1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ግጭት በሞዛምቢክ፣

ዓርብ፣ መጋቢት 27 2005

በሞዛምቢክ ማዕከላዊ ጠ/ግዛት በሶፋላ፣ ሙክሱንጌ በተባለችው ጣቢያ ትናንት ጎሕ ሲቀድ፤ በታጠቁ የተቃውሞው ፓርቲ የ«ሬናሞ» ደጋፊዎችና በፖሊሶች መካከል በተካሄደ ግጭት 4 ፖሊሶች መገደላቸውና 13 መቁሰላቸው ተነገረ። ይኸው ግድያ ከ 20 ዓመት

https://p.dw.com/p/18AjF
ምስል Getty Images/AFP

በላይ በአገሪቱ ሠፍኖ የቆየውን ሰላም በማደፍረስ እንደገና የአርስ በርስ ጦርነት እንዳያስነሣ አሥግቷል። የ ዶቸ ቨለ የፖርቱጋልኛው ክፍል ባልደረባ ዮሐንስ ቤክ ያቀረበውን ዘገባ ተክሌ የኋላ እንደሚከተለው አጠናቅሮታል።

የሞዛምቢክ ይዞታም ሆነ ፀጥታ ፤ በጥቂት ሰዓቶች ውስጥ እጅግ ደፍርሶ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱ ነው የተገለጠው። ባለፈው ሌሊት የሞዛምቢክ ብሄራዊ የተቃውሞ ንቅናቄ በፖርቱጋልኛ ምኅጻር «ሬናሞ» በመባል የታወቀው የቀድሞው የደፈጣ ውጊያ ድርጅት፣ በማዕከላዊው ጠ/ግዛት በሶፋላ፤ ሙክሱንጉ በተሰኘችው ጣቢያ የፈጥኖ ደራሽ ፖሊሱን ኃይል አጥቅቷል። ድርጊቱን የተከታተሉት፣ «ካናልሞዝ» የተሰኘው የሞዛምቢክ የ«ዖንላይን» ዜና አገልግሎት ዋና ሥራ አስኪያጅ ፌርናንዶ ቬሎሶ እንዲህ ብለዋል።

Mosambik Opfer von Zusammenstößen in Muxungue
ምስል Fernando Veloso

«የፖሊሱ ጣቢያ ከሌሊቱ 9 ሰዓት ከ 40 ጀምሮ ፣ 45 ደቂቃ ያህልr ያለማቋረዝ የተኩስ ዒላማ ሆኖ ነበር። የተጋጋለ የተኩስ ልውውጥ ከመደረጉም ከ 3-4 ጊዜ ያህል ከባድ ጦር መሣሪያ ተተኩሷል። ዛሬ ጧት አንድ ሰዓት ገደማ ላይ 4 ሰዎች መገደላቸውንና 13 መቁሰላቸውን ለመገንዘብ ችለናል።»

የሬናሞ አባላት የተጠቀሰውን እርምጃ የወሰዱት፤ በዋዜማው የፈጥኖ ደራሹ ፖሊስ ኃይል፣ ሙክሱንጌ ላይ ያካሂዱት የነበረውን ሰብሰባ በትኖ 15 አባሎቻቸውንም ወስዶ በማሠሩ ነው ። ፖሊስ ደግሞ ሰዎቹ የታያዙት የጦር ልምምድ በማድረጋቸው ነው ብሏል። ማኒካ በተሰኘው ሌላ ማዕከላዊ ጠ/ግዛት፤ ጎንዶላ በተባለችው ጣቢያም ባለፉት ቀናት ፤ ሳምንታትና ወራት በፖሊስና በሬናሞ መካከል ውዝግቦች በተደጋጋሚ ማጋጠማቸው አልታበለም። በተለይ አንድ ዘመን ፤ የሬናሞ ዋና ምሽግ በነበረው ጠ/ግዛት በሶፋላ ፍጥጫው ኃይለኛ ነው። የእርስ በርስ ጦርነት ይካሄድ በነበረበት ዘመን፣ በዚሁ ጠ/ግዛት፣ በጎሮንጎንሳ ብሔራዊ ፓርክ ፣ «ካዛ ባናና » የተባለው ጣቢያ የደፈጣው ድርጅት ዋና ማዕከል እንደነበረ ይነገራል። የሬናሞ ዋና ኀላፊ አፎንሶ ድላካማም በአሁኑ ጊዜ፤ ድርጅቱ በመንግሥት እየተገለለ የመጣበትን ሁኔታ ለመቃወም ፣ ከተወሰኑ የፓርቲው አባላት ጋር በመምከር፤ የደፈጣ ውጊያውን ድርጅት እንደገና ለማንቀሳቀስ ከመሻታቸውም፤ «ወደ ጫካ ገብተን እንደገና የደፈጣውን ውጊያ እንጀምራለን» በማለት በተደጋጋሚ መዛታቸውም ተጠቅሷል። በሞዛምቢክ የአደናዎር ድርጅት ተጠሪ ሱልታን ሙሳ፣ የአርስበርሱ ጦርነት እንደገና ሊጋረሽ ይቻላል ባይ ናቸው።

Mosambik Opfer von Zusammenstößen in Muxungue
ምስል Fernando Veloso

«መንግሥት ከሬናሞ ጋር የሚደረገውን ማንኛውንም ውይይት ቁም ነገር ያለው አድርጎ አልወሰደውም። በህገ-መንግሥቱ ላይ እንደሠፈረው፤ ሮማ ላይ በተፈረመው የሰላም ውልም መሠረት፤ ውይይቱ በፓርላማ መከናወን ይኖርበታል። ይሁን እንጂ፤ ሬናሞ በፓርላማ ያን ይህል ተሰሚነት የሚያስገኝ ውክልና አላገኘም። ተዳክሟልና ተጽእኖ ማሳደር አቅቶታል። ስለሆነም ከፓርላማ ውጭ ከመንግሥት ጋር መነጋገር ይሻል። መንግሥት ደግሞ ይህ ተፈላጊ ነው ብሎ አልተቀበለውም።»

አሁን ታዲያ፤ ለመበቀል ቃጥቶታል። እ ጎ አ በ 1992 ኦ ም የፍሬሊሞ ንቅናቄ መንግሥትና አማጺው ሬናሞ ሰላም ለመፍጠር ቢስማሙም፤ ሁሉም የሬናሞ ተዋጊዎች ትጥቅ አለመፍታታቸው የታወቀ ነበር። የፍሬሊሞ አስተዳደር እንደገና ውጊያ እንዲካሄድ ፍላጎቱ አይደለም። እርግጥ የሬናሞ መሪ ድላካማ 400 ገደማ የሚሆኑትን ተዋጊዎቻቸውን ትጥቅ ያስፈታሉ ብሎም አይተማመንባቸውም። በሶፋላ ጠ/ግዛት ጎሮንጎንሳ ብሔራዊ ፓርክ አዋሳኝ ማሪንጌ በተሰኘው መንደር የሚገኘው ምሽግቸው በፖሊስ በጥብቅ ክትትል ይደረግበታል። ውደ ውስጥ መግባት ግን ለማንም፤ ለገለልተኛ ታዛቢም ቢሆን ክልክል ነው። ሬናሞም በበኩሉ፤ እንደገና ውጊያ እከፍታለሁ እያለ በተደጋጋሚ መዛቱ ተዓማኒነት እንዲያገኝ ሲልም ቢሆን ትጥቅ እንዲፈታ አያደርግም።

የሰላም ውል ከተፈረመ በኋላ በመጀመሪያው ምርጫ፣ ከሞላ ጎደል የተሣካ ዕድል ነበረ የገጠመው እ ጎ አ በ 1999 ዓ ም እንዲያውም፤ ድላካማ 47,7 ከመቶ የመራጩን ህዝብ ድጋፍ በማግኘት የዮአኪም ቺሳኖን ዳግም መመረጥ ለጠቂት ለማሰናከል ተቃርበው እንደነበረ አይዘነጋም።

የሆነው ሆኖ የድላካማው ሬናሞ በተለይ በከተሜዎች ዘንድ እስከዚህም ተቀባይነት አላገኘም። ባለፉት ጥቂት ዓመታት ራሳቸው ድላካማ ፣ የፓርቲያቸውን ሥልጣን ባይለቁም፣ ከበሰሜናዊው የአገሪቱ ክፍል በናምፑላ ተገልለው መኖርን ነበረ የመረጡት።

እ ጎ አ በ 2009 በተካሄደው ምርጫ፣ 16,4 ከመቶ ብቻ የሚሆነውን የሞዛምቢክ ህዝብ ድምጽ ነበረ ለማግኘት የበቁት። በመጪው ኅዳር በሚካሄደው የማዘጋጃ ቤቶች ምርጫ፣ በፓርላማ ከተወከሉት 3 ፓርቲዎች መካከል እንደማይሳተፍ ያሳወቀ ሬናሞ ብቻ ነው። የምርጫው ኮሚሽን፤ በአንድ ፓርቲ ብቻ የተያዘ ነው ሲሉ የገለጹት፣ የሬናሞ ዋና ጸሐፊ ፣ ማኑኤል ቢሶፖ፣ ከ 16 ቀናት በፊት በሰጡት መግለጫ ላ ይ እንዲህ ብለው ነበር።

Mosambik Opfer von Zusammenstößen in Muxungue
ምስል Fernando Veloso

« መጪው ምርጫ፤ ግልጽ፤ ነጻና በፍትኀዊ መንገድ የሚያዝ እስካልሆነ ድረስ ፣ ሬናሞ እንዲካሄድ አይፈቅድም። በዚሁ ምርጫ አንሳተፍም፤ ከኛ መሥዋእትነትን የሚጠይቅ ቢሆንም እንኳ!»

ድሮ፤ መፍቀሬ ምዕራብ፣ መፍቀሬ የገበያ ኤኮኖሚ መሆኑ ይነገርለት የነበረው ሬናሞ፣ ከእርስበርሱ ጦርነት ፍጻሜ በኋላ፤ በኤኮኖሚው መስክ አልቀናውም። በአንጻሩ፤ ቀድሞ የምሥራቁ ዓለም ተባባሪ የነበረው ማርክሳዊው ፤ሶሺያሊስቱ፣ ፍሬሊሞ ምርታማ ኩባንያ ነው የመሰለው። በድንጋይ ከሰልና የተፈጥሮ ጋዝ በመታጋዝ ፣ ጥሬ ዕቃዎችን በሰፊው በማቅረብ አመርቂ የኤኮኖሚ ዕድገት አስገኝቷል።

ተክሌ የኋላ

አርያም አብርሃ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ