1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ጠንካራ ቅዝቃዜ በኢትዮጵያ

ማክሰኞ፣ ጥር 23 2009

እንደ ባዘቶ ጥጥ እየተበተነ በሚከመረዉ ብናኝ በረዶ የሚታጀበዉን ምህረት የለሹ የሰሜኑ ንፍቀ ክበብ አካባቢ የክረምት ወቅት የሙቀቱ መጠን ከዜሮ በታች ወርዶ በጣም ሲጠነክር ወራጅ ዉኃዎችን የበረዶ ንጣፍ ማድረጉ የተለመደ ነዉ።  ከሳምንት በፊት በጀርመን የተለያዩ አካባቢዎች ጠንክሮ የታየዉ ቅዝቃዜ ዉኃን መረማመጃ ድንጋይ አድርጎት ታይቷል።

https://p.dw.com/p/2Wiz4
Ungarn Parlament und Fluss Danube im Winter in Budapest
ምስል Reuters/B. Szabo

ጠንካራ ቅዝቃዜ በኢትዮጵያ

በዚህ አጋጣሚ ቀዝቃዛዉን የክረምት ወቅት ከነበረዶዉ የተላመደዉ ኅብረተሰብ በየቦታዉ ተጋግሮ በማይነቃነቀዉ ዉኃ ላይ ሲንሸራተት እና ሲዝናና መመልከቱ አዲስ ነገር አይደለም።

ከሰሞኑ የሙቀት መጠኑ ከዜሮ በታች 7 ዲግሪ መድረሱ በተነገረባት ደብረ ብርሃን ለመንሸታረቻ የሚሆን ባይሆንም ያለ ማቀዝቀዣ ድጋፍ ዉኃዉ ወደ ግግር በረዶነት መለወጡን ኗሪዎቿ ተመልክተዋል። አጥንት ድረስ ዘልቆ የሚያንሰፈስፈዉ የሰሜን ንፍቀ ክበቡ የክረምት ቅዝቃዜ በሚታይባቸዉ አካባቢዎች ዛፎች የደረቀ ጭራሮ መስለዉ ወራትን ማሳለፋቸዉ እንግዳ አይደለም። በዚህ የክረምት ወቅት ለምሳሌ ጀርመንን የተመለከተ ይህ ገፅታዋ ከሚያዝያ ጀምሮ የሚቀየር ቢሆንም አረንጓዴ ነገር ያላትም ላይመስለዉ ይችላል። የደብረ ብርሃኑ ብርድም ለተክሎቹ አልራራም ነዉ የሚሉት።

Deutschland Schnee in der Eifel
ምስል picture-alliance/dpa/H. Kaiser

በየጊዜዉ የአየር ጠባይ ሁኔታዎችን አስቀድሞ ለመጠቆም የሚሞክረዉ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሚቲሪዎሎጂ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ፈጠነ ተሾመ በደብረ ብርሃንና በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ስለታየዉ ጠንካራ ቅዝቃዜ እንደሚከተለዉ ይገልጻሉ።

ምንም እንኳን የአዉሮጳም ሆነ የሰሜን አሜሪካ እና የእስያዉ ነዋሪ ለአሰቃቂዉ ቅዝቃዜ እንግዳ ባይሆንም፣ አልፎ አልፎ በጥንቃቄ ጉድለት፣ በአቅም ማጣትና በመሳሰሉት ምክንያቶች በየዓመቱ ብርዱ በሰዉ ህይወት ላይ ሳይቀር ጉዳት ማድረሱ ሳይነገር አያልፍም። ከሰሞኑም በአፍጋኒስታኗ ጃዉዚጃን ክፍለ ሃገር የወረደዉ በረዶ ያስከተለዉ ከባድ ቅዝቃዜ ለበርካታ ልጆች ሞት ምክንያት መሆኑ ተነግሯል። በቅዝቃዜዉ ምክንያት የሳንባ ምች እና የሰዉነት ሙቀት መቀነስ ጤናቸዉን ያወከዉ 27 ሕጻናት የህክምና ርዳታ እንዳያገኙ በረዶዉ እንቅፋት እንደሆነባቸዉ ነዉ የተገለጸዉ። ሕንድ ዉስጥም የበረዶ ናዳ የገደላቸዉ ሰዎች ቁጥር 26 መድረሱ ተነግሯል። የደብረ ብርሃን አካባቢ ቅዝቃዜም ዓይነት እና መጠኑ ይለይ እንጂ ጉዳት አድርሷል።

እህልና አዝመራንም ብርዱ አበላሽቷል ጎድቷልም ይላሉ። ይህም የኅብረተሰቡ ዋነኛ የመነጋገሪያ ርዕሰ ጉዳይ ሆኖ እንደሰነበተም ካነጋገርናቸዉ ወገኖች ተረድተናል። በደብረ ብርሃንም ሆነ በተለያዩ ደጋ እና ወይናደጋ አካባቢዎች ላይ የታየዉ ከፍተኛ ቅዝቃዜ መንስኤዉን ለማብራራት የሞከሩት የሜትሪዎሎጂ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር በተጠቀሱት አካባቢዎች ቅዛቃዜዉ እንግዳ ባይሆንም ረዥም ጊዜ መቆየቱ አዲስ ነገር እንደሆነ ነዉ የገለፁት።

Ungarn Parlament und Fluss Danube im Winter in Budapest
ምስል Getty Images/AFP/A. Kisbenedek

ከደብረ ብርሃን እና አዲስ አበባ በተጨማሪም ሐረማያ፤ ሐረር ከተማ አካባቢ፣ በባህር ዳር አካባቢ፤ ሌላዉ ቀርቶ ቆላማ በሆኑ እካባቢዎች በአዳማ እና ጅጅጋን የመሳሰሉ አካባቢዎች ሳይቀሩ ዝቅተኛ የሙቀት መጠን እንደታየባቸዉ ነዉ አቶ ፈጠነ የገለፁልን።   ከጥቅምት ወር ያነሳዉ ቅዝቃዜ ይላሉ የደብረ ብርሃኖቹ ነዋሪዎች ከጥምቀት በዓል ወዲህ ትንሽ ሻል ብሏል።  እንዲያም ሆኖ የወደፊቱ የአየር ጠባይ ምን ሊሆን ይችላል የሚለዉ ያሳሰባቸዉ ይመስላል።

ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሃመድ