1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ጠቅላላ ምርጫ በናሚብያ

ረቡዕ፣ ኅዳር 8 1997

በደቡብ ምዕራብ አፍሪቃዊቱ ሀገር ናሚብያ ሁለት ቀናት የቆየው ምክር ቤታዊውና ፕሬዚደንታዊው ምርጫ በትናንቱ ዕለት አበቃ።

https://p.dw.com/p/E0kl
ናሚቢያዊው መራጭ
ናሚቢያዊው መራጭምስል AP

የቀድሞው የናሚብያ መሬት ጉዳይ ሚንስቴርትር ሂፊኬፑንየ ፖሀምባ ሀገሪቱን ካለፉት አሥራ አራት ዓመት ወዲህ የመሩትን ፕሬዚደንት ሳም ንዮማን ይተካሉ ተብሎ ተገምቶዋል። ሰባት ፕሬዚደንታዊ ዕጩዎችና ዘጠኝ የፖለቲካ ፓርቲዎች የተወዳደሩበት ምርጫ ይፋ ውጤት በነገው ዕለት ይወጣል ተብሎ ይጠበቃል።
በናሚብያ የገዢው የደቡብ ምዕራብ አፍሪቃ ሕዝብ ድርጅት፡ ስዋፖ ተፅዕኖ ጠንካራ ቢሆንም፡ ትናንት ባበቃው ምክር ቤታዊ እና በፕሬዚደንታዊ ምርጫ ላይ የተሳተፈው መራጭ ሕዝብ አሀዝ ከፍተኛ እንደነበር አስመራጩ ኮሚስዮን አስታውቋል። በግምት ወደ ዘጠና ከመቶ የሚጠጋ መራጭ ሕዝብ መሳተፉን ነው ኮሚስዮኑ የምርጫ ጣቢያዎች ከተዘጉ በኋላ ገልፆዋል። በሀገሪቱ የአሻካቲ አካባቢ ከታየና ሦስት ሰዎች ከተጎዱበት ግጭት በስተቀር ምርጫው በሰላማዊ፡ ነፃና ትክክለኛ ዘዴ መካሄዱ ተረጋግጦዋል። የመንግሥቱ ሂሰኛ እና የተቃውሞው የኑዶ ፓርቲ መሪና ፕሬዚደንታዊው ዕጩ ኩዋይማ ሪሩዋኮ ሳይቀሩ በምርጫው ክንውን መደሰታቸውን ገልፀዋል። የምርጫው ውጤት ይፋ የሚወጣበትን ጊዜ በጉጉት እንደሚጠባበቁ በማመልከት፡ ከቀናቸው ከአሥራ አራት ዓመት በኋላ የስዋፖ አባል ያልሆኑ የናሚብያ የመጀመሪያ ፕሬዚደንት እንደሚሆኑ አስረድተዋል። ሪሩዋኮ ፓርቲያቸው በምክር ቤታዊው ምርጫ ላይ ከአሥራ አምስት እስከ ሰባ ሁለት የብሔራዊውን ሸንጎ መንበሮች እንደሚያገኝ ተስፋ ቢያደርጉም፡ ታዛቢዎች ይህንኑ የሪሩዋኮ አባባል ገሀድ ሊሆን የማይችል ባዶ ምኞት አድርገው ነው የተመለከቱት። ባለፈው የመጨረሻው ምክር ቤታዊ ምርጫ ላይ ገዢው የስዋፖ ፓርቲ ሰባ አምስት ከመቶ ነበር ያገኘው። በመዲናይቱ ዊንድሁክ እየታተመ የሚወጣው ብቸኛው የጀርመንኛ ቋንቋ ዕለታዊ አልገማይነ ጋዜጣ ዋና አዘጋጂ ሽቴፈን ፊሸር ስዋፖ ባሁኑ ምርጫ ሁለት ሦስተኛውን የመራጭ ድምፅ እንደሚያገኝ ገምተዋል። ይሁንና፡ ይላሉ ፊሸር፡ ስዋፖ ባለፈው ምርጫ ያገኘውን ማለትም ከሰባ ከመቶ የሚበልጠውን የመራጭ ድምፅ አያገኝም። ስዋፖ ምን ያህሉን፡ ሌሎቹ ፓርቲዎችና ፕሬዚደንታዊ ዕጩዎች ደግሞ ምን ያህል የመራጭ ድምፅ ያገኛሉ የሚለው ጉዳይ ነው አሁን በጉጉት የሚጠበቀው። ባሁኑ ምርጫ ላይ በርካታ ፓርቲዎችና ዕጩዎች የተወዳደሩ ሲሆን፡ ይህ ዴሞክራሲ ለሚዳብርበት ድርጊት ማልካም አጋጣሚ እንደፈጠረ ፊሸር አክለው አመልክተዋል።
በናሚብያ ምርጫ ሥርዓት መሠረት፡ ንዑሳኑ ፓርቲዎች ሳይቀሩ በምክር ቤት የመወከል ዕድል አላቸው። በሌለኩል ግን በፕሬዚደንታዊው ምርጫ ላይ የስዋፖ ዕጩ ሂፊኬፑንየ ፖሀምባ በመጀመሪያው ዙር ምርጫ የአስፈላጊውን የብዙኃን ድምፅ እንደሚያገኙ አላጠራጠረም። ናሚብያን ለነፃነት ያበቁት የቀድሞው ፕኤዚደንት ሳም ንዮማ ባለፈው መጋቢት ወር ነበር ሥልጣናቸውን የለቀቁት። በመሬት መወረስ ዛቻ ተደናግጠው የነበሩት የሀገሪቱ ነጮች ገበሬዎች አዲሱ ፕሬዚደንት የቀድሞውን መንግሥት ፖሊሲ እንደሚከተሉ ተስፋ አድርገዋል። የገበሬቹ ፕሬዚደንት ራይማር ፎን ሀዘ እንዳስረዱትም፡ ፕሬዚደንት ሳም ንዮማ በተጨባጩ ገሀድ ሁኔታ የሚያምኑ መሪ መሆናቸውን አረጋግጠዋል፤ በነጮቹ የሚመራው ግብርናም ለሀገሪቱ ኤኮኖሚ ዕድገት ሰፊ ድርሻ ማበርከቱን በሚገባ ያውቃሉ። ተተኪያቸው ይሆናሉ ከሚባሉትም ጋር በተደረገ ውይይት፡ ፖሀምባ ነጮቹ ገበሬዎች አለመረጋጋት እንዲገጥማቸው የሚፈልጉ አይመስሉም።