የቆየ፤ ከአጠቃላይ ቆይታውም ለአምስት ሰአታት ያኽል ከጠፈር ምርምር መዓከሉ ውጪ የቆየ፤ ብዙዎቻችሁ ልታዩት የምትናፍቁት አንድ ሰው እመሀከላችን ይገኛል። ይኽ ሰው የብሪታንያው ጠፈርተኛ ቲም ፒክ ነው።»

ከምርምር ጣቢያው በቅርብ ርቀት ላይ የሚገኘው የጀርመን መከላከያ የዓየር ማረፊያ ውስጥ የአውሮጳ የኅዋ ምርምር ማዕከል እየገቡ በቀጥታ እንዲጠቀሙበት በመደረጉ ኃላፊው ምስጋና አቅርበዋል። እናም መድረኩን ለጥያቄ እና መልስ ለቀው ወረዱ።

ለመሆኑ የስበት ኃይል ዜሮ በሆነበት ጠፈር ላይ ለመንፈቅ ያኽል ቆይቶ ወደ ምድር መመለስ ምን አይነት ስሜት ይፈጥር ይኾን? የጠፈር ቆይታውስ እንዴት ነበር? እንግሊዛዊው ጠፈርተኛ ለእነዚህ እና ለሌሎች ጥያቄዎች ማብራሪያ ሰጥቷል።

«ባለፈው ቅዳሜ ምሳ ሰአት ላይ ከተሰማኝ ስሜት የተሻለ ነው አኹን በእርግጠኛነት የሚሰማኝ። ከምንም በላይ ግን የሚደንቀው የሰው ልጅ አካል ምን ያኽል በፍጥነት ከአዲስ አካባቢ ጋር መላመድ መቻሉ ነው። እንዲህ አይነት ስሜት ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ኅዋ ስመጥቅ ተሰምቶኛል። እናም የኅዋ ምርምር ማዕከሉ ላይ ካረፍን ከ24 ሰአታት በኋላ ሰውነታችን ምን ያኽል በፍጥነት አካባቢውን መልመዱ አስደንቆኛል። ግን ከኅዋ ወደ ምድር ስትመለስ ትንሽ ለየት ያለ እና አስቸጋሪ ነገር ነው። መላመዱ ዝግ ይላል። ቢሆንም ከሦስት ቀናት በኋላ ሰውነትን መልሶ ከአካባቢ ጋር የማላመድ ድጋፍ ከባልደረቦቼ ጋር ከተሰጠኝ በኋላ ደህና ነኝ። የሰውነትን ሚዛን የመጠበቅ ስልጠና ካገኘሁ ከሦስት ቀናት በኋላ ዛሬ ድንቅ ስሜት ነው የሚሰማኝ።»

በእርግጥም ኅዋ ውስጥ በዜሮ ስበት ለስድስት ወራት ቆይታ አድርጎ ለመጣ ሰው ከምድር የስበት ኃይል ጋር ለመላመድ የሚኖረው ትግል በቀላሉ የሚገለጥ አይደለም። የአውሮጳ የኅዋ ምርምር ማዕከል ኃላፊም ተመሳሳይ ነገር ነው የተናገሩት። አሠሣ እና ቅኝት ያለ ሣይንሳዊ ምርምር ከቱሪዝም ወይም ከጉብኝት አይለይም ብለዋል።

በዓለም አቀፍ የኅዋ ምርምር ጣቢያው የሚከናወነው ምርምር ለሰው ልጆች ኑሮ የወደፊት አጋዥ ነገሮችን ለማምረት፣ የኃይል ምንጭን ዘላቂ ለማድረግ ብሎም ሮቦትችን በተሳካ መልኩ ለማጎልበት እመርታ የታየበት የስነ-ቴክኒክ ዘርፍ መሆኑን ኃላፊው ገልጠዋል። ጠፈርተኛው ቲም ፒክ በበኩሉ በኅዋ የስድስት ወር ቆይታቸው ወቅት ከ250 በላይ ምርምሮችን ማከናወናቸውን አስታውቋል።

«እንደ ጠፈርተኛ በዓለም አቀፉ የኅዋ የምርምር ማዕከል ለሥራ እና ለኑሮ ቆይታ ማድረግ ከምንም በላይ የምተመኘው ነገር ነው። እዛ ስትቆይ በየአቅጣጫው ድጋፍ ይደረግልሃል፤ ምርምር የምታደርግባቸው መሣሪያዎች እጅግ ዘመናዊ የስነ-ቴክኒክ ውጤቶች ናቸው። በአንድ ቀን ውስጥ ከስድስት ወይንም ከሰባት የተለያዩ የምርምር እና ጥናቶች ጋር ግንኙነት ይኖርህ ይኾናል። እነዚህ ምርምሮችም በሺህዎች እንኳን ባይሆኑ በመቶዎች የሚቆጠሩ በተለያዩ መስኮች የተካኑ ጠበብቶች የተጨነቁበት የምርምር ውጤት መኾኑን ታውቃለህ። እናም ይኽን ምርምር በኃላፊነት የምታከናውነው አንተ ነህ። ስለዚህ እጅግ መታደል ነው እዚያ መሥራት። በምትሠራው ነገር ሁሉም ትረካለህ። ስለዚህ ዳግም ወደዚያ መምጠቅ እፈልጋለሁ።»

የኅዋ ላይ ምርምሩ በእርግጥም በሳይንሱ ዓለም ለሚገኙ ተመራማሪዎች እጅግ አጓጊ በኾነ መልኩ እየተስፋፋ ነው። ጠፈርተኛው ቲም እና ባልደረቦቹ አሁን ከሚያከናውኗቸው ጥናት እና ምርምሮች መካከል ከፊሉ ማርስ ላይ ወደፊት ለሚደረገው ምርምር በር ከፋች ነው ተብሏል።

ማርስ ላይ ለማረፍ በጉዞ ላይ የምትገኘው ኤክሶ ማርስ የተሰኘችው መንኲራኲር ከአምስት ወራት በኋላ ጥቅምት ወር ላይ የጉዞዋን ገሚሱን አጠናቃ በማርስ ንፍቀ ክበብ ውስጥ በመሽከርከር የማርስ አካል ላይ ታርፋለች። እናም በሰው ልጆች ስልጣኔ የተቀናጀ የሮቦት እገዛ የታከበለበት ከርሰ-ማርስ ቡርቦራ የሚያከናውነው ኤክሶማርስ ሮቦት እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2020 ሥራውን ይጀምራል ተብሎ ይጠበቃል።

ያኔ የሰው ልጅ በኅዋ ምርምሩ አንዳች ምዕራፍ ከፈተ ማለት ነው። የጠፈር ምርምሩ ወደ ማርስ ትኩረት ማድረጉ ስለማይቀርም ከዐሥር ዓመት በኋላ ዓለም አቀፉ የኃዋ ምርምር ማዕከል የ25 ዓመታት አገልግሎቱ አብቅቶ እንደሚዘጋም ተጠቅሷል። ከዚያ በፊት ግን በርካታ ምርምሮች እንደሚከናወኑ የአውሮጳ የኅዋ ምርምር ማዕከል ኃላፊ አስታውቀዋል።

«እስኪ አስቡት በ2018 ናሳ የመጀመሪያው በኾነው የመንኲራኲር ማምጠቂያው መንኲራኲር ሲያመጥቅ ዓለም በመላ ይመለከታል። አፖሎን ካየንበት ጊዜ አንስቶ ዐይተነው የማናቀው አይነት እጅግ ግዙፍ መንክራኲር ያመጥቃል። በመንኲራኲር ፈጠራ ታሪክ የመጀመሪያው የሆነው ይኽ መንኲራኲር ይመጥቃል። እናም ሁለተኛው ክፍል መንኲራክር ጠፈርተኞችን ጭኖ ይወነጨፍ እና በጨረቃ ዙሪያ ተሽከርክሮ ወደ ምድር ይመለሳል። ጎን ለጎንም ጠፈርተኞች ለኅዋ ሣይንሱ ወሳኝ በሆነው የኅዋ ምርምር ማዕከሉ ምርምር ማድረጋቸውን ይቀጥላሉ።»

ወደፊት በጨረቃ እና በመሬት የስበት ኃይል አማካይ በኾነ ቦታ ላይ አዲስ የኅዋ የምርምር ማዕከል እንደሚዘረጋ የአውሮጳ የኅዋ ምርምር ማዕከል ኃላፊ ይፋ አድርገዋል። መንኲራኲሮች በጥልቁ ኅዋ ላይ እየተመላለሱም ወደፊት ወደ ሚቋቋመው የኅዋ ላይ ማዕከል ናሙናዎችን ያመላልሳሉ። ምናልባት ጥላማ በሆኑ የጨረቃ ዋልታዎች ላይ እንደ በረዶ ቀዝቅዞ የሚገኘው ውኃ ወደፊት ለጠፈርተኞቹ ጥቅም ላይ ይውል ይኾናል ተብሏል። ጥቅም ላይ የመዋሉ ጉዳይም በስነ-ከዋክበት ጠበብት እና የከርሰ ምድር ተመራማሪዎች ጥልቅ ፍተሻ ከተከናወ በኋላ ነው።

ወደፊት ከአራት ዓመት በኋላ ማርስ ላይ ቁፋሮ የሚጀምረው ሮቨር የተሰኘው ሠርሳሪ ሮቦት ወደ ጨረቃ ጥላማ ዋልታዎች በማቅናት የግግር ውኃ ናሙናዎችን ቆፍሮ በመውሰድ ኅዋ ላይ በሚመሰረተው የጠፈርተኞች የምርምር ጣቢያ ያቀብላል ተብሏል። ይኽ ሁሉ ሲታይ የሳይንስ ልብወለድ ይመስላል። ሆኖም ግን እስከዛሬ ድረስ የሳይንስ ልብወለድ የመሰሉ እጅግ ውስብስብ ጉዳዮች በሰው ልጆች እየተፈተሹ ለሰው ልጆች ጥቅም ላይ መዋላቸው ነገሩ አይኾንም ማለት ይከብዳል።

የስበት ኃይል ዜሮ በኾነበት የኅዋ ክፍል ከምድር ርቆ ከ186 ቀናት የጠፈር ምርምር ቆይታ በኋላ ወደ መሬት የተመለሰው እንግሊዛዊው ጠፈርተኛ ቲም ፒክ ከባልደረቦቹ ጋር ወደ ምድር ሲመለሱ ሁኔታው ከባድ እንደነበር ገልጧል። ወደ ምድር ለማረፍ በሚደረገው ሙከራ ችግር የሚፈጠር ከኾነ ቀድሞውኑም ከመመሬት ንፍቀ-ክበብ ውጪ በነበረው ጉዞ ችግር ነበር ማለት ነው፤ አለበለዚያ ሁሉንም ነገር በጥንቃቄ መከወን ከተቻለ ወደ መሬት ማረፉ አስቸጋሪ አይደለም ብሏል ቲም።

በእርግጥ እጅግ በፍጥነት ወደ ምድር የሚምዘገዘገው መንኲራኲር ከከባቢ አየር ጋር በሚኖረው የስብቀት ኃይል የሚፈጠረው ሙቀት 1600 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ እንደሚጠጋ ይነገራል። የሰው ልጅ በሞቃታማ አካባቢዎች የአየሩ ግለት 40 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ እጅግ ለአደጋ እንደሚጋለጥ ይታወቃል።

መንኲራኲሩ ከጠፈር ወደ መሬት ሲከንፍ የመሬት ንፍቀ-ክበብ ውስጥ ከመግባቱ አስቀድሞ ለሦስት ይክፋፈልና ጠፈርተኞቹን ከያዘው አካል ውጪ ያለው ክፍል በከባድ ፍንዳታ ብትንትኑ ይወጣል። ዕይታው እጅግ ልዩ እንደሆነ ሰሞኑን ከዓለም አቀፍ የጠፈር ምርምር ማዕከሉ የመጣው ተመራማሪ ቲም ገልጧል። መንኲራኲሩ ለሦስት ይከፈልና ከከባዱ ፍንዳታ በኋላ ብትንትኑ ይወጣል። ያኔ «የሚንቀለቀል ወላፈን በመስኮትህ አቅጣጫ ታያለኽ። የብረት ቁርጥራጮች እጅግ በቅርብ ርቀት ሲበታተኑ መመልከቱ ልዩ ስሜት ይፈጥራል» ብሏል።

«ወደ ምድር እይተመዝገዘክህ ከመሬት 100 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ስትደርስ ቀደም ብሎ በተረጋጋ ኹኔታ ምድርን በ400 ኪሎ ሜትር ስትመለከት ስለቆየኽ በመስኮት የምትመለከውን ፍጥነት የማትቆጣጠረው ሆኖ ይሰማሃል። እናም ከፕላኔት ወደ ምድር የምትወድቅ ያኽል አስደናቂ ስሜት ነው የሚሰማህ። ግዙፉ ዣንጥላ እስኪዘረጋ እና ፍጥነቱ ረገብ እስኪል ድረስ ጊዜው ዘግየት ስለሚል ግን ሰውነትህ ይላመደዋል።»

ለስድስት ወራት ግድም በዜሮ የስበት ቆይቶ በከፍተኛ የመሬት ስበት የሚጓዝበት መንኲራኲር አሽቆልቁሎ ሲበታተን የነበረውን አስደናቂ ትዕይንት ቲም በመስኮቱ ኾኖ ተመልክቷል። መንኲራኲሯ ለሦስት ከተከፈለች እና ከተበታተነች በኊላ የቀረው ባለሦስት ማዕዘኑ ኩብ ውስጥ ኾነህ ማዘቅዘቅህ ትንፋሽህን እንኳን ለመቆጣጠር ይሳንሃል ብሏል። ባለሦስት ማዕዘኑ ወደ ምድር መመለሻ ኩብ የመቆጣጠሪያ መሣሪያዎች እጅግ ስለሚግሉም በእጅ ለመንካት ይከብዳል። እውስጡ የአየር መቆጣጠሪያው እስኪያስተካክለው ድረስ አየሩ እጅግ ከመጠን በላይ ይግላል። ከዚያም የኩቧን ፍጥነት ለመቆጣጠር ግዙፍ ዣንጥላ ይዘረጋል። ያኔ ነገሮች ሰከን ይላሉ።

በዚያ መልኩ ቲም እና ሁለቱ ባልደረቦቹ፤ ሩስያ አሜሪካዊው የናሳው ቲሞቲ ኮፕራ እና ሩስያዊው ጠፈርተኛ ዩሪ ማሌንቼንኮ ከጠፈር ቆይታቸው ያለአንዳች አደጋ ወደ ምድር ተመልሰዋል። ሌሎች ሦስት ጠፈርተርተኞች ኅዋ ማዕከሉ ውስጥ ወደ ሚጠብቋቸው ሦስት ጠፈርተኞች ከአንድ ወር ባነሰ ጊዜ ይመጥቃሉ። እስከዚያው ድረስ የናሳው ጠፈርተኛ ጄፍ ዊሊያምስ ከሩስያ ባለልደረቦቹ ኦሌግ ስክሪፖችካ እና አሌክሴይ ሮስኮሞስ ጋር በኅዋ ማዕከሉ ምርምሩን እያከናወነ ይጠብቃቸዋል። የኅዋ ምርምሩ ወደ ሌላ ምዕራፍ እስኪሸጋገር ድረስ እንዲህ በፈረቃ በሒደት ይቀጥላል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ጠፈርተኛው ቲም ፒክ
ጠፈርተኛው ቲም ፒክምስል picture-alliance/empics/G. Fuller
ሦስቱ ጠፈርተኞች ከዓለም አቀፉ የኅዋ ምርምር ጣቢያ መልስ ካዛክስታን ውስጥ ከባልደረቦቻቸው ጋር
ሦስቱ ጠፈርተኞች ከዓለም አቀፉ የኅዋ ምርምር ጣቢያ መልስ ካዛክስታን ውስጥ ከባልደረቦቻቸው ጋርምስል Reuters/S. Zhumatov
ከዓለም አቀፉ የኅዋ ምርምር ጣቢያ መልስ ኩቧ ካዛክስታን ውስጥ በዣንጥላ ለማረፍ ተንሳፋ
ከዓለም አቀፉ የኅዋ ምርምር ጣቢያ መልስ ኩቧ ካዛክስታን ውስጥ በዣንጥላ ለማረፍ ተንሳፋምስል Reuters/S. Zhumatov
ዓለም አቀፉ የኅዋ ምርምር ጣቢያ ከፊል ገጽታ
ዓለም አቀፉ የኅዋ ምርምር ጣቢያ ከፊል ገጽታምስል ESA/NASA/Tim Peake
ጠፈርተኛው ቲም ፒክ ከዓለም አቀፉ የኅዋ ምርምር ጣቢያ መልስ ኮሎኝ ከተማ ውስጥ
ጠፈርተኛው ቲም ፒክ ከዓለም አቀፉ የኅዋ ምርምር ጣቢያ መልስ ኮሎኝ ከተማ ውስጥምስል DW/Z. Abbany

ነጋሽ መሐመድ